የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የምንከተለው ማንን ነው ?

“እንግዲህ እንደ ተወደዱ ልጆች እግዚአብሔርን የምትከተሉ ሁኑ”

ኤፌ. 5 ፡ 1 ።

ሥልጠና እንኳን ሰውን እንስሳትን ሳይቀር ይለውጣል ። ከመመርመሪያ ማሽኖች ይልቅ መርማሪ ውሾች ውጤታማ እየሆኑ ነው ። ወደዚህ ብቃት የደረሱት ግን በሥልጠና ነው ። ሥልጠና የሰውን ሀኬተኛነት በመውሰድ ትጋትን ይሰጣል ። ትላንት የማይችለውን ነገር እንዲችል ያደርገዋል ። ሥልጠና ዘላንነትን ወደ ሥነ ሥርዓት ፣ የተለምዶ ነዋሪነትን በዓላማ ወደ መኖር ይቀይራል ። ዛሬ አሉን የምንላቸው በጎ ነገሮች የሥልጠና ውጤት ናቸው ። ሥልጠና ሌሎች ለእኛ ይሰጡናል ፣ ራሳችን ለራሳችንም የምናስለምደው የሕይወት መርህ ነው ። ሥልጠና በመጀመሪያው አለማወቅንና አለመቻልን ያሳያል ፣ ቀጥሎ ማወቅና መቻልን ያመጣል ። ሥልጠና ራስን ማስለመድ ነው ። ራሳችንን ስፖርት ካስለመድነው ራሱ አምጡ ይለናል ። ሥልጠና ወደ መልካም ሱስ ይከተናል ። መልመድ ሳይሆን መለማመድ በመሆኑ ሥልጠና ዋጋ የሚያስከፍል ነገር ነው ። ክርስትና በዚህ ዘመን ቅመሙን አጥቶ አልጫ የሆነው ፣ በአረመኔነት ተቀምሞ የሰውን ሕይወት የሚቀጨው ሥልጠና ወይም ራስን ማስለመድ በመጥፋቱ ነው ። ክርስትና መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ፣ አለቃ ፣ መርህና የሚኖሩለት ዓላማ ያለው ነው ። ዛሬ ክርስቲያኑ ለራሱ አባት ፣ ለራሱ ልጅ እየሆነ ሲመጣ ፣ ራሱ መርህና ራሱ ግብ እየሆነ መጣ ። በዚህ ምክንያት  የሚታየው በቀዳዳ ስልቻ የመሙላት ትግል ውስጥ ገባን  ። ዛሬ ከምናያቸው የጭካኔና የዘረኝነት ፉጨት ጀርባ ክርስቲያን ነን የሚሉ አሉበት ። መነቃቃት አገኙ የተባሉ ከተሞች ሳይቀር አንገት የሚቀላባቸው የጭካኔ ካምፕ ሁነዋል ። ድንቄም መነቃቃት !! የአገሬ ሰው፡- “ጽድቁ ቀርቶ በቅጡ በኰነነኝ” የሚለው ለዚህ ነው ። ክርስትና ራስን ማስለመድና መለማመድ የሚፈልግ ነው ። መንፈሳዊ ዕድገት ማለት ተአምራዊ ዕድገት አይደለም ። በተአምራት እንፈወሳለን እንጂ አንለወጥም ። መንፈሳዊ ዕድገት ደግሞ ራስን የማስለመድ ውጤት ነው ።

“ተመልከት ዓላማህን ፣ ተከተል አለቃህ” ይባላል ። የወታደር ቤትን ልዩ የሚያደርገው የሚመለከተው ዓላማና የሚከተለው አለቃ ያለበት መሆኑ ነው ። ወታደር ከሀ እስከ ፐ በሥነ ሥርዓት የታነጸ ነው ።  ወታደር የሚያሰኘው ልብሱ ሳይሆን ዲሲፕሊኑ ነው ። ራሱ ጸንቶ በመቆም አገሩን ለማቆም የሚጥር ነው ። የወታደር ዓላማው አገሩንና ሕዝቡን መጠበቅ ነው ። ወታደር ዘርና ጎሣ አለኝ ብሎ ለዚያ ካደረ ወታደርነቱ እያበቃ ይመጣል ። ከፍ ብሎ የተሰቀለ ፣ የሚኖርለትና የሚሞትለት ዓላማ ያስፈልገዋል ። በዓላማው መሠረትም አለቃውን መከተል ያሻዋል ። ክርስቲያንም ልክ እንደ ወታደር ዓላማውን ፍቅር ፣ አለቃውን ክርስቶስ መከተል አለበት ። ፍቅርን የጣለ ፣ ክርስቶስን ከመከተል የተመለሰ ክርስቲያን ሊሆን አይችልም ። ክፋትን ካልተጠየፈ ፣ ወንጀልን ካላወገዘ ክርስቶስን እንደ ገና በታሪኩ የሚሰቅል ይሆናል ።

