የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የምእመኑ ማቃሰት

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ረቡዕ ኅዳር 11/2006 ዓ.ም.
ጌታዬ ሆይ! ስለምን ተውኸኝ? እኔን ከማናገር ዝምታን፣ እኔን ከመዳሰስ ርቀትን ለምን መረጥህ? አምላክ እንደሌለው ስረገም፣ ወዳጅ እንደሌለው ስከሰስ፣ ዳኛ እንደሌለው ስኰነን ለምን ዝም ትላለህ? የእኔና የአንተ የጥንቱ ፍቅራችን የት ደረሰ? በእኔስ አንጀትህ እንዴት ጠና? በስንት ተራራ አብረኸኝ ስለነበርህ ከባዱ ቀለለኝ፣ ዛሬ ግን ቀላሉ ከበደኝ፡፡ ያላንተ መስኩ ተራራ፣ ሜዳው ሸለቆ ነው፡፡ አንተ የሌለህበት፣ የራስን ድምፅ በልዑል ድምፅ የሚሰሙበት ባዶ አዳራሽ ነው፡፡ ያሳለፍኩትን የልቅሶ ዓመታት ሳስብ ከዚህ በኋላ ሌላ ልቅሶ ይኖራል ብዬ አስቤም አላውቅ ነበር፡፡ ልቅሶ ግን ርእሱ ይቀየራል እንጂ እንደማይቀር አውቅሁ፡፡ ዛሬ ለእኔ ጥቁር ቀን ነው፡፡ ያንን የቤትህን ክብር፣ የካህናትህን ሞገስ የት ወሰድከው?
እግዚአብሔርም መለሰ፡– ልጄ ወዳጄ ሆይ! ጊዜ የወለደውን ፍቅር ጊዜ ይወስደዋል፡፡ የእኔ ፍቅር ግን ከጊዜ በፊት የነበረ ዘላለማዊ ነውና ይለወጣል ተብሎ አይሰጋም፡፡ ሰዎች ብዙ ጊዜ ይተውኛል እንጂ እኔ ማንንም ትቼ አላውቅም፡፡ ልቀቀን በራሳችን እንቆማለን ሲሉኝ ስለቃቸው ይንገዳገዳሉ፡፡ እንኳን እነርሱን፣ እነርሱን የተሸከመች ምድርም በመዳፌ ላይ እንዳለች ይረሳሉ፡፡ ልጄ አጠገብህ ሳለሁ ህልውናዬ የራቀብህ መስሎሃል፡፡ የቀኑ ጥያቄ፣ የኑሮ ትግሉ፣ የወዳጆችህ መንሸራተት፣ የምትወደው መራቅ፣ የምትጠላው ነገር መጣበቅ ይህንን ስሜት እንዳመጣብህ አውቃለሁ፡፡ ዝም ያልኩህ መሰለህ እንጂ በአገልጋይ፣ በመጻሕፍት በየቀኑ እየተናገርኩህ ነው፡፡ ድምፄ የህልውናዬ ካንተ ጋር የአብሮነቴ መገለጫ ነው፡፡ እኔ ባለሥልጣን ነኝ፣ ደግሞም አይጠቅምህምና ዝርዝሩን እንዳስረዳህ አትጠብቅ፡፡ ርእሱ የከበደህ ዝርዝሩ እንደሚያደክምህ አውቃለሁ፡፡ ልጄ ሆይ ወዶ መጥላት፣ ታምኖ መክዳት በእኔ የለም፡፡ ዝምታዬ እንኳ ላንተ ጥቅም ተሠርቷል፡፡ የምታደርገውን ለማወቅ አንዳንዴ አጠገብህ እያለሁ እሰወራለሁ፡፡ ልጄ ሆይ ቃል ካበዛህ እኔን መስማት አይሆንልህም፡፡ ኢዮብ አንደበትህ 37 ምዕራፎች ይናገራል፡፡ እኔም እስክትጨርስ ዝም እልሃለሁ፡፡ ሰው እየተናገረ መናገር አልችልም፣ ክብሬ ይከለክለኛል፡፡ ዝም ስትል ግን ላንተ የፈጠርኩትን ዓለም ሰሌዳ አድርጌ አስተምርሃለሁ፡፡ ልጄ ሆይ! የምትችል ይመስልሃልና አልመቻልህን እንድታውቅ እነዚህ ቀኖች ልክ ማሳያ ናቸው፡፡ አዎ ልጄ ቀን ብሎ ጨለማ ከባድ ነው፡፡ ማንም አያውቅልህም፡፡ ግን ሰው ቢያውቅም ሊረዳህ ፈቃዱም ኃይሉም የለውም፡፡ እኔ ግን አንተን ለመርዳት ፈቃዱም ኃይሉም አለኝና አይዞህ! ይኸው ድምፄን እየሰማህ ለምን ትፈራለህ? ድምፄ ድምፅን ይሽራል፣ ኃይሌ ኃይልን ያስቀራል፡፡ እኔ ተናግሬህ ማንን ትፈራለህ? እኔ ከረዳሁህ ማን ይችልሃል?
