የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የቀደመው ታሪኬ

“አስቀድሞ ተሳዳቢና አሳዳጅ አንገላችም ምንም ብሆን፥ ይህን አደረገልኝ፤ ነገር ግን ሳላውቅ ባለማመን ስላደረግሁት ምሕረትን አገኘሁ” /ጢሞ. 1፡13 ።/
የእግዚአብሔር ሰዎች ስላለፈው የውድቀት ታሪካቸው መናገር አያሳፍራቸውም ። ምክንያቱም በእግዚአብሔር ምሕረት አግኝቷልና ። ስለ ቀደመው ሕይወታቸው የሚያወሩት ናፍቆአቸው ፣ ኮርተውበት አሊያም ተሳቅቀው ሳይሆን የእግዚአብሔርን ፍቅር ለዓለም ለመዘከር ነው ። እግዚአብሔር ጻድቃን ቢላቸውም እነርሱ ግን ራሳቸውን ኃጢአተኛ ብለው ይጠሩት ነበር ። የእግዚአብሔር ከፍታ በታያቸው ቊጥር ራሳቸው ያንስባቸው ነበር ። ለሕይወት ሁለት ዓይነት ገጽ ወይም መልክ የሚሰጥ እግዚአብሔር ብቻ ነው ። ቀድሞ ሙት ነበርሁ ለማለት ሕይወትን ማግኘት ያስፈልጋል ። ጨለማ በታሪክ መልክ የሚወራው ብርሃን ሲገኝ ብቻ ነው ። የጠዋቱ ብርሃን የእኛ እጅ የሌለበት የእግዚአብሔር የፍቅር ስጦታ ነው ። የሕይወት ብርሃንም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው ። የተሰረዘ ታሪክ ቢሆንም ሐዋርያው ግን ያለፈውን ዘመን ውድቀቱን እያነሣ የእግዚአብሔርን ምሕረት ያውጅበታል ። እኔ የጀመርሁት ከዚህ ሳይሆን እኔ የጀመርሁት ከዚያ ነው ይላል ። ብዙ ሰው እንዳለ ያለ አድርጎ ራሱን ለመግለጥ ይፈልጋል ። ቀድሞም ቢሆን እንደ ዛሬው አማኒ ፣ እንደ ዛሬው ጤነኛ ፣ እንደ ዛሬው አገልጋይ ፣ እንደ ዛሬው ባለጠጋ እንደሆነ ለመናገር ይዳዳዋል ። “የትላንት ታሪክ የሌለው ጻድቅ ግን የለም ።” የእግዚአብሔር አዳኝነት ያስፈለገውም የሰው ውድቀት ስላለ ነው ።

የእግዚአብሔር ሰዎች የማይፈሩት ሁለተኛው ነገር የሚባሉትን ለመስማት ነው ። የሚባሉት ላይ አይዘገዩም እንጂ ለመስማት ደፋር ናቸው ። ስማቸውን ጥለው በክርስቶስ ክርስቲያን ተብለዋል ። ስለዚህ ስለ ስማቸው አይጨነቁም ። ዓለም ሳይጥለው ቀድመው ጥለውታል ። በምርጫቸው አያጨማልቁት እንጂ ሰዎች በጥላቻ ጥላሸት ቢቀቡአቸው አይጨነቁም ። ሰዎች የሚሏቸውን ክርስቶስ ስለማይላቸው በዚህ ደስተኞች ናቸው ። የሰዎች ስም መስጠት የመጨረሻው ብያኔ አይደለም ። ደግሞም ውሉደ እግዚአብሔር ተብለዋልና የእገሌ ልጅ ተብለው የሚጠሩበት ስም ባይኖራቸው አይጨነቁም ። ትልቁም ትንሹም ማጠቃለያው መቃብር ነው ። የእግዚአብሔር ልጅ መሆን ግን የማያልፈውን ዓለም መውረስ ነው ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፊልጶስ ቂሣሪያ፡- ሰዎች የሰውን ልጅ ማን እንደ ሆነ ይሉታል ? ብሎ ጠየቀ ።”/ማቴ. 16 ፡ 13 ።