ራስን ማስለመድና መለማመድ ያለበት ሥልጠና አንዱ መገለጫው መከተል ነው ። እንስሳት መጀመሪያ የሚሰለጥኑት የሚያሰለጥናቸውን በመከተል ነው ። በስልጠና ውስጥ መቀመጥ ፣ መቆም ፣ ሰላምታ መስጠት ፣ መከተል ወሳኝ ናቸው ። የሚከተሉት በአለቃው እርምጃ መጠን ነው ። የሚመራቸውን ማወቅና መንገዳቸውን ይዘው መሄድ ይገባቸዋል ። ሰውም ከፍ ያለ ፍጡር ቢሆንም መሪ ያስፈልገዋል ። ሰው በዋናነት የሚከተለው እግዚአብሔርን ነው ። ልጆቻችንን ማሰልጠን አለብን ። ሳንናገር እንድንግባባ አድርገን ፣ ሁሉን እንዲወዱና ሁሉን እንዲያፈቅሩ አድርገን ማለማመድ ያስፈልገናል ። ቤተ ክርስቲያንንና አገራቸውን እንዲያፈቅሩ ፣ ድሆችን በፍቅርና በርኅራኄ እንዲመለከቱ ተግተን ማስተማር ይገባናል ። ማሰልጠን እስኪይዙት ድረስ በጣዕም ማስተማር ፣ በተግባር አርአያ መሆንና ማለማመድ ያለበት ነው ።

ተወዳጅ ልጆች የሚባሉት ወላጆቻቸውን የሚከተሉ ሲሆኑ ተወዳጅ ክርስቲያኖችም እግዚአብሔርን የሚከተሉ ናቸው ። እግዚአብሔርን የሚከተሉትም ውስጣዊ ጥላቻን በማራቅ ፣ የተበዳይነት ስሜትን በመጣል ፣ ግልፍተኛነትን በመተው ፣ አስደንጋጭ ቍጣን በማራቅ ፣ በጩኸት አሳምናለሁ ብሎ መነሣትን በማቆም ፣ የሰውን እንከን እየፈለጉ ማዋረድን በመጠየፍ ፣ ሰውን ጠልፎ መጣልን እንደ ቆሻሻ በመመልከት ነው ። ኤፌ. 4 ፡ 31 ።

እየተከተልን ያለነው ማንን ነው ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን ። አንድ ሰው በጣም በኦርቶዶክሳዊነቱ አትንኩኝ ባይ ነው ። በቅርብ ሰሞን ግን ዘሩና ጎሣው እያንገበገበው ይሳደባል ። “ከክርስትናህና ከጎሣህ ?” ብለው ቢጠይቁት “ጎሣዬ ይበልጥብኛል” አለ ። አንዳንድ ሰው ሃይማኖቱን የያዘው ጎሣው እስኪመጣ መጠበቂያ አድርጎ ነው ። እየተከተልን ያለነው ወቅታዊ ዘፈኖችን ፣ ጊዜ የሰጣቸው ወሬዎችን ፣ የፖለቲከኞችን የተስፋ ዳቦ ሊሆን ይችላል ። እግዚአብሔርን መከተል ግን ወደ ዘላለም ደጃፍ ያደርሳል ።

መከተል መሰልጠን ነው ። ትውልዳችንን በዘረኝነት ሳይሆን በፍቅር ማሰልጠን ያስፈልገናል ። ገና ጨዋታ ሳይጠግቡ ቂምን እያስታጠቅን የዕድሜ ልክ ታማሚ ማድረግ የሚበጅ አይደለም ። ልጆቻችንን በቁም መግደል ነው ። ወጣቱ እያጠፋ ነው ፣ እያየንም ነው ። የሚለውጠው ግን ትምህርት ነው ። በቂ እውቀትና ሀብት ያላቸው ትውልድን ለመቅረጽ ፣ በፈሪሀ እግዚአብሔር ለማነጽ መነሣት አለባቸው ። በማውገዝ ብቻ ሰው አይለወጥም ፣ እኛም አናርፍም ።  እግዚአብሔርን ስለ መከተል ማስተማር ይዋል ይደር የማንለው ተግባራችን ሊሆን ይገባል ። ያለን ብቸኛ መፍትሔ ትውልድን ማስተማር ፣ በፈሪሀ እግዚአብሔር ማነጽ ብቻ ነው ። የተለወጠ ትውልድ ያልተለወጠን አገር ይለውጣል ፣ ያልተለወጠ ትውልድ ግን የተለወጠን አገር ያፈርሳል ።

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሐምሌ 18 ቀን 2012 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