ልጄ ሆይ! ልብህን ስጠኝ፣ እኔ ለጆሮ መናገር አልወድም፡፡ ያ ጠባሳህ የሻረው በእኔ መዳሰስ፣ ያ ስብራትህ የተጠገነው በእኔ መናገር ነው፡፡ ለምን አይተህ እንዳላየ ትሆናለህ? ልጄ ሆይ፣ ክፉዎች ቢረግሙህም ቢመርቁህም አይሠራም፡፡ ሁለት ጆሮ የሰጡሁህ እኔን አብዝተህ እንድትሰማ እንጂ እኔንና ሌሎችን እንድትሰማ አይደለም፡፡ ስላንተ የሚቆረቆር ቢታጣ፣ የሚያውቁህ በችሎት ዱዳ ቢሆኑ፣ እንጀራቸውን ላለማጣት ቢፈርሙብህ አትደነቅ፡፡ የሚጸናው የእኔ እንጂ የሰው ውሳኔ አይደለም፡፡ ልጄ ሆይ፣ ፍቅራችን አሁንም ያው ነው፡፡ ራስህንም እንዲህ የወደድከው በእኔ ነው፡፡ ራስህን ለመቀበልም የረዳኹህ እኔ ነኝ፡፡
ልጄ ሆይ! እኔ የሌለኹበት መስኩም ተራራ፣ ሜዳውም ሸለቆ፣ ገነትም ሲኦል ነው፡፡ የራስንም ድምፅ መስማት አስፈሪ ነው፡፡ የገጠመህ አዲስ ልቅሶ ሳይሆን አዲስ ትምህርት ነው፡፡ ሁሉን መድኃኒት በአንዴ ብትውጥ ትሞታለህ፡፡ ሕይወትም በእንክብል መልክ ተሰጥታሃለች፡፡ ልጄ ሆይ፣  በጥቁር ቀንም ብርሃንን ማወጅ እችላለሁና አትፍራ፡፡ ለጨለማው ሳይሆን ለእኔ ክብር ዘምር፡፡ የቤቴን ክብር የአገልጋዮቼን ሞገስ የምመልስበት ዘመን ደርሷል፡፡ አንተ ግን በመጠበቂያህ ላይ ፀንተህ ጠብቀኝ፡፡

አስተያየት ይስጡ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ያግኙን

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ስልክ ፡ +251930006086                             +251911699907

ኢሜል፡ ashumekon@gmail.com

የገጹ ዓላማ

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።

አሸናፊ መኮንን
Ashenafi Mekonnen
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
Commercial Bank of Ethiopia
1000165078482

አቢሲኒያ ባንክ
Bank of Abyssinia
23202573

ሕብረት ባንክ
Hibret Bank
1030416569497017

ወጋገን ባንክ
Wegagen Bank
0870286030101

አዋሽ ባንክ
Awash Bank
01320034656200

በማህበራዊ ሚዲያ ይወዳጁን።

copyright @ 2021 ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን 
በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።