/ ሰዎች የሚሉንን ለመስማት ድፍረት እንዲኖረን እያስተማረን ነው ። ሰዎች ክርስቶስን የሚሉት እንኳ አላጡም ። የሆነውን ሳይሆን ያልሆነውን ተናገሩ ። ክርስቶስ ማን እንደሆነ የነበራቸው እውቀት ሳይሆን ግምት ነበር ። ግምታቸውን ግን እንደ እውቀት በድፍረት ይናገሩት ነበር ። ሰዎች የሚሰጡት ክፉ ስያሜ ብቻ ሳይሆን መልካም ስያሜም ትክክል አይደለም ። ይኸውም ጌታችንን፡- አንዳንዱ መጥምቁ ዮሐንስ ፥ ሌሎችም ኤልያስ ፥ ሌሎችም ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው” ይሉት ነበር ። እርሱ ግን ወልደ አብ ፣ ወልደ ማርያም ነበረ ። ሰዎች ክፉ ሲናገሩብንም ሆነ መልካም ሲናገሩልን ሁለቱንም በማስተዋል ተቀብለን ማዘንም ሆነ መዝለል የለብንም ። እኛ የሆነውን ብቻ ነን ። መልካም ብንሆን ለእግዚአብሔር ደስታ ነው ፤ ክፉ ብንሆንም የሚያድነን እርሱ ነው ።
ሐዋርያው፡- “አስቀድሞ”በማለት ይናገራል ። አስቀድሞ ክፉ ታሪክ ነበረው ። ትላንቱ የሚያጸጽት ገጽታ ነበረው ። እርሱ አስቀድሞ ተሳዳቢና አሳዳጅ አንገላች ነበረ ። ክፉ ነገርን በነበር ለመተረክ በቅቷል ። አስቀድሞ ነበረ ፣ ዛሬ ግን አይደለም ። የጻፍነው እኛ ብንሆን በአሁን ሰዓት ተሳዳቢና አሳዳጅ አንገላችም ነኝ እንል ነበር ። ክፋት ታሪክ ሳይሆን ሕያው ሁኖብናልና ። ሐዋርያው ጳውሎስ ተሳዳቢ ነበርሁ እያለ ነው ። ሥጋዊ ቅንዓት ይዘን ለሃይማኖት ዘብ ስንቆም የመጀመሪያው መሣሪያችን ስድብ ነው ። ስድብ የምንጠላውን ሁሉ ማጠልሸት ነው ። ስድብ ሕግ የለውምና የተገኘውን ጭቃ መለጠፍ ነው ። ስድብ ከሐሜት ልዩ የሚያደርገው ሐሜት ሰውዬው በሌለበት ፈርቶ ክፉ መናገር ሲሆን ስድብ ግን ሰውዬው ባለበት ደፍሮ ክፉ መናገር ነው ። ስድብ ለእጅና ለእግር የሚወረወር ሳይሆን ስድብ ለኅሊና የሚወረወር ቀስት ነው ። የታሰረ ኅሊና የተፈቱ እግሮች ቢኖሩትም መራመድ አይችልም ። ስድብ ሰውዬውን በሆነውና ባልሆነው ነገር ማዋረድና ተስፋ የለሽ ማድረግ ነው ። ስድብ የሰይጣን ዋነኛ መሣሪያው ነው ። ስድብ በሰብእና ላይ የሚወረወር ጦር ነው ። ስድብ ከአንደበት ኃጢአቶች ዋነኛው ነው ። ስድብም ሰውየው መቆም እንዳይችል የማሽመድመድ ዘዴ ነው ። ሐዋርያው እንዲህ ነበርሁ እያለ ነው ። የሚሳደበው ደግሞ ወንጌልንና ወንጌላውያንን በመሆኑ ትልቅ ውድቀት ውስጥ ነበር ።
አሳዳጅ ነበርሁ ይላል ። ማሳደድ ሁለት ዓይነት ነው ። የመጀመሪያው ከሰፈሩ ፣ ከቀዬው ፣ ከቤቱና ከቤተሰቡ ተለይቶ እንዲባረር ፣ በኃይል እንዲወጣ ማድረግ ነው ። ሁለተኛው በሐሜትና በውግዘት ከሰው ኅሊና እንዲወጣ ማድረግ ነው ። ቢናገር እንደ እብድ እንዲቆጠር ፣ ቢያስተምር እንደ መናፍቅ እንዲታይ ማድረግ ነው ። ሐዋርያው በሁለቱም ስልት ሳይንቀሳቀስ አልቀረም ።
አንገላችም ነበርሁ ይላል ። ከሮማው ፍርድ ቤት የመግደል ፣ ከአይሁድ ሸንጎ የማግለል ሥልጣን አግኝቶ በአገር ውስጥና በውጭ አገር የነበሩትን ክርስቲያኖች ያሳድድና ያንገላታ ነበር ። ማሳደድ ማባረር ሲሆን ፣ ማንገላታት ግን በወኅኒ እንዲጣሉ ፣ እንዲገረፉና እንዲወገሩ ማድረግ ነው ። ሐዋርያው እጅግ የጠላው ክርስትና እጅግ ወረሰው ። ክርስትና ጠላትን ወዳጅ የማድረግ ፣ አሳዳጁን ተሰዳጅ የማድረግ ብቃት አላት ። ሰዎች በጣም ሲቃወሙ በጣም ሊድኑ ተቃርበዋል ። መፍራት ልዝቦቹን ነው ። የከረረ መበጠሱ አይቀርም ። 
