ሰሞኑን ከወጡ ዘገባዎች አንዱ የጋቦንና የብሪታንያ ተመራማሪዎች ጉሬዛና ጦጣ የሚመገቡአቸውን ቅጠሎች በመለየት ለተለያዩ በሽታዎች መድኃኒት እያገኙ ነው። በሰውነት ውስጥ ያሉ ኬሚካሎችን ለማስወገድ ፣ መድኃኒቶችን በመላመድ የተነሣ የሚፈጠሩ ባክቴሪያዎችን ለማጥፋት ፣ ለተለያዩ የሆድ ሕመሞች፣ ከሁሉ የሚገርመው መፅነስ አለመቻልን ሊያስወግዱ የሚችሉ ቅጠሎችና መድኃኒቶችን ጉሬዛዎችና ጦጣዎች ያውቃሉ። ከጋቦን ገጠራማ ነዋሪዎች ጋር በመሆን እንስሳቱ የሚበሉትን ቅጠል በመከታተል የመለየት ሥራውን እየሠሩ ነው። የሰው ልጅ ብዙ ተመራምሮ ያልደረሰበትን ጉሬዛና ጦጣዎች ያለ ምርምር ደርሰውበታል። የሰው ልጅ ትሑት ሆኖ ከእንስሳትም መማር አለበት። ብዙ የመጠቅን ሲመስለን ገና መሆናችንን የሚነግሩን ብዙ ነገሮች አሉ። ተፈጥሮ ለመማሪያነት ለሰው ልጅ እንደ ተሰጠ በመጽሐፍ ተነግሮናል። እንኳን ከፍ ያለውን አምላክ ፣ ዝቅ ብሎም እንስሳትን ማክበር፣ መጠበቅ፣ ከእነርሱ መማር ያስፈልገዋል ።
አምላካችንን የሰውን ያህል እንኳ አላከበርነውም። ስደተኞች ዓለም አቀፍ ሕግና ተቋም ተዘጋጅቶላቸዋል። ስደተኛ ወላጆች ሕፃናትን ከያዙ ይበልጥ ተቀባይነትን ያገኛሉ። ሰዎች በተለያየ መንገድ ይሰደዳሉ። ነገሥታትም ክፉ ሲሆኑ ለብዙ ሰዎች አገር ጥሎ መንከራተት ምክንያት ይሆናሉ። የበረት ኑሮ በዛብህ ተብሎ የተሰደደው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ሰው ቅንዓት ከመጣበት የእኛ በረት ቤት ፣ ፓላስ ሆኖ ይታየዋል። እኛ በረት ይታየናል፣ ቀናተኛው ግን ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል መስሎ ይታየዋል። እስካሁን በበረት የተወለደ የቅርብ ሰው አናውቅም ። ቢወለድም የሚናገር ማንም የለም። ስለ እኛ ድሀ መሆኑ ያላሳፈረው ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታችን ግን በበረት ተወልዷል። የሁለት ዓመት ሕፃንን ያሳደደ ንጉሥ ላይኖር ይችላል። ጌታችን ግን ገና የሁለት ዓመት ሕፃን ሳለ ተሰደደ ። ምንም ሳንጀምር ፈተና ከበዛ ሰይጣን የአሁኑን ሳይሆን የወደፊቱን አይቶ እየተዋጋን ነው።
ስለ ወዳጃችን ደግነት በጣም ማውራት በእርሱ ላይ ጠላት ማብዛት ነ ው። ሰብአ ሰገል ሺህ ኪሎ ሜትሮችን በኮከብ ተመርተው 20 ኪሎ ሜትር ሲቀራቸው ለከተማው ሁሉ በመናገራቸው ለጌታችን ጠላት አመረቱበት። ቤተ ክህነቱና ቤተ መንግሥቱ ተባብረው እንዲያሳድዱት አደረገው። በስቅለቱም ቤተ ክህነቱና ቤተ መንግሥቱ ተባብረዋል። ነገሥታት ለመግደል መነሻ ሲፈልጉ ከቤተ ክህነቱ ይማከራሉ። ቤተ ክህነቱ በእጃችን መሳሪያ የለም፣ እኛ አንገድልም በሚል መመፃደቅ ለቤተ መንግሥቱ አሳልፈው ይሰጣሉ። ክርስቶስ በቤተ ልሔም እንደሚወለድ መጽሐፍ ጠቀሰው የተናገሩት ሊቃውንት የመወለዱን ምልክት ቢያዩም ልባቸው አልደነገጠም። ይወለዳል ብለው በማስተማር እንጀራ የሚበሉ እንጂ የመወለዱን ትርፍ የሚናፍቁ አልነበሩም። ለሄሮድስም ከተወለደ ቤተ ልሔም ነው የሚወለደው ሄደህ ግደለው በሚል ስሜት ነገሩት። ወሬ ለማየት እንኳ አልናፈቁም። ትልልቅ ከሀዲያን ያሉት በሃይማኖት ቤት ውስጥ ነው ።
