የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የምሕረት አዋጅ

ያጌጡ ከተሞች የደስታ ማስታወቂያ እንጂ ደስታ የላቸውም ። ሁልጊዜ ለመደሰት ሙከራ ይደረጋል ፣ ስሜት ጊዜያዊ መልስ አግኝቶ ወዲያ መከፋት ይጀምራል ። ልብን የሚያሳርፍ ደስታ ግን ከዓለማዊ ነገር ሊገኝ አይችልም ። ያማ ከሆነ ደስታ ሸቀጥ ፣ ወይም የፍለጋ ውጤት ሆነ ማለት ነው ። ደስታ የኑሮ ፍሬ እንጂ በተፈጥሮ የሚታደሉት አይደለም ። ፍሬ ነውና ሁሉም የሚኖረው እንጂ እገሌ ያለው ፣ እገሌ የሌለው ተብሎ እንደ ጸጋ የሚመደብ አይደለም ። የደስታ ፍሬ እንጂ የደስታ ጸጋ የለም ። ዓለም በዚህ ኃጢአት ደስታ ያጣውን ሰው ሌላ እንዲሞክር እየመከረች ከድጡ ወደ ማጡ ትነዳዋለች ። ዮሐንስ መጥምቅ ይህችን ዓለም ሲመንን አልተሳሳተም ። የደመቀ ከተማ ዕረፍት ቢሰጥ ኖሮ ተነሣሕያን ወደ ምድረ በዳ አይመጡም ነበር ። የበደለኝነት ስሜት በመጠጥ ፣ በሱስ ዝም ሊል አይችልም ። የበደለኝነት ስሜት ራስን በመቅጣት ፣ በችሎት ተገቢውን ፍርድ በማግኘት ረጭ የሚል አይደለም ። የበደለኝነት ስሜት ከእግዚአብሔር ምሕረት ጋር በመገናኘት ብቻ ይገሠጻል ።

ዮሐንስ መጥምቅ ይቅር ተብላችኋል የሚለውን የምሥራች ለመንገር የእግዚአብሔር ምሕረት ተጨባጭ እንዲሆንላቸው በውኃ ያጠምቃቸው ነበር ። ሰውዬው ንስሐ የገባበትን በደል እየቀሰቀሱ በአደባባይ ፣ የእግዚአብሔር ቀጪ ነን ብለው የሚናገሩ በዮሐንስ አገልግሎት ፊት መቆም አይችሉም ። የሃይማኖት ተግባሩ መግለጥ እንጂ ማጋለጥ አይደለም ። መግለጥ ሰውዬውን ሕመሙን አስረድቶ ለንስሐ ማብቃት ነው ። ይቅር አልተባልሁም የሚል ስሜት ቢሰማው እንኳ፡- “የውቅያኖስ ውኃ በቤት ጥራጊ አይቆሽሽም ፣ በእግዚአብሔር ምሕረት ፊት ያንተ በደል እንደዚህ ነው” እያሉ ያረጋጉታል ። ሰው ግን የሚዘምረውን ፣ የሚያስቀድሰውን ወገኑን ለማሸማቀቅ ፣ የሰውዬው ትላንት ላይ ቆሞ ይቀራል ። ኦ ንስሐ የምንገባው ሰዎች እንዲያምኑን አይደለም ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ለመታረቅ ነው ። እርሱ ይቅር ካለን ማነው የሚከስሰን ? አንድ ክርስቲያን በአደባባይ የወንድሙን በደል ካወራ ክርስቲያንነቱ እያበቃ ነው ። ምክንያቱም ክርስቲያን የሆነው በክርስቶስ ደም ተከልሎ እንጂ በብቃቱ ተመዝኖ አይደለምና ። ዮሐንስ መጥምቅ ሆይ ምንኛ ቅዱስ ሰው ነህ ! የበደለ ያርፍ ዘንድ እንዲህ ትተጋለህ !

ውኃ የቆሸሸውን ያጥባል ፣ የዕለትና የዘመናት እድፍን ያጠራል ። በደለኛም በእግዚአብሔር ምሕረት አዲስ ሰው ሁኖ ይቆማል ። አንዳንድ ተነሣሕያን / ንስሐ ገቢዎች/ የማልቀስ አቅም የላቸውም ። ሁሉንም በደላቸውን ለማስታወስም ይቸገራሉ ። እግዚአብሔር ግን ከእኛ የሚፈልገው በደለኛ መሆናችንን ማመን ብቻ ነው ። የምሕረት ነጋዴዎች “ይህን ያህል ገንዘብ አምጣ ኃጢአትህ ይቅር ይባላል” ሊሉ ይችላሉ ። ምሕረቱ ግን ከደሙ የተነሣ ገንኖ ይኖራል ። ምሕረትን እንቀበለዋለን እንጂ አንሸምተውም ። የምንገዛው ምሕረት የለም ፣ የገዛን ምሕረት ግን አለ ። ማልቀስ ስላልቻለ ፣ ሁሉንም የኃጢአት ዝርዝር ስላልተናገረ ይቅር እንዳልተባለ የሚሰማው ይኖራል ። ንስሐ ግን የትግል ፍሬ ሳይሆን የደሙ ውጤት ነው ። “የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኃጢአት ሁሉ ያነጻናል።” (1ዮሐ. 1 ፡ 7 ።) ከቤተ ክርስቲያን ምሥጢራት አንዱ ንስሐ ነው ። ንስሐ ምሥጢር ፣ ንስሐ ጸጋ ነው ።

ቢያነባ መጸጸቱን አመልካች ነው ፣ ውኃውም ምልክት ነው ። ይቅር ማለት ግን የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው ። ዮሐንስ መጥምቅ የእግዚአብሔርን ምሕረት ተጨባጭ ለማድረግ በእጅ በሚዳሰስ መልኩ የይቅርታ ስሜት እንዲሰማቸው በውኃ ያጠምቅ ነበር ። ተነሣሕያኑ አሉ ፣ የንስሐ ሰባኪውም አለ ፣ ይቅር ባዩ ክርስቶስም ተገኝቷል ። ራሳችንን እንድናይ የሚያግዙን ውሉደ ክህነት የሆኑት የንስሐ ሰባኪዎች ይደነቃሉ ። ሰውን በድለሃል ማለት ከባድ ዋጋ ያስከፍላል ። መንግሥትን አጥፍተሃል ማለት ከምድረ ገጽ ሊያጠፋ ይችላል ። ሰውን በድለሃል ማለት እንዴት ደፈርከኝ ? ያሰኝ ይሆናል ። መንፈሳውያን አባቶች ግን ይህን የማድረግ ትልቅ ሥልጣን አላቸው ። ማንም የሥነ ልቡናና የሥነ አእምሮ ባለሙያ “ይቅር ተብለሃል” ማለት አይችልም ። ሥልጣን የተሰጣቸው ውሉደ ክህነት ግን ይቅርታን ያውጃሉ ።

“ይቅር ተብለሃል” ከሚል የበለጠ የምሥራች የለም ። ሰዎች በመጠጥና በሱስ ውስጥ የሚያልፉት ከበደለኝነት ስሜት ለመውጣትም ነው ። የሕሊና ክስ በእግዚአብሔር ምሕረት ካልሆነ በምንም ሊቆም አይችልም ። ሰይጣን እንድንበድል ያደርገናል ፣ ስንበድል ደግሞ ይከስሰናል ፣ ንስሐ ስንገባ “ይቅር አልተባልህም” እያለ በራሱና በሰዎች በኩል ይዋጋናል ። ዮሐንስ መጥምቅ ማማር በሌለው በረሃ የሚያምር የምሥራች ይናገር ነበር ። የሚታይ ውበት የሌለው ሰው እግሮቹ ያማሩ ነበሩ (ሮሜ. 10 ፡ 15) ። መልካሙን የምሥራች ያወራልና ። ዛሬም ኃጢአት የሚያስጨንቃቸውን ያህል ይቅር አልተባልሁም በሚል ስሜት የሚሰቃዩ አሉ ። ንስሐ እምነት ነው ። በደልንና ምሕረቱን ማመን ነው ። ይቅር አልተባልሁም ማለት “አንተ ይቅር አትልም” ብሎ እግዚአብሔርን መሳደብ ነው ።

ንስሐ የገባችሁ ወገኖች ይቅር ተብላችኋል ። ደስ ይበላችሁ ! የሚበልጥ ጸጋ ይጠብቃችኋል ። “እኔስ ለንስሐ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ጫማውን እሸከም ዘንድ የማይገባኝ ከእኔ በኋላ የሚመጣው ግን ከእኔ ይልቅ ይበረታል፤ እርሱ በመንፈስ ቅዱስ በእሳትም ያጠምቃችኋል” (ማቴ. 3 ፡ 11)።

በበዓለ ጥምቀቱ የሚነገረው የምሥራች ይህ ነው !

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥር 18 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