የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የቤተ ክርስቲያን ታሪክ /ክፍል 14/

ኔሮን ቄሣር /54-68 ዓ.ም./
   ክርስቲያኖች በመጀመሪያ ጊዜ በሮማውያን ዘንድ የአይሁድ እምነት ተከታዮች ተደርገው ይታዩ ነበር ። ለዚህም ብሉይ ኪዳንን መቀበላቸውና መጠቀማቸው ሲሆን የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች አይሁዳውያን መሆናቸውም ይህን ግምት እንዲወሰድ አድርጓል ። ክርስቲያኖች ጠላትነትን ያተረፉት፡-
1-  ከአይሁዳውያን፡- አይሁዳውያን ክርስቶስን ሰቅለው ከገደሉ በኋላ የእርሱን ተከታዮች በማሳደድ ሥራ ተጠምደው ነበር ። ሕጋችንን ፣ ትውፊታችንን ይቃወማሉ ፣ አሕዛብንም ወደ እስራኤል ርስት ያስገባሉ ብለው ስላሰቡአቸው እንደ ጠላት ያዩአቸው ነበር ።
   2-  ከአሕዛብ፡- አሕዛብ በብዙ አማልክት የሚያመልኩ በመሆናቸው የአንዱን አምላክ አስተምህሮ መቀበል ከብዶአቸው ነበር ። የተለያዩ ተፈጥሮአዊ ችግሮች ማለትም ረሀብ ፣ ቸነፈር ሲነሣ የአማልክት መቆጣት እንደሆነ በማሰብ በክርስቲያኖች ላይ ጥላቻ አሳድረው ነበር ። ጣዖታት በመሸጥ የሚተዳደሩ ሰዎችም የዚህ ተቃውሞ መሪ ነበሩ ። ክርስቲያኖች ከአይሁድ ጋር የሚያደርጉት ክርክር ምክንያታዊ ወይም ባለ መጽሐፍ ነበረ ፤ ከአሕዛብ ጋር የሚያደርጉት ክርክር ግን መጽሐፍ አልባ ስለነበር በጣም አስቸጋሪ ነው
    3-  ሮማውያን፡- የሮም ቄሣሮች የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ቄሣር ጌታና አምላክ ነው የሚለውን ተቃውመው ኢየሱስ ጌታ ነው በማለታቸውና ለቄሣርም ምስል አንሰግድም በማለታቸው ይጠሉአቸው ነበር ። መሳፍንትና መኳንንቱም ሁሉ በክርስቶስ እኩል ነው የሚለው ትምህርት ፣ ባሪያና ጌታን አንድ ያደረገ ነው በማለት ክርስትናን ለመቃወም ምክንያት ሆኗቸዋል ። አይሁዳውያን የጀመሩትን ክርስቲያኖችን የማሰደድ ተግባር የቀጠሉበት  ሮማውያን ናቸው ፤ ለዚህ ቀዳሚው ኔሮን ቄሣር ነበር ።

ክርስቲያኖች የተለያዩ ክሶች ይሰነዘሩባቸው ነበር ። እህትና ወንድም በመባባል እርስ በርሳቸው ይጠራሩ ስለነበር በዘመድ መካከል የሚፈጸም ጋብቻን ያበረታታሉ ተብሎ ይታሰብ ነበር ። ቅዱስ ቊርባን የጌታ ሥጋና ደም ነው ብለው ስለሚናገሩም የሰው ሥጋ በላተኞች ናቸው ተብለው እንደ ጭራቅ ይፈሩ ነበር ። በክርስቲያኖች ላይ ይደርስ የነበረው መከራም ለማሰብ እንኳ የሚከብድ ነበር ። ከቄሣሮች በክርስቲያኖች ላይ ስደት በማስነሣት የመጀመሪያው የሆነው ኔሮን ቄሣር /54-68 ዓ.ም/ ነው ። ኔሮን ቄሣር ከ54 እስከ 64 ዓ.ም በክርስቲያኖች ላይ ምንም ጥላቻ አልነበረውም ። በ64 ዓ.ም የሮማ ከተማ ሁለት ሦስተኛው ወይም የሚበዛው ክፍል መቃጠል ግን ክርስቲያች ላይ እንዲዘምት አድርጎታል ። የሮም ከተማ መቃጠል ምክንያት ራሱ ኔሮን ቄሣር ነው ።
1-  ቤተ መንግሥቱን አስፋፍቶ መሥራት ስለሚፈልግ የሮምን ከተማ አቃጥሏታል ።
    2-  የሮም ከተማ ስትቃጠል ምን ትመስላለች የሚለውን ለማየት የሮምን ከተማ አቃጥሏል ። በዚህም ኔሮን ቄሣር “ግማሽ እብድ” ተብሎ ይጠራል ።
 የከተማይቱ መቃጠል በሕዝቡ ዘንድ ታላቅ ቊጣን ቀሰቀሰ ። ውብ ከተማቸው በመቃጠሏና ብዙ ዘመን ያፈሩት ሀብት አብሮ በመንደዱ ሕዝቡ ዓመፅ ሲያስነሣ ኔሮን ቄሣር ይህን ያደረጉት ክርስቲያኖች ናቸውና ማንም ሰው ነጻ ርምጃ እንዲወስድባቸው ብሎ አዘዘ ። የሕዝቡን ቊጣ አቅጣጫ ለማስቀየር የማገደው ክርስቲያኖችን ነበር ። ኔሮን ቄሣር ታላላቆቹን ሐዋርያት ጴጥሮስና ጳውሎስን የገደለ ነው ። በክርስቲያኖች ላይ የሚፈጸመው መከራ ስልቱና ዓይነቱ በእርሱና ከእርሱ ዘመን በኋላ የተለያየ ነበር፡-
1-  ክርስቲያኖችን በርጥብ ቆዳ ተጠቅልለው ለተራቡ አንበሶች ይሰጡአቸው ነበር ፤
2-  ክርስቲያኖችን ከተራቡ አንበሶች ጋር በማታገልም ይዝናኑባቸው ነበር ፤
3-  ክርስቲያኖችን በቁማቸው ሰም ነክረው ያቃጥሉአቸው ነበር ።
ክርስቲያኖች በመከራ ሰዓት ይጠየቁ የነበረው ጥያቄ፡-
1-  ክርስቶስን ክዳችሁ ቄሣር ጌታ ነው በሉ ፤

2-  ሮምን ማቃጠላችሁን እመኑ ነጻ ትወጣላችሁ የሚሉ ጥያቄዎች ነበሩ ።
ሌላው ኔሮን ቄሣር የሚታወቀው በኢየሩሳሌም ውድመትና በዘሩባቤል መቅደስ መደምሰስ ነው ። መቅደሱ እስካሁን ያልተሠራ በመሆኑ ኔሮንና ከእርሱ በኋላ የነበረው