የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የማይከራከር

“እንግዲህ ኤጲስ ቆጶስ እንዲህ ሊሆን ይገባዋል፤… የማይከራከር” 1ጢሞ. 3፡2-3
ሰው የአስተሳሰቡ ውጤት ነው ። አስተሳሰቡ የአስተዳደጉ ውጤት ነው ። አስተዳደግ መደበኛ ያልሆነ ከመደበኛው ትምህርት ቤት ግን የበለጠ የምንማርበት ነው ። አስተዳደግ ተግባራዊ ትምህርት ቤት ነው ። ክርስቶስ ሕይወታችንን ካልለወጠ ይዘን የምንዞረው አስተዳደጋችንን ነው ። አስተዳደግን በመደበኛ ትምህርት ፣ በዕድሜ መለወጥ አይቻልም ። እውቀት ያለንን ነገር የሚያዳብር እንጂ የሚለውጥ አይደለም ። ዕድሜም አስተዳደጋችንን የበለጠ የምናጠነክርበት ነው ። ሰው ሁሉ ክርስቶስን ተሸክሞ ካልዞረ አስተዳደጉን ተሸክሞ ይዞራል ። እኛን አይወዱንም በሚል ቤተሰብ ያደገ ሰው ዘረኛ ይሆናል ። ቆንጆ ነህ ተብሎ ያደገ ራሱን ለዝሙት ይሸጣል ። ሰነፍ ተብሎ ያደገ ሌሎችን ማመስገን ይቸገራል ። እኔ በሚል አስተዳደግ ያደገ ለሌሎች ስሜት ግድ የለሽ ይሆናል ። በብዙ እንክብካቤ ያደገ ጥገኛ ይሆናል ። እኛ በሚል አስተዳደግ ያደገ ከቤተሰቡ ውጭ ሌላውን መውደድ ይቸገራል ። በስድብ ያደገ ሌሎችን በማዋረድ ይረካል ። በበታችነት ስሜት ያደገ ትዕቢተኛ ይሆናል ። በመልኩ ሲሰደብ የኖረ ቆንጆ የሚባሉትን ይጠላል ። በቀለሙ ሲተች ያደገ ሌላ ቀለም ያለውን ሰው ለመግደል ይነሣሣል ። ከአመክንዮ የራቀ አስተዳደግ ያለው ያለ ምክንያት ሰው ይጠላል ። ሴት ብቻ ባለበት ቤት ውስጥ ያደገ ወንድ ብቻ ጥሩ ይመስለዋል ። ወንድ ብቻ ባለበት ቤት ውስጥ ያደገ ሴት ብቻ ጥሩ ትመስለዋለች ። በጥላቻ ያደገ ሰው ሁሉ ክፉ ይመስለዋል ። በዱላ ያደገ በቀለኛ ይሆናል ። ይቅርታን በማያስተምር ቤተሰብ ያደገ የሰውን ስህተት ማለፍ ይከብደዋል ። እኔን ብቻ አዳምጡኝ በሚል ቤተሰብ ያደገ ለፍላፊ ይሆናል ። በር ተዘግቶበት ያደገ ሰውን ሁሉ ይጠራጠራል ። በውግዘት ያደገ የሰዎችን እንከን ይፈልጋል ። በቅናት ያደገ በሌሎች በጎ ዕድል መደሰት ያቅተዋል ። ጉድለት አለብህ ተብሎ ያደገ ነጭናጫ ይሆናል ። አትችልም ተብሎ ያደገ መሞከር ይፈራል ። ሳይገራ ያደገ ክርክር ይወዳል ። የእግዚአብሔር አገልጋይ ግን የማይከራከር ሊሆን ይገባዋል ።

ክርክር ፍቅርን የሚያጠፋ ነው ። እውነትን ቢይዝም ክርክር ስህተት ነው ። ምክንያቱም እውነትን የሚናገረው ሰዎችን ለማሳወቅ ሳይሆን ለመርታት ነው ። የክርክር ዓላማው የበላይነትን ለማሳየት ነው ። የክርክር ዓላማው ሌላውን አጠልሽቶ ራስን ውብ አድርጎ ለማቅረብ ነው ። የክርክር ዓላማው ሌላውን ጥሎ ለማለፍ ነው ። ክርክር ለፖለቲካ እንጂ ለኑሮ መልካም አይደለም ። ክርክር ሌሎች እንዲሰለቹን የሚያደርግ ነው ። ክርክር የሥጋ ሥራ ነው /ገላ. 5፡20/ ። ክርክር