የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የበዛ እውቀት

“ጸጋውንም በጥበብና በአእምሮ ሁሉ አበዛልን ።”

ክርስቲያናዊ ሕይወት ከእውቀት ጋር የተሳሰረ ነው ። በእውቀት አይዳንም ፣ ያለ እውቀትም አይዳንም ። ከነገረ ድኅነት ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው ቅዱስ ቍርባን የሚወስደው ሰው የክርስቶስን ሞትና ትንሣኤ መናገር አለበት ። አሊያ ዕዳ ይሆንበታል ። “ይህን እንጀራ በበላችሁ ጊዜ ሁሉ፥ ይህንም ጽዋ በጠጣችሁ ጊዜ ሁሉ ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁና” ይላል ። 1ቆሮ. 11፡20 ። ክርስትና በማወቅ የሚጀመር ጉዞ ሲሆን ታውቆ የማይፈጸመውን ነገረ እግዚአብሔር ሲረዱ መኖር ነው ። የክርስቲያናዊ እውቀት መሠረቱ አስተርእዮ ወይም አምላካዊ መገለጥ ነው ። እግዚአብሔር ራሱን በፍጥረት ፣ በተአምራት ፣ በመጻሕፍት ፣ በነቢያት ገልጧል። እግዚአብሔር መታወቅ የሚፈልግ አምላክ ነው ። እግዚአብሔር መታወቅ የሚፈልግ አምላክ ስለሆነ በፍጥረት ላይ የኃያልነቱና የጥበበኛነቱ አሻራ ጎልቶ ይነበባል ። ዓይንን ግንባር ላይ ማድረጉ እግር ላይ አለመሰካቱ ጥበበኛነቱ ነው ። ሁሉንም በቦታና በዘመኑ ማስቀመጡ የጥበቡ መገለጫ ነው ። ግዙፉ ሰማይ ፣ በመለኪያ የማይታወቀው ባሕር ፣ ከሚዛን በላይ የሆኑ ተራሮች የኃያልነቱ አስረጂ ናቸው ። ፍጥረት በዘፈቀደ እንዳልመጣና ወደ ታላቅ ግብ እየተጓዘ እንደሆነ የሚካድ አይደለም ። ሁሉንም በመልክ በመልክ ያስቀመጠ ጉዞውን ያስጀመረና እስካሁንም እየመራ ያለው እግዚአብሔር ነው ። ዓለም እንዲህ ሰክራ እንኳ ያልወደቀችው የእግዚአብሔር እጅ ከለላ ስለሆነላት ነው ።

የዚህችን አገር መሪ ስሙን ለመጥራት ባንወድ እንኳ ገዥነቱን ልባችን ይቀበለዋል ። እንዲሁም አንድ ኃይል አለ የሚሉ እግዚአብሔር ብለው ግን ለመጥራት የማይፈልጉ ቢኖሩም እግዚአብሔር ግን ይገዛቸዋል ። እርሱ ሳይሰጋ ይኖራል ። እርሱ ለፍጥረቱ እውቅና ይሰጣል እንጂ ፍጥረቱ ለእርሱ እውቅና አይሰጠውም ። ለአባቱ እውቅና የሰጠ ልጅ ፣ ሠሪውን የቀደመ ሸክላ የለም ። ያልካደንን እግዚአብሔር መካድ በእውነት ነውር ነው ።

አምልኮት ሙሉ የሚሆነው በእምነትና በመንፈሳዊ ዓይን በማየት ብቻ ሳይሆን በእውቀትም ነው ። እግዚአብሔር በስሙ የሚለመን አምላክ ነውና ስሙን ካላወቅን መለመን አንችልም ። ሰው በአእምሮውና በመንፈስ ቅዱስ መጸለይ አለበት ። አሊያ አምልኮቱ ሙሉ አይሆንም ። አምልኮ አብሾ እንደ ጠጣ ለፋፍ ፣ እንደ ሰከረ ጥጋበኛ ፣ አቅሉን እንደ ሳተ ሰው መዘላበድና መጮኽ ያለበት ሳይሆን በአእምሮና በመንፈስ የሚከናወን ነው ። ሰው አሜን ብሎ የሚለምነውን ነገር አውቆ ካልተባበረ አሜን ባለማለቱ መልሱ ይቀራል ። በረከቱ ይዘገያል ። አእምሮ ማለት እውቀት ማለት ነው ።

እውቀት ብቻውን ወደ ክርስቶስ ባያቀርብም ያለ እውቀት ወደ እምነት መምጣት አይቻልም ። ጻፎችን ፈሪሳውያም ክርስቶስ የት እንደሚወለድ በቂ እውቀት ነበራቸው ። ተወለደ ሲባል ግን ልባቸው አልደነገጠም ። ለሄሮድስም የነገሩት እንዲሰግድለት ሳይሆን እንዲገድለው ነው ። /ማቴ. 2፡5/ እውቀት ብቻና ያለ እውቀት መሆን ሁለቱም አደጋ አለው ። ከሁሉ የከፋው ግን ሳያውቁ የሚያውቁ የሚመስላቸው ፣ በተቦጨቀ ጥቅስ ዶግማ ሲቀርጹ የሚውሉ ፣ ስተው የሚያስቱ ሰዎች ናቸው ።

ነገረ ድኅነት እውቀትን አብዝቷል ። ስለ ቅድስት ሥላሴ ያወቅነው ፣ ነገረ ሥጋዌን በልካችን የመረመርነው በዳነ አእምሮ ነው ። አልማርም የሚል ሰው ለቤተ ክርስቲያን አደጋ ነው ። የበዛልን እውቀትም ምሥጢረ ሥላሴና ምሥጢረ ሥጋዌ ነው ። ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን መሠረታቸው ነገረ ሥጋዌ ፣ የሥጋዌ መሠረትም ምሥጢረ ሥላሴ ነው ። በማይናወጥ መሠረት ላይ ለመቆምና ለሌሎችም የመዳን ምክንያት ለመሆን ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን የምታስተምረውን ነገረ ሃይማኖት ጠንቅቆ ማወቅ ያስፈልጋል ።

እውቀት ያሳስታል የሚሉ ሰነፎች ሲሆኑ መዳን በእውቀት ነው የሚሉም ግኖስቲካውያን ሁለቱም በቤተ ክርስቲያን የተወገዙ ናቸው ። “እኔ እንደሚመስለኝ ፣ ለእኔ እንደ በራልኝ” እያሉ መጽሐፍ ቅዱስን የሚተረጉሙ ወጣቶች ኢትዮጵያውያን ናቸውና እንደ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ፡- “የሚመራኝ ሳይኖር ይህ እንዴት ይቻለኛል?” ማለት ይገባቸዋል ። የሐዋ. 8፡31። ይህን ጥያቄ የተቀበለው ወንጌላዊው ፊልጶስ ተርጓሚ አያሻም እንዳሻህ ተርጉመው አላለውም ፣ ተረጎመለት እንጂ ። ከዚያም አምናለሁ ብሎ ለመጠመቅ አስቀድሞ አሳብ አቀረበ ። እስከ ምሥጢረ ጥምቀት ድረስ ባይማር ኖሮ ልጠመቅ ብሎ አይጠይቅም ነበር ። መማር ማወቅ ለዳኑ ሕዝቦች የተሰጠ ትልቅ በረከት ነው ። እውቀትን ከሚጠላ መንፈስ አድነን ።

የኤፌሶን መልእክት ትርጓሜ /17

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
የካቲት 30 ቀን 2014 ዓ.ም.

ያጋሩ