የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የምሕረቱ ዕቃዎች

እግዚአብሔር በምሕረቱ የሚገለጥበት ዙፋን የሰው ልጅ ነው ። በየዕለቱ ያለውን ክፋትና መጠላለፍ ስናይ ከሰው ግድፈት በላይ የእግዚአብሔር ምሕረት ይደንቃል ። ይህ ምሕረት ያላስፈለገው በሥራው የቆመ ጻድቅ ፣ በችሎታው የሚኖር ኃያል ማንም የለም ። ሰዎች የሰውን ሕይወት ለመቅጨት ሲያስቡ እነርሱ ያልሰጡትን ሕይወት ለመንሣት ፣ እነርሱ ያላወጧትን ፀሐይ ለመከልከል እየከጀሉ እንደሆነ እንረዳለን ። ፀሐይን የሰጠ ጌታ ያልከለከለውን እኛ ፣ የእኛ ባልሆነ ሀብት እንዴት እንከለክለዋለን ? እግዚአብሔር ደምስሶን ቢያድር ጻድቅና ትክክለኛ ነው ። የሚገርመው ግን ዛሬም እኛን በፍቅር ማነጋገሩ ነው ። ሰው ከእግዚአብሔር ርቆ ሲኖር የሚሰማው የራሱን አሳብ ብቻ ነው ። ስለዚህ “እኔ ዋጋ የለኝም ፣ አልድንም” ብሎ ያምናል ። አዎ የምሕረቱ ዜና ያለው በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ነው። የእግዚአብሔር ምሕረት ብዙ ነገሮችን ያከናውናል ። ወይም ያለ ምሕረቱ የተደረገልን በጎነት አንዳች የለም ። ከሁሉ በላይ ምሕረቱን መዘመር ያስደስታል ።
ሰማይ እንደ ጃንጥላ የተዘረጋልን ፣ ምድር እንደ መርከብ የሆነችልን በምሕረቱ ነው ። እግዚአብሔር አምላክ ከተባሉት አማልክት የሚለየው በምሕረት ጠባዩ ነው ። እነርሱ ግብር ሲጎድልባቸው ለመግደል ይነሣሉ ። እግዚአብሔር ግን ምስጋናውን እያስቀረን ገና ሊሰጠን ይኖራል ። ከብዙ ጌቶች እግዚአብሔርን ልዩ ጌታ የሚያደርገው ምሕረቱ ነው ። ጌቶች “ከአህያ አመድ ፣ ከድሃ ገንዘብ አይታጣም” እያሉ አስጨንቀው ይገዛሉ ። እግዚአብሔር ግን ሳይቀበል የሚሰጥ ቸር ጌታ ነው ። እግዚአብሔር ብሑተ ህላዌ ወይም የብቻነት አኗኗር ያለው አምላክ ነው ። እግዚአብሔር ብቸኛ አይደለም ፣ ብቻውን ግን የሚሠራ አምላክ ነው ። እኛንም ሲምረን ማንንም አያስፈቅድም ። ምሕረት እንዲደረግልን የድጋፍ ፊርማ አምጡ ብንባል ማንም አይፈርምልንም ። ቢፈርሙልንም በቀን ሰባት ጊዜ ለምናብድ ለእኛ የሚፈርም አናገኝም ።
በሰማይ ዣንጥላ ፣ በመሬት መርከብ የሚያንሸራሽረን እግዚአብሔር ፣ ሰማይን ያለ ምሰሶ ፣ ምድርን ያለ ካስማ ያፀና እግዚአብሔር ፣ በውኃ ላይ ይህን የሚያህል ታላቅ ቤት የሠራ አዶናይ እንዴት ድንቅ ነው !? ፀሐይን በቀን ማሰልጠኑ ምሕረቱ ነው ። ምክንያቱም ፀሐይ ካልወጣ መሰማራት ፣ ፀሐይ ካልጠለቀም መሰብሰብ አይቻልም ። እግዚአብሔር እንደወጣን እንዳንቀር በጨለማ ፣ እንደገባን እንዳንቀር በብርሃን መግቦት ያንሸራሽረናል ። ፀሐይ ቶሎ በማይጠልቅባቸው አገራት መኪናው ሲሄድ ያመሻል ። ልጆች መሰብሰብ አይፈልጉም ። ፀሐይን ማውጣትና ማስገባቱ ምሕረቱ ነው ። ለካ ማታ ልጆችህን ለመሳም ፣ ሚስትህን ለማየት የበቃኸው በምሕረቱ ነው ? ሌሊቱ ጨርሶ እንዳይጨልም ጨረቃና ከዋክብትን ያደረገው ያ ምሕረቱ ነው ። ፀሐይ በመሰወሯ ፈጽሞ እንዳያዝን ጨረቃን አወጣ ። በጨለማው ውስጥም ብርሃን አለ ። ሲነጋ “ደግሞ ነጋ” ማለት ተገቢ አይደለም ። ሁልጊዜ ለምንበድለው ፣ ለዛሬ የኃጢአት ቀጠሮ ላለን ሰዎች በማንጋቱ ልንደነቅ ይገባል ። እኛ ዛሬ የበደሉን ሰዎች እንደሚበድሉን ብናውቅ ኑሮ ወዳጅ አናደርጋቸውም ነበር ። እያወቀ የወደደን ግን መሐሪው እግዚአብሔር ነው ። በሞት መንደር ውስጥ በሕይወት የሚያኖር ፣ የብረት መዝጊያ በሚደፈርበት ዘመን የእኛን