የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የበረሃ ምንጭ

 

ወዳጄ ሆይ !

በቀጥታ መስማት ያለብህን ከሦስተኛ ወገን አትስማ ። ከሦስተኛ ወገን ስትሰማ ቀዝቅዞ ሊያሰንፍህ ፣ ግሎ ሊያስጨንቅህ ይችላል ። በመጠኑ የምትሰማው ጉዳይህ ፊት ራስህ ስትቆም ብቻ ነው ። የሦስተኛ ወገን ጠባይ ብዙ ዓይነት ነው ። አገላለጽ ባለማወቅ የሚያድበሰብስ ፣ የቃላት ድህነት ኖሮበት መርዶ አርጂ የሚመስል ፣ ነፋስ ሊወልድ ብዙ ሰዓት የሚያምጥ ፣ ነገርን አቃልሎ ዋጋ የሚያስከፍል ፣ አጋንኖ በእሳት ላይ ቤንዚን የሚያርከፈክፍ አለ ። ዝምታን የመረጠን ሰው ተናገር ብለህ በጣም አትጎትጉት ። “የእንጦጦ መምህር ቢናገር ባመት ፣ ያውም እሬት” እንዲሉ ንግግር ባለማወቅ የሚያስቀይምህ ሊሆን ይችላል ። 

ወዳጄ ሆይ !

የጥንት እውቀት በመደበቅ ፣ የዛሬ እውቀት ግን በመስጠት ይከብራል ። በዚህ ዘመን እውቀትን ብትደብቅ አላዋቂ ትሆናለህ ። የእውቀት ስስት የጠፋበት ዘመን በመሆኑ ልናደንቅ ይገባናል ። የምትወደው ሰው ጋር ለመኖር በዝግ ልብ ሁነህ አትቅረበው ። ብዙ አለመጠበቅ ፣ ይቅር ማለትና ማለፍ እንዲሁም ጠባዩንና የአስተዳደግ ተጽእኖውን መረዳት ይገባሃል ። የምትወዳቸው አንተን የማወቅ መብታቸውን ከከለከልካቸው ይጠሉሃል ። በዝግ በር እንደማይገባ ዝግ በሆነ ልብም ወዳጅ አይስተናገድም ። 

ወዳጄ ሆይ !

ዛሬ ያበሳጨህን ነገር በትዕግሥት አሳድረው ። ከቻልህ አሠልሰው ። በልኩ ማየት ትጀምራለህ ። ፈጥነህ መልስ መስጠት ጸጸትን ፣ ተስፋ መስጠትም ቁጭትን ያመጣል ። እንደ ሄሮድስ ከእውነት ስሜትህን ካስቀደምህ ፣ ይደርን ከጠላህ የቅዱሳንን አንገት የምትቀላ ትሆናለህ ። ፈጣን ፍርድ በሚሰጥባቸው አገራት የተፈረደባቸው በሞቱ በማግሥቱ ንጹሕ ነበሩ ይባላል ። 

ወዳጄ ሆይ !

ተፈሪ ሰው ለመሆን አትሻ ። የግርማ ሞገስ ድግምትም አትፈልግ ። ግርማ ሆኖ የሚጋርድ ፣ ሞገስ ሆኖ የሚያስወድድ እግዚአብሔር ብቻ ነው ። የምወደደው በምሰጠው ስጦታ ነው ብለህ ገንዘብህን አትጨርስ ። ፍቅርን እንደ ቻልህ ጠብንም ቻል ። ነገር ከፈራህ እያስፈራሩ ይበዘብዙሃል ። አፈኞችን ሳይሆን ቅዱሳንን አክብር ። የራቁትን በማሰብ ውስጥ ከሆንህ በፊት የቆሙትን ማየት ያቅትሃል ። ለተወለዱት እንጂ ለሞቱት ምንም ማድረግ አትችልምና በሥጋ ከሞቱት ጋር በስሜት አትሙት ። የሞተ ወዳጅህን መርዳት ከፈለግህ ቤተሰቡን ጠይቅለት ። መንፈሱ እንዳያዝንብህ የተከለውን አትንቀል ። የሚያይ አምላክ አለውና አያየኝም ብለህ አደራውን አትካድ ።

ወዳጄ ሆይ !

ሩኅሩኅነት ልፍስፍስ ፣ ጠንካራነት ጨካኝ ፣ ቸልተኛነት ዳተኛ አያድርግህ ። መምሰልን የመሆን ምትክ አታድርገው ። እርቦህ እንደ ሰረቅኸው ጠግበህም አትስረቅ ። በአፍህ ያለውን ሳትውጥ ለሌላ ጉርሻ አትጨነቅ ። እንዳለ ያለ እግዚአብሔር ብቻ ነውና በሚለዋወጠው ሥርዓት አትደነቅ ። የከፈለ የከፈለውን ነገር ካልወሰደ ያስጨንቅሃል ፤ ዋጋ ከፍሎ ለገዛህ ጌታ ካልሆንህ ልታስብ ይገባል ። 

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ጥቅምት 20 ቀን 2013 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