የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሬሳ ቁንጅና

 “እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን ፥ በውጭ አምረው የሚታዩ በውስጡ ግን የሙታን አጥንት ርኩሰትም ሁሉ የተሞሉ በኖራ የተለሰኑ መቃብሮችን ስለምትመስሉ ፥ ወዮላችሁ ።” ማቴ. 23፡27
የትያትር መነሻ ፣ ታሪካዊ ዳራው በዘርፉ ባለሙያዎች ሊተነተን ይችላል ። ትያትር ግን የጀመረው በሃይማኖት ስም በሚደረግ ጥፋት ነው ። የትያትሩ ጀማሪም ቃየን ነው ። ቃየን መሥዋዕት ሲያቀርቡ አይቶ ያቀረበ ነው ። መሥዋዕት ማቅረብ የሚጠይቀው ሀብት ነው ፤ ልብን ለማቅረብ ግን የሚጠይቀው ሃይማኖት ነው ። መሥዋዕት ያለ ልብ ለበጣ ነው ፣ መሥዋዕት ከልብ ጋር ፍቅር ነው ። የልብ አማኝና የታይታ አማኝ አቤልና ቃየን ናቸው ። ተዋናዩ ቃየን ወንድሙን ገደለ ። ቃየን ፍሬን መሥዋዕት አድርጎ በማቅረብ ጀመረ ፣ ወንድሙን በመግደል ፈጸመ ። ግብዝነት ቁራሽ ጽድቅ ሲያሳይ መደምደሚያው ግን መግደል ነው ። ግብዞች የዘመናቸው ጠላት እውነተኛ ሰው ነው ። ሐሰታቸውን ያጋለጠባቸው ስለሚመስላቸው ፣ እውነተኛውን ሰው በሞት ያርቁታል ። ጻፎችና ፈሪሳውያን ሕጉን በቃላቸው የሚያውቁ በኑሮአቸው ግን የካዱት ናቸው ። ውጫቸው ሃይማኖታዊ መሳይ ውስጣቸው ግን በፍላጎት የሸፈተ ነው ። ይህን አይቶ የሚወቅሳቸው ቢመጣ “ሃይማኖት ውስጥ ያለው ፖለቲካ ያልገባው ነው” ብለው ያልፉታል እንጂ አይበሳጩም ። የልቡን የሚሠራ መቼ ይበሳጫል ! እግዚአብሔርን እወዳለሁ እያሉ ወንድምን መጥላት ቃየናዊ መሥዋዕት ፣ ያልተፈተነ ፍቅር ነው ።
የቲያትር ኑሮ በመልአክ ዕድሜ የነበረ ነው ። የመድረክ ተውኔት የተከበረ ሥራ ሊሆን ይችላል ። የምንናገረው በሕይወቱ ስለሚተዉን ወገን ነው ። ሰይጣን የብርሃን ገፀ ባሕርይን በጣም ይወዳል ። ጨለማ መሆኑ ስለሚያሳስበው ተሽቀዳድሞ ብርሃናዊ ለመምሰል ይፈልጋል ። ልብ አድርጉ ሰይጣን በራሱ ስም መጥቶ አያውቅም ፣ በእግዚአብሔር ስም ይመጣል ። ሰይጣን ብርሃን ይመስላል እንጂ ብርሃን መሆን አይፈልግም ። ይህም ድንቅ አይደለም ፤ ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና ።” 2ቆሮ. 11፡14 ። አንዳንድ ውሸት ባለቤቱን ሳይቀር ያሳስታል ። ውሸታሞች የሚያለቅሱት ውሸቱ ለራሳቸው እውነት ስለሚመስላቸው ነው ። የውሸት ችግሩ ሰውዬውን ራሱን ማታለሉ ነው ። ሰው አታልላለሁ ብሎ የተነሣው ሰውዬ ተታሎ ያለቅሳል ፣ አታልላቸዋለሁ ያሉት ይነቁበታል ። ለጊዜው ያጭበረብራል ። ሰይጣን የብርሃን መልአክ እስኪመስል የብርሃን ልብስ ይለብሳል ። ተዋናዩ ከመድረክ ሲወርድ የሚቸኩለው ልብሱን ለማውለቅ ነው ። የድራማ ኑሮ ያደክማልና ። አጥንቶ መስበክ ፣ አጥንቶ ማፍቀር ፣ አጥንቶ ደግ ፣ ደግ ማውራት ይደክማል ። እውነት ሳይጠና ይፈስሳል ።
