የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የቤተ ልሔሙ ሕፃን

ሰብአ ሰገል ሀብታቸው ድንጋይ ሁኖባቸው የፈለጉህ ፣ የጥበብ ሰዎች እውቀታቸው ኀዘን ሁኖባቸው ያሰሱህ ፣ እንደ ዛሬው የተባበሩት መንግሥታት ሳይመሠረት የምሥራቅ ነገሥታት ተባብረው ወዴት ነው ? ያሉህ የቤተ ልሔሙ ኢየሱስ ሰላም እልሃለሁ ። ሀብት ካላሳረፈ እውነተኛው ሀብት አንተ ነህ ። ጥበብ ብስጭት ከሆነ እውነተኛው ተድላ አንተ ነህ ። ንግሥና ጭስ አልባ ቃጠሎ ከሆነ እውነተኛው ክብር አንተ ነህ ። በአገራቸው ተገኝተህ የጠራሃቸው ፣ በቤተ ልሔም የተቀበልሃቸው ፣ በልባቸው ናፍቆት ፣ በዓይናቸው ጥጋብ የሆንህ አንተ አማኑኤል ነህ ። የምድር ኃያላን የሚፈልጉህ በበረት የወደቅህ ፣ የምድር ጠቢባን የሚከጅሉህ በእናትህ እቅፍ ሁነህ ጡት የምትለምን ፤ አንተ የዘላለሙ አባት ፣ አንተ የቤተ ልሔሙ ሕፃን ፤ አንተ የአብ ልጅ ፣ አንተ የድንግል ልጅ ባለ መለየት አምላክም ሰውም ለሁንከው ሰላም እላለሁ !

የሆነውን ነገር ማንም ሊናገረው አይችልም ። እንደ ቅድስት እናትህ በአርምሞ ከመግለጥ ውጭ ምንም አይባልም ። ልጅ በመውለድዋ እናት እንጂ ቅድስት የተባለች ሴት የለችም ። ቅድስት እናትህ ግን በመውለድም እንደገና ቅድስት ተባለች ። ሰማይ ሰማይ ነበረ ፣ ሰማይ ምድር ሆነ ፤ ይህችውም እናትህ ናት ። ከዳግሚት ሰማይ ከድንግል የወጣኸው ፀሐይ አንተ ነህ ። ድሀ አይወድም እንዳይሉህ እረኞችን ጠራህ ፣ ባለጠጋ አይሻም እንዳይሉህ ሰብአ ሰገልን ጋበዝህ ። አንተ የሁሉ ወዳጅ ነህ ። ቦታ ሳይገድብህ ለሁሉ ትደርሳለህ ። ልደትህም የሁሉ የምሥራች ነው ።

ያቀረቡልህን እጅ መንሻ ተቀበልህ ። የሰጡህ ወርቅ ብቻ ሳይሆን የሰጡበት እጅም ያንተ ነው ። ያንተን ያንተ ከሆነው እጅ የተቀበልህ ፣ የሕፃንነት ዓይንህ እየተንከራተተ ፣ በመንበርህ ሁነህ ደግሞ ግብራቸውን ትቀበል ነበር ። አንተ ስትወለድ ሰማያውያንና ምድራውያን ጉባዔ አደረጉ ፣ ይህም የመንግሥተ ሰማያትን ዘመን ያስታውሳል ። አንተ ስትወለድ ኑሮ ያራራቃቸው ነገሥታትና እረኞች አብረው ሰገዱ ፣ ይህም የቤተ ክርስቲያን መገለጫ ነው ። መንግሥተ ሰማያትንና ቤተ ክርስቲያንን ላየንበት ልደትህ ሰላም እንላለን ።

ባለ መደነቅ ከመዘመር ፣ በመደነቅ ዝም ማለት ይሻላል ። የተደነቀም ዝም ማለት አይችልም ። ለእኔም በልደትህ ምሥጢር መደነቅን ስጠኝ ። አሜን ።

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥር 1 ቀን 2014 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