የሥጋ ሥራ ከሆነ የሚከራከሩ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም ። ክርክር የሕፃንነት ጠባይ ነው ። ደቀ መዛሙርት ማነው ትልቅ እያሉ ይከራከሩ ነበር /ማቴ. 18፡1/ ። ክርክር የሌሎችን ነጻ ፈቃድ አለማወቅና አለማክበር ነው ። ክርክር ሱስ ነው ። ክርክር ግጥሚያ ነው ። ግጥሚያነቱም የቃላት ግጥሚያ ነው ። ክርክር የነቀፋ ፣ የዘለፋና የስድብ መውጫ ነው ።
ክርክር የአሳብ ልውውጥ አይደለም ። ክርክር በአሳብ የበላይነት ሳይሆን በእኔነት የበላይነት ማመን ነው ። ክርክር የእውቀት ብርሃን የሚያስገኘው የአሳብ ፍጭት አይደለም ። ክርክር መናገር እንጂ መስማት የሌለበት ነው ። ክርክር እኔ እንጂ እኛ የማይል ነው ። ክርክር በራስ አጥር ውስጥ መዞር ነው ። ክርክር እውቀት ከመስጠት በእውቀት ስም ሌሎችን ማሳነስ ነው ።
ክርክርን የሚወልዱ ነገሮች አሉ ። እነዚህም፡-
1-  በአስተሳሰብ አለመብሰል፡- ዕድሜና እውቀት እየገፋ ሲመጣ እውቀት የሌለው መሃይም ማንም እንደሌለ እንረዳለን ። ሰዎችን ሁለት እርምጃ ወደ እኛ ለማምጣት አንድ እርምጃ ወደ እነርሱ መሄድ ተገቢ እንደሆነ እንረዳለን ።
2-  ሕፃንነት፡- ሕፃናት ቁመት ሲለካኩ ይውላሉ ። ቢረዝሙ የሚያገኙት ነገር ባይኖርም ከሌላው በመብለጣቸው ደስ ይላቸዋል ። ሌላውን መብለጥ ብቻ የሚፈልግ ትሑት መሆን አይችልምና ከእግዚአብሔር መንግሥት ይርቃል ።
3-  የቃል ሰው ብቻ መሆን፡- የምናውቀውን መኖር ቢያቅተን የምናምነውን መኖር ተገቢ ነው ። የቃል ሰዎች ግን የሚያውቁትና የሚያምኑትን መለየት ያቅታል ። ሰው በኑሮው ሲረታ እንጂ በቃል ሲረታ ጊዜያዊ ድልን ብቻ ያገኛል ።
4-  ጭብጨባን ፈላጊነት፡- መታከም ከሚገባቸው ስሜቶች አንዱ ጭብጨባ ፈላጊነት ነው ። ጭብጨባ ፈላጊዎች ስሜታዊ እንጂ እውነተኛ ወዳጅ የላቸውም ። ስሜት የሚበርድ ነውና መልሰው ይነቀፋሉ ። ክርክር ከጭብጨባ ፈላጊነት ይመነጫል ።
ሰው ከራሱ ፣ ከሰዎችና ከእግዚአብሔር ጋር ክርክር ውስጥ ይገባል ። የክርክር ጥልቅ ትርጉምም ይህ ነው ። ሰው ከራሱ ጋር ክርክር ውስጥ ሲገባ ትላንትና ላይ መቆየት ይጀምራል ። ያጣቸውን ነገሮች መቊጠርና ማዘን ይፈልጋል ። በስህተቱ ከመጠን በላይ ያዝናል ። የቀደመ ስህተቱ ዛሬን እንዲበክልበት ይፈቅዳል ። ቆሻሻ ቦታ መቆየት ለመቆሸሽ ነው ። ረጅም ሰዓት በስህተት ፊት መቆየትም ለመረበሽ ነው ። የራሱን መልካምነት በጣም እያሰበ ምላሽ አጥቻለሁ በማለት ጥያቄ ውስጥ ይገባል ። ፍቅርን ለማትረፍና ፣ ጥሩ ሰው ነው ለመባል የሄደባቸው ርቀቶች ጠላትነትን ብቻ እንዳተረፉበት ያስብና ክፉ መሆን ሳያዋጣ አይቀርም የሚል አስተሳሰብ ውስጥ ይነከራል ። ክፋትንም ሲያደርግ እንደ ክፉዎቹ አይረጋጋም ። ክፉዎቹ ቀጥተኛ ኑሮአቸው ሲሆን የእርሱ ግን መጨነቅ የወለደው ነውና ። ይህ ሰው ራሱን በክርስቶስ ካላየ አይድንም ። አንድ የእግዚአብሔር አገልጋይ እንዲህ ያለ ክርክር ውስጥ ካለ የሚያገለግለውን ሕዝብ እየጎዳ ይመጣል ። አገልግሎቱ ሁሉ መረበሽ ያለበት ፣ የዝቅተኛነት መንፈስ የሚያሰቃየው ይሆናል ። “እኔ ማን ነኝ ?” “ወላጆቼ እነማን ናቸው?” የሚል ክርክር በውስጡ ያለበት ሰው አለ ። የማይሞተውን ወላጅ ሥላሴን ይዞ የሚሞቱ ወላጆችን አጣሁ ብሎ መጨነቅ አይገባም ።
ከሰዎች ጋር ክርክር ውስጥ የገቡ ሰዎች አሉ ። እነዚህ ሰዎች በሰዎች መካከል እየተሟገቱ የሚኖሩና ብቻቸውን የሚኖሩ ሁለት መደብ ያላቸው ናቸው ። በሰዎች መካከልና ከሰዎች ርቀው የሚኖሩ በሰዎች ደረስብን የሚለውን እያሰቡ ቀኑን በሙሉ ሲከራከሩ ይውላሉ ። እነዚህ ሰዎች ይቅርታ ማድረግ በጣም የሚቸገሩ ፣ ዓለም ሁሉ ጠፍቶ ያለሁት እኔ ብቻ ነኝ የሚሉ ናቸው ። እነዚህ ሰዎች ምንም ነገር መስማትም ማየትም የማይፈልጉ ሲሆን ጥንቃቄአቸውን አልፎ ከሰሙና ካዩ ለሰዎች ያላቸው ጥላቻ ይበልጥ እየጨመረ ይመጣል ። ከዓመታት በፊት ሰዎች የተናገሩአቸውን እንደ አሁን ማሰብ ይጀምራሉ ። ከሰዎች ጋር ሲገናኙም የሚያወሩት ፣ ሰው ክፉ መሆኑን ነው ። ይህን አልፎ በፍቅር የሚያክማቸው ሰው ካገኙ  በጣም ጠቃሚ ሰዎች ይሆናሉ ። አሊያ ራሳቸውን የሚያክሙበት ዘዴ ይቅርታ ብቻ ነው ። ከሰው ጋር ክርክር ያላቸው ሰዎች አትኩረው የሚያዩና አጣርተው የሚሰሙ ናቸው ። ነገሮችን በመልካም ጎናቸው አይቶ ከመደሰት የችግሩን ክፍል መፈለግ ይቀናቸዋል ። አንድ አገልጋይ ከሰዎች ጋር ክርክር ካለው አገልግሎቱ የጎዱትን ሰዎች ለመንካትና ለመበቀል ይሆናል ። የንግግሩ ቃና ፣ የስብከቱ አድራሻ የጎዱት ሰዎች ይሆናሉ ።
ከእግዚአብሔር ጋር ክርክር ያላቸው ሰዎች በራሳቸው ሕይወት በደረሰባቸውና በሌሎች ሰዎች ሲደርስ ባዩት ክፉ ነገር እንዴት እግዚአብሔር ዝም አለ? ብለው ያዘኑ ናቸው ። ፍትሕ ሲጠፋ ፣ ሐሰተኛ ረታሁ ብሎ ሲጨፍር ፣ ደካማ ሲገፋ ፣ ጉልበተኛ ጣልኩኝ ብሎ ሲዘል ይህች ዓለም በእግዚአብሔር ተጥላ ያለ አስተዳዳሪ ቀርታለች ማለት ይጀምራሉ ። የጎዱአቸው ሰዎች እያበቡ እነርሱ ግን እየኮሰሱ የመጡ ሲመስላቸው እግዚአብሔርን መቀየም ይጀምራሉ ። ጸሎትን ሊያቆሙ ከመንፈሳዊ አገልግሎትም ሊወጡ ይችላሉ ።የእግዚአብሔር ፍርድ በእነርሱ ጊዜና እነርሱ በሚፈልጉት መንገድ ባለመከናወኑ ብስጩ እየሆኑ ይመጣሉ ። ክርክር ያለባቸው ሰዎች ወደ መንፈሳዊ ሹመት ከመጠራታቸው በፊት ሊለወጡ ይገባል ።
ኤጲስ ቆጶስ እንዲህ ሊሆን ይገባዋል ።
1ጢሞቴዎስ 43
ጥር 26 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲ.አ.መ.
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