የሩቆቹ ሰብአ ሰገል ያከበሩትን ክርስቶስ የቅርቦቹ አላከበሩትም። ክርስቶስ በዚህ ዓለም በሥጋ እንግድነት በመጣ ጊዜ የገጠመው ብቸኝነት መሳይ አልነበረውም። የክርስቶስ መከራ በወዳጆቹ ላይ ይወድቃልና እመቤታችንና ረዳትዋ ዮሴፍ ይህን ብቸኝነት ተጋፍጠዋል። ጉዳዩ ግራ የሚያጋባ ነው። ሰዎች አመናጭቀው በር ይዘጉባቸዋል፣ እንስሳት የተወለደው አምላክ መሆኑን አውቀው በእስትንፋሳቸው ያሞቁታል። የቅርቦቹ ገሸሽ አሏቸው፣ ሰብአ ሰገል ከምሥራቅ መጥተዋል። ፀጥ ባለው ሌሊት ፍጥረት አሸልቧል፣ መላእክት ምስጋና ያቀርባሉ። ለሥጋዊ አእምሮ የክርስቶስን ነገር መረዳት ከባድ ነ ው።
የሁለት ዓመት ሕፃንን የሚጣላው ክፉ በዓለም ላይ የለም። ከወላጅ ተለይቶ ብቻውን ቢያገኙት ሁሉም ሰዉ የማን ልጅ ነዉ? ብሎ ይይዘዋል፣ እንባውን ይጠርግለታል፣ ያበላዋል፤ ለፖሊስ ያሳውቃል። ሕፃን ዘርና ቋንቋ የሌለው የሰው ዘር ወዳጅ ነው። ክርስቶስ ግን በሕፃንነቱ ተሰደደ። ወደ ሰሜን ወደ ለመለም ሊባኖስ ሳይሆን ወደ ግብጽ ተሰደደ ። በተፀነሰባት በናዝሬት ቢወለድ ኖሮ ወደ ሊባኖስ ይሰደድ ነበር። ሰዓቱ አጣዳፊ ስለ ነበር ሄሮድስ ወደማይገምትባት ፣ አስጨናቂ በረሃ ወዳለባት ግብጽ ተሰደደ ። በስደቱ አፍሪካን ባረከ።
ለሰው የሚደረገው ለክርስቶስ አልተደረገም። የሰው ያህል እንኳ አላከበርነውም። በስደቱ ስደተኞችን ተቤዣቸው ፤ የተሰደደውን አዳም ወደ ገነት ሊመልስ ክርስቶስ ወደ ግብጽ ተሰደደ። እርሱ የስደተኞች ሰብሳቢ ነው። የስደተኞች አገራቸው ክርስቶስ ነ ው። በስደት አገር እንባ እንባ የሚላችሁ ከዘመድ እንጂ ከክርስቶስ አልራቃችሁም። ያለ ጊዜው ላለ መሞት መሰደድ ብልሃት እንጂ ፍርሃት አይደለም ። ነገሥታት ጥንትም ዛሬም ለብዙዎች መሰደድ ምክንያት ይሆናሉ። ሄሮድስ ከሃያ ዓመት በኋላ መንበሬን ይነጥቀኛል ብሎ ጌታን አሳደደ። በሕይወት የቆየው ግን ለሦስት ዓመት ብቻ ነው። ዓለም አጭር ናት። አሳዳጁም ይሞታል ።
ስደተኛ ስድስቱ ቃላተ ወንጌል የሚፈጸምበት ነው። የራበው ነው፣ የጠማው ነው ፣ የተራቆተ ነው፣ እንግዳ ነው፣ የሕሊና እስረኛ ፣ የመንፈስ ታማሚ ነው። ስደተኞችን ማሰብ የተፈናቀሉትን መርዳት የክርስቶስን ስደት መካፈል ነው።
ጌታችንን ይህች ዓለም የሰው ያህል እንኳ አላከበረችውም::
ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መስከረም 4 ቀን 2017 ዓ.ም.