ሐዋርያው፡- “አስቀድሞ ተሳዳቢና አሳዳጅ አንገላችም ምንም ብሆን፥ ይህን አደረገልኝ፤ ነገር ግን ሳላውቅ ባለማመን ስላደረግሁት ምሕረትን አገኘሁ” ይላል ። ሳላውቅ ፣ ባለማመን ስላደረግሁት ይላል ። ሐዋርያው የአይሁድ ሃይማኖት መምህር ነበረ ። ብዙ ዘመኑንም በመማር ያሳለፈ ፣ ስመ ጥሩ ከሆነው ከገማልያል እግር ሥር ተቀምጦ የተማረ ፣ በአይሁድ ሸንጎም አባል የሆነ ፣ የተከበረ ሰው ነበር ። ነገር ግን ባለ ማወቅ ስላደረግሁት አለ ። ጌታችንም የሰቀሉትን እነዚያን የሃይማኖት ምሁራን፡- “አባት ሆይ፣ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” አለ ። እኛ ይቅር ለማለት የምንቸገረው የሚያደርጉትን ያውቃሉ ብለን ነው ። መጻሕፍትን ቢያውቁም የሚያደርጉትን አያውቁም ። ሐዋርያው ባለማመን ስላደረግሁት ይላል ። ሐዋርያው ክርስትናን ያሳድድ የነበረው ለኦሪት እምነቱ ቀንቶ ነው ። አሁን ግን አላምንም ነበር እያለ ነው ። አላውቅም ፣ አላምንም ነበር ማለት ትልቅ ትሕትና የሚጠይቅ ነው ። ማንም ሰው ከዜሮ መጀመር አይፈልግም ። ባለው ላይ መደመር ይፈልጋል ። ሐዋርያው ግን በእግዚአብሔር ምሕረት ስለተከለለ ይህን አለ ። እግዚአብሔር ይቅር ካለን የሚቀርብን ጸጋ የለም ።
ምሕረት አገኘሁ ይላል ። በብዙ አገሮች ይቅርታና ምሕረት በመንግሥት ደረጃ ይሰጣል ። ፍርዱ በሕግ ስለሆነ ምሕረትና ይቅርታም በሕግ መሆን አለበት ። ሕጋዊ ያልሆነ ምሕረት ሕጋዊውን ፍርድ መሻር አይችልም ። ይቅርታ የሚባለው በአብዛኛው ተሳስተናልና ቅጣት ይቅለልልን የሚሉ እስረኞች የሚቀበሉት መፈታት ነው ። ምሕረት ግን መንግሥት ራሱ የቅጣት ዘመናቸውን አስቦ የሚለቃቸው እስረኞች የሚያገኙት  ነጻነት ነው ።አሊያም ይቅርታ የእስረኛው ጥያቄ ሲሆን ምሕረት የመንግሥት ምላሽ ይሆናል ። ሐዋርያው ምሕረት አገኘሁ ሲል እኔ ስገፋው እግዚአብሔር ግን አብዝቶ ቀረበኝ ፣ ሞት ሲገባኝ ሕይወትን ፣ እስር ሲገባኝ አገልግሎትን ሰጠኝ እያለ ነው ። ሐዋርያው የእግዚአብሔር ምሕረት መንገድ ዘግቶ ባይመልሰው ፣ እጆቹ በደማስቆ ክርስቲያኖች ደም ይጨቀዩ ነበር ። ትልቁን ክፋቱን ሳይጨርሰው እግዚአብሔር አቋረጠው ። እኛም ወደ እግዚአብሔር የተመለስነው ይበልጥ እግዚአብሔርን ለማሳዘን በተነሣንበት ጊዜ ይሆናል ። የክፋት መንገዳችንን ሳንጨርሰው ገንዘቡ ያደረገን እንዴት ቡሩክ ነው !
ሐዋርያው የሕግ አስተማሪ ሊሆኑ ለሚሹት ሰዎች እኔ ተሳዳቢና አሳዳጅ ፣ አንገላችም ሳለሁ ሐዋርያ የሆንሁት በቸርነቱ ነው እያላቸው ነው ። በምሕረት ገብተው በሕግ ለመኖር ለሚያስቡ ፣ ለሚመጻደቁ ፣ ሌሎችንም ለሚንቁ ፣ የትላንቱን ለረሱት እያስታወሰ ነው ። እግዚአብሔር ቀጣዩ መንገድ እንዳይጠፋን የመጣንበትን መንገድ ያስታውሰናል ።
በእውነት ጌታዬ ሆይ ማደሪያህ ይባረክ !
1ጢሞቴዎስ /15/
ኅዳር 20 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲ.አ.መ.
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