የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሰፈር ምጣድ

የዲያቆን አሸናፊ መኮንን ገጽ ማክሰኞ ጳጉሜን 3/2007 ዓ.ም. ሰፈር ቤቶች ብቻ ሳይሆን ሰዎች ተጠጋግተው የሚኖሩበት፣ መተዋወቅና መናናቅ የበዛበት፣ ፍቅር ከመቼው ደፍርሶ ወደ ጠብ የሚቀየርበት፣ ወዲያው እንደ ገና ይቅር የሚባባሉበት፣ ሁሉም ነገር የጋራ የሆነበት፣ የአንዱን ልጅ አንዱ የሚያሳድግበት፣ መልሶ በልጅ የተነሣ ወላጆች የመረረ ጠብ ውስጥ የሚገቡበት፣ እነርሱ እየተሰዳደቡ ልጆቹ ተቃቅፈው የሚታዩበት፣ ብዙ መነካካት ያለበት እንደ ተላጠ የኤሌክትሪክ ሽቦ በየሰዓቱ መቀጣጠል ያለበት እንደገና ፍቅር የሚለኮስበት፣ አንዳንዴ ምርጫ የሆነ አንዳንዴ አማራጭ ያጣ የኑሮ ቅያስ ነው፡፡ ሰፈር ልቅሶውና ሠርጉ የጋራ በመሆኑ ማን ሀዘነተኛ ማን ሠርገኛ መሆኑ አይታወቅም፡፡ እየተወጋጉ መኖር ያለበት የሰፈር ኑሮ በክፉ ቀን ደግሞ ይላቀሳል፡፡ ሰፈሩ ሰፊ ቤት ሆኖ ሰው ቤቱን እንደሚሸከም ተሸካክሞ የሚኖርበት ተቋም፣ ተፈጥሮአዊ ግንኙነት ነው፡፡ ከዚህ ሰፈር ወጥተው የባለጠጋ መንደር የገቡ ሰዎች ቢጮኹ የሚደርስ፣ ቢጣሩ አቤት የሚል በማጣታቸው ከብቸኝነት ብርድ የሰፈሩን መወጋጋት ያለበት ሙቀት መርጠዋል፡፡ ታዲያ ሰፈር ብዙ ነገሮች የጋራ ናቸው፡፡ አንዱ በአንዱ መሶብ ያዛል፡፡ በጋራ ይበላል፡፡ በአንዱ ቤት ድግስ ሌላው እንግዳውን ይሸኛል፡፡ ፍጹም ቸርነት ያለበት፣ ካለ ፈጣሪ አሟጠሽ ጋግሪ የሚባልበት ነው፡፡ የጋራ ከሆኑ ነገሮች አንዱ የሰፈር ምጣድ ነው፡፡ ይህ ምጣድ ከዘመናት በኋላ ማን እንደ ገዛው አይታወቅም፡፡ ግን የተተወ ምጣድ ነው፡፡ የሰፈር ምጣድ እንደ ተዘዋዋሪ ችሎት በተለኮሰበት ይጣዳል፡፡ ይህ የሰፈር ምጣድ ሜዳ ላይ ጉልቻ ተጎልቶ እሳት ከተቀጣጠለ በኋላ ካለበት ሳብ ተደርጎ ይጣዳል፡፡ ከጠፋም ይረሳል፡፡ቢሰበርም ጠያቂ የለውም፡፡ ባለቤቱ አይታወቅምና፡፡ እሳት በተለኮሰበት የሚጣደው የሰፈር ምጣድ ከትክል ምጣድ ይለያል፡፡ ትክል ምጣድ ቋሚ ንብረት ነው፡፡ ባለቤት አለውና ማንም አይወስደውም፡፡ አድራሻ አለው፡፡ ዙሪያው ስለታጠረለት እሳት አያባክንም፡፡ ስለማይዟዟርም የመሰበር አደጋው አነስተኛ ነው፡፡ ቢሰበርም ከፍሎ የሚያስጠግነው ባለቤት አለው፡፡ ደበቅ ያለ በመሆኑ የሚታየው ፍሬው ወይም እንጀራው ነው፡፡ የሰፈር ምጣድ ግን በአደባባይ ተጋግሮበት በድብቅ ይበላል፡፡ በድብቅ የተጋገረበት ትክል ምጣድ ግን በግልጽ ያጠግባል፡፡ የሰፈር ምጣድ በተለኮሰበት ሁሉ የሚጣድ፣ የራሱ የሆነ አድራሻ የሌለው የጎዳና ንብረት ነው፡፡ እሳት የሚነድበት ታዋቂ ምጣድ ነው፡፡ ይህ ታዋቂነት ግን ባለቤት የለውም፡፡ ይህ በእረኝነት ሥር ያላደሩ፣ አዳዲስ አስተሳሰብ በመጣ ቁጥር የአዲስ ትምህርት፣ የአዲስ ቤተ ክርስቲያን አድማቂ የሆኑ ሰዎችን የሚያሳይ ነው፡፡ ዛሬ እንዲህ ያሉ አማንያን ዕለት ዕለት እየፈሉ ነው፡፡ አዲስ ቤተ ክርስቲያን ሲተከል የሚሞላው አረማውያን ተጠምቀው፣ ዓለማውያን ተመልሰው አይደለም፡፡ ከገንቦ ገንቦ የሚገላበጥ ሕዝብ ስለበዛ ነው፡፡ አዲሱ ቦታ የሞላው አሮጌው ቦታ ስለቀነሰ ነው፡፡ አሳሳች የሕዝብ ቆጠራን የሚያመጡ እነዚህ የሰፈር ምጣድ ናቸው፡፡ መሠረት ስለሌላቸው ሲዞሩ ይኖራሉ፡፡ ይልቁንም ከጊዜ በኋላ የመጣ የንባብ ልምድ፣ ሥርዓትን ያልተከተለ የእውቀት አሰሳ በየቀኑ የአቋም ለውጥን የሚያመጣ ጠባይን ይፈጥራልና መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ የዚህ መድኃኒቱ ቆም ብሎ መሠረትን በደንብ መመሥረት፣ በቃል ኪዳንም ከእግዚአብሔር ጋር መተሳሰር ነው፡፡ የሰፈር ምጣድ ተፈልጎ የሚገኝ ነው፡፡ ስለመጥፋቱም የሚቆጭለት ወገን የለም፡፡ እሳት ካልተቀጣጠለ ማንም አያስታውሰውም፡፡ ሁሉም ጋግሮበት አንድ ጥግ ላይ ይተወዋል፡፡ እንዲሁም ከርታታ ከዋክብት የሆኑ ምእመናን የአዲስ ትምህርት መሞከሪያ ሆነው እንደ ባዘኑ ይኖራሉ /ይሁዳ. ቁ. 12/፡፡ አህያ ክብር መስሏት ሁሉም ሥራውን ሲናገር “እኛ ያልፈሳንበት ዳገት የለም” አለች ይባላል፡፡ እነዚህ ሰዎች ሁሉም ተጠቅሞ ይጥላቸዋል፡፡ ለአሙቁልኝ እንጂ ለሕይወት አይፈለጉም፡፡ እንደ ላቦራቶሪ አይጥ የትምህርት መሞከሪያ ሆነው ይኖራሉ፡፡ ዝም ስለማይሉ የሰሙትን አዲስ ነገር ያስተላልፋሉ፣ እነርሱ ሲመለሱ የዘሩበት ሰው ግን አይመለስም፡፡ ስህተት ማስፋፊያ ይሆናሉ፡፡ ስሜት ስለሚነዳቸው ፍሬን ወይም ማብረጃ የላቸውም፡፡ መገለባበጥ ስለማይደክማቸው ሁሉም ያውቃቸዋል፡፡ መፍትሔው በግ ተብለናልና በእረኝነት ሥር ማደር፣ ተጠሪነት ያለውን ሕይወት መውደድ ነው፡፡ ዳግመኛም ክርስትና ራስን የማየት ኑሮ ነውና ከነቃፊነት መትረፍና ቀጥ ብሎ መንገድን መጓዝ ነው፡፡ መሠረት የአንድ ጊዜ ሥራ ሲሆን ሕንጻ ግን ቀጣይ መሆኑን ተገንዝበን አንድ ጊዜ መመሥረት ያስፈልጋል፡፡ እኛስ ትክል ምጣድ ነን ወይስ? እግዚአብሔር ያግዘን!

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