ጌታችን የገሠጸው በተውኔት ኑሮአቸው ፣ በግብዝነት አቋማቸው ትልቅ ደረጃ ላይ የወጡትን ፣ የሃይማኖታዊ ተውኔት ራስ የሆኑትን ጻፎችና ፈሪሳውያንን ነው ። እነዚህን ወገኖች፡- “እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን ፥ በውጭ አምረው የሚታዩ በውስጡ ግን የሙታን አጥንት ርኩሰትም ሁሉ የተሞሉ በኖራ የተለሰኑ መቃብሮችን ስለምትመስሉ ፥ ወዮላችሁ” አላቸው ።
ሞታችኋል እያላቸው አይደለም ያለው ። ከሞት አልፋችኋል እያላቸው ነው ። በሁለት ዓይነት የሞት መደብ ውስጥ ያሉ ሰዎች አሉ ማለት ነው ። የመጀመሪያው በቁማቸው ሞተው የሚንቀሳቀሱ ናቸው ፣ ሁለተኛዎቹ ደግሞ ሞትን ጌጥ አድርገው የሚኖሩ ናቸው ። ፈሪሳውያን በሁለተኛው ምድብ ላይ ነበሩ ። እንዲህ ያሉ ሰዎች ውሸታቸው እግዚአብሔርንም የሚያታልል እየመሰላቸው ይታለላሉ ።
ሰውየው ወደ ጦር ሜዳ ዘምተው ሲመለሱ ትጥቃቸውን ሁሉ አስረክበው ነበር ። ሚስታቸው፡- “ጋሻው የታለ ?” ሲሏቸው “አስረክቤዋለሁ” አሉ ። “ጦሩስ የት አለ ?” ሲሏቸው “አስረክቤዋለሁ” አሉ ። “ጠመንጃውስ የት አለ ?” ሲሏቸው “አስረክቤዋለሁ” አሉ ። ሚስትየው ባላቸውን ትኩር ብለው ሲያዩ ዝናር ወገባቸው ላይ አለ ። “ዝናሩስ እንዴት ተረፈ ?” ቢሏቸው “እስከዚህስ ሞቻለሁ መሰለሽ ?” ብለው መለሱ ይባላል ። ጋሻው ከተወሰደ ፣ ጦሩ ከተነጠቀ ፣ ጠመንጃው ከተገበረ ወዲያ ምን ቀረ ? ራስን ለማጽናናት ግን በዝናር መፎከር ከንቱ ነው ። ዝናሩ ያለ ጠመንጃው ከድንጋይ ጠጠር የማይሻል ፣ ከቀበቶም የማያልፍ ነው ። መከላከያ ጋሻው ተነጥቆ ፣ ማጥቂያ ጦሩ ተወስዶ ፣ ቆመው የሚልኩት ጠመንጃው ተወርሶ በዝናር መመካት አልሞት ባይ ተጋዳይነት ነው ። ከዝናሩ በቀር ምን የቀረን ነገር አለ ? የቀረን የፌስ ቡክ ፉከራ ፣ የቀረን በኢንተርኔት ጫካ ተደብቆ መለፍለፍ ነው ። ርኅራኄው ፣ ሰው ተቀባይነቱ ፣ ቸርነቱ ፣ የሰው ክብር ፣ የአገር ፍቅር ፣ የንጉሥ ክብር ፣ የሽማግሌ ምክር ፣ የአባት ምርቃት … ይህ ሁሉ ርቆናል ። የምንመካው ፣ አልሞትንም የምንለው መተኮሻ በሌለው ዝናር ነው ። ያለፉት አርባ ዓመታት የተደበቀው የአውሬ ጠባያችን ገሀድ የወጣበት ነበር ። አባት ልጁን ፣ ልጅ አባቱን ያስገደለበት