የጭራሮ መዝጊያ ባለ ግርማ የሚያደርግ ያ ምሕረቱ ነው ። በእጁ እየሰጠ የሚያጠግበን ፣ በክንዱ እየመከተ የሚጋርደን ምሕረቱ ግድ ስላለው ነው ። እናቶች እየተከተሉ “ልጄ ተመለስ” ሲሉ ልጁ “ተይኝ በቃ” ሲል እናት የሚሉት አንድ ቃል አለ፡- “ሆዴ እንቢ አለኝ ።” ምሕረቱ እንቢ እያለው እኛን የሚከተል ጌታ በእውነት ድንቅ ነው ። ታዲያ እኒያ እናት ሲብስባቸው ፣ ልጃቸው አልረዳ ሲላቸው “ወልደህ እየው” ይላሉ ። ምናልባት የወለድነው የእግዚአብሔር አባትነት እንዴት እንደሆነ እንዲሰማን ይሆን ? ልጃችን ተኝቶ ዓይን ዓይኑን እናየዋለን ። እርሱ አያየንም ፣ እኛ እናየዋለን። እግዚአብሔር ሳናየው ብዙ ዘመን ያየን መሐሪ አባት ስለሆነ ነው ።
አባትም ፣ እናትም ፣ ወዳጅም ፣ መንግሥትም ትዕግሥታቸው ያልቃል ። ሆደ ሰፊ የተባሉት ሁሉ ምሕረታቸው ይገደባል ። “እስመ ለዓለም ምሕረቱ፣ አያልቅም ብዙ ነው የአምላክ ቸርነቱ” የተባለለት ግን ለዘላለም ይኖራል ። እኛ ትክክለኛው ጠባችን የሚጀምረው የታረቅን ቀን ነው ። ከቀድሞ ቅያሜአችን በላይ ስንታረቅ በተነጋገርነው ቃል እንቀያየማለን ። የእኛ ይቅርታ በአሸዋ ላይ የተጻፈውን በደል በአለት ላይ የሚቀርጽ ነው ። እግዚአብሔር ግን ሲምር የሚምር አምላክ ነው ።
ከኃያላን ባላጋራዎች የሚያድነን ፣ በመዋረዳችን ከፍ የሚያደርገን ፣ በሚያስፈልገን ነገር የማይጨክንብን በምሕረቱ ነው ። ምሕረቱ ለዓለም ሁሉ የተሰጠ እንጂ የግለሰቦች መጽናኛ አይደለም ። እኛ ስንበድል እግዚአብሔር መሐሪ ነው ፣ ሰዎች ሲበድሉ እግዚአብሔር ፈራጅ ነው እንድንል የሾመን ማነው ? የእኛ ኃጢአት በስውር ኑዛዜ እንዲያበቃ ፣ የካህናት ኃጢአት በአደባባይ እንዲናዘዝ ይህን ያደላደለ ማነው ? ምሕረቱ ለምእመንና ለካህን ልዩነት የለውም ። መድኃኒት ለታመመ ሁሉ ነው ። ምሕረቱም ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ ነው ። እኛ እርስ በርሳችን ስንፈራረድ በዓለም ያሉ “የእኛማ ኃጢአት እንዴት ይቅርታ ያገኛል ?” ብለው እየሸሹን ነው ። የምሕረቱ ዕቃዎች መሆን ሲገባን የምሕረቱ መጋረጃዎች ሁነናል ። የእግዚአብሔርን ምሕረቱን ለራሳችን ፣ ፍርዱን ለሌሎች የምንመኝ ከሆነ በጣም ምስኪኖች ነን ። ያለፉት ቅዱስ ፓትርያርክ አንድ ሰው ገብቶ እግዚአብሔር ይገለብጦታል ፣ ይፈርድቦታል በማለት በእምነት ሳይሆን በወንድነት ድፍረት ተናገራቸው ። እርሳቸው ግን ሳቁና ፡- “በአንተ የሚታዘዝ እግዚአብሔር ካለ የማላውቀው እግዚአብሔር ነው” አሉ ይባላል ። እግዚአብሔር በራሱ ምክር የሚሠራ ነው ።
ሥጋችሁ ያሸነፋችሁ ፣ ዓለም በቆሻሻ እጇ መላልሳ ያቆሸሸቻችሁ ኑ ወደ እግዚአብሔር ። ይቀበላችኋል ። እግዚአብሔር እንደ ዲያቆኑም እንደ ሰባኪውም አይደለም ። እግዚአብሔር እንደ ራሱ ነው ። እናንተ የክርስቶስ የደሙ ዋጋ ያለባችሁ ውድ ናችሁ ። አስተውሉ ምእመናን ፣ አማኝ ከሚባሉ ሰዎች ጋር ስትጣሉ የእግዚአብሔር ምሕረቱ ለምን ይሰወርባችኋል ? ምሕረቱን ካላሰባችሁ መጸለይም ፣ ንስሐ መግባትም ፣ ቅድስናን መቀደስም አትችሉም ።
በእውነት እግዚአብሔር የማረን የምሕረቱ ዕቃዎች እንድንሆን እንጂ እንድንመጻደቅ አልነበረም ። “እነርሱንማ ይቅር ካለ እኛንም ይቅር ይለናል” እንዲባል አስቀድሞ ዋነኛ ኃጢአተኞቹን እኛን ማረን ።
ተንቀሳቃሽ የምሕረቱ ማስረጃዎች እኛ ነን ።
እግዚአብሔር በምሕረቱ ዜማ እንደገና ያባብላችሁ ።
ተጻፈ በአዲስ አበባ
ሚያዝያ 20/2010 ዓም

ያጋሩ