የጉድ ታሪካችን ነው ። ዛሬ ደግሞ የተደበቀው ብልግናችን ዘመን ባመጣው መገናኛ እየወጣ ያለበት ነው ። የቀረን ምንድነው ? አልሞትንም ብለን ለመናገር ያልደፈርነው የቱን ይዘን ነው ? መስቀልና ሽጉጥን ስንቀላቅል አልሞትንም ወይ ? የምድር ነገሥታትን የሃይማኖት አባቶች ሲማጸኑና መጠጊያ ሲያደርጉ አለን ወይ ? የቀረው ልብሳችን እንጂ ሁሉም ተማርኳል ። ያልሠራነው ምን አለ ? የድብቅ ኃጢአተኞች ፣ የግልጽ ጻድቃን ስለሆንን ተውኔቱን ስላስረዘምነው ብቻ ነው ። የሚያድነን መሞታችንን መቀበላችንና የትንሣኤውን ጌታ መማጸናችን ብቻ ነው ። ሳንድንበት መድኃኔዓለም አዳነን እንላለን ፣ ሳንገዛለት ኢየሱስ ጌታ ነው እንላለን ። ስንት ጣዖት በልባችን አዝለን አንድ አምላክ እያልን እንፎክራለን ። ሰውዬው እንዳሉት “አልሞትንም ብለን አንዋሽም ።”
ምንም ባንቀበር ባንገባ መሬት ፣
አያሳፍረንም ሞተናል ማለት ፤
የሞተና ሞቱን ጌጥ ያደረገ ሁለት ዓይነት ሟቾች አሉ ብለናል ። ስለ ሞተ ሰው እስቲ እንናገር ። የሞተ ሰው አለ ግን የለም ። መሞት ማለት እያሉ አለመኖር እንጂ እየሌሉ አለመኖር አይደለም ። ኖሮ መሞት ጸጋ ነው ፣ ሞቶ መኖር ግን ዕዳ ነው ። የሞተ ሰው አሳቡን በሰው ስለጣለ ያለ ልክ የሚከብድ ነው ። አገርን ለመሪው ብቻ ሰጥቶ ፣ ቤተ ክርስቲያንን ለአገልጋይ ብቻ ሰጥቶ መኖር ከዚህ በላይ መሞት የለም ። የማይሠሩ እጆች ይዘን የሚሠሩ እጆችን መንቀፍ ይህ ሞት ነው ። ሌላው ከሚገርፍህ እኔ ብገሸልጥህ ይሻላል ብሎ ጭካኔውን ቂቤ ማስመስል ይህ ሞት ነው ። ስለ ተቆረጠ ጽረዳ እያለቀሱ ስለሚቆረጡ ወጣቶች አለማዘን ይህ ሞት ነው ። የሞተ ያስጨንቃል ። እስኪቀበርም ማንም እህል አይቀምስም ። ማሳረፍ እንጂ ማስጨነቅማ የሬሳ ዋነኛው ሥራ ነው ። ሌላውን ማወክ ፣ ማስለቀስ ፣ በሰው ውድቀት ባለቅኔ መሆን የሞት ባሕርይው ነው ። የሞተ ሰው ብዙ ሰው ቢሸከመውም አይነሣም ። ራሱን የገደለ አገርና ትውልድም የትኛውም እርዳታ ቆሞ እንዲሄድ አያደርገውም ። ምንድነው የቀረን ? ልብሱ የሰው ፣ ግብሩ የአራዊት አይደለም ወይ ? ፍትወት ያልሰለጠነበት ፣ ጭካኔ ጉዳይ አስፈጻሚ ያላደረገው ማን ነው ? በልቼ ልሙት የማይል ፣ ሆዱን ያሸነፈ እስቲ ይናገር ? ሁላችንም ሞተናል ። በፍቅር ተጋብተን በዘር ስንፋታ ፣ ሰማይን እያየን በምድር ስንራኮት ፣ የፖለቲካና የሃይማኖት ድንበሩ ሲጠፋን የቀረው ዝናሩ ብቻ ነው ። አዎ መተኮሻ የሌለበት ፣ ለፉከራ ግን የሚሆን ዝናር ብቻ ቀርቶናል ። አልሞትንም ብለን አንዋሽም ።
ፈሪሳውያን ግን ሐውልት የተሠራለትና የሚጎበኝ የመቃብር ሥፍራ ሁነው ነበር ። ይህኛው ያደገ ሟች ነው ። እርሱ ፈርሶ ቤቱ የታነፀ ፣ ውስጡ ሸትቶ ላዩ የተዋበ ፣ የራሱን ዓለም ሲቀጭ ኑሮ “ሩጫውን ጨርሻለሁ ፣ መልካሙንም የሃይማኖት ገደል ተጋድያለሁ” ብሎ ላዩ ላይ የሚያጽፍ ኩሩ ሟች ነው ። ስለ ቅናትና ስለ ምቀኝነት ሲጋደሉ ኑረው ስለ ሃይማኖት ነው የተፋጀነው የሚሉ ተናጋሪ ሙታን በዓለም እየበዙ ነው ። ሳይታደሱ ሃይማኖትን እናድሳለን  ብለን የተነሡ ፣ የኪራይ ተሳዳቢ ሁነው ቤተ ክርስቲያንን የሚያቃልሉ አያሌ ናቸው ። ሰው ጠፍቷል እያሉ የሚያለቅሱ ራሳቸው ግን እንደ አዳም በገነት የጠፉ ፣ በቤቱ የሸፈቱ ብዙ ናቸው ። አልሞትንም ብለን አንዋሽም ። ቃየንን ያልሰደበ ሰባኪ ማን ነው ? ቃየንስ አንድ ጊዜ የገደለ ነው ፣ እኛ ግን ደጋግመን ወንድሞቻችንን የገደልን ነን ። የቀረው ዝናሩ የቀረው ፉከራ ነው ። ይሁዳን ያልረገመ ማን አለ ? ይሁዳ ያልሆንን እነማን ነን ? እኛ ዝም ብለን እግዚአብሔር ቢናገር ለዘላለም ዝም እንል ነበርን ። ሰባራ በሰንጣራ ይስቃል እንዲሉ የራሳችንን አስቀምጠን በሰዎች የምንስቅ ፣ እንኳን እንደ እገሌ አላደረገኝ እያልን የግብዝ ስብሐት የምንቀርብ ሞኞች ነን ። ቀሚሱና ካባው ለሰው ነው ። አጥርና ቤቱም ለፍጡር ነው ። እርሱ ግን ሳያስፈቅደንና ሳይገልጠን ያየናል ። እርሱ ችሎን ነበር እኛ አልቻል አልን እንጂ ። አዎ ሞተናል ትንሣኤ ያስፈልገናል ። በቂም ፈራርሰናል ፣ በበቀል ተንኮታኩተናል ። የሸኘነው ጋሻ ወንድማችንን ፣ ያስረከብነውን ጦር ታሪካችንን ፣ ያስወረስነውን ጠመንጃ ደግነታችንን እንደገና ገንዘብ ማድረግ ይገባናል ። ከገጣሚው ጋር እንዲህ እንላለን፡-
ምንም ባንቀበር ባንገባ መሬት ፣
አያሳፍረንም ሞተናል ማለት ፤
በዙፋንህ ያለኸው ፣ በባሕርይ ምስጉን የሆንከው ፣ ዛሬም በዓይነ ምሕረት የምታየን ቸሩ ጌታ እናመሰግንሃለን ። መጠላለፍ አልደክም ፣ መገዳደል አልበቃ ፣ መሰዳደብ አልሰለች ያለንን ልጆችህን እባክህን ወደ እውቀትና አንተን ወደ መፍራት መልሰን ። አፍ ተከፍቶ ፣ ጆሮ የተደፈነበትን የእኛን ዓለም ይቅር በለው ። ስለበደልናቸውና ስለገፋናቸው ወገኖቻችን ይቅር በለን ። በረከታችንን ያነቀብንን ስህተት ሁሉ በመሐሪነትህ ደምስስልን ። የጉብኝትህ ቀን ይድረሰን ። እኔን ባሪያህንና ወገኖቼን ይቅር በለን ። ተራው ይድረሰንና በመባረክህ ባርከን ። በታላቁ ፍቅርህ ለዘላለሙ አሜን ።
የዕለቱ መና 28
ግንቦት 28 ቀን 2011 ዓ.ም.
ዲአመ
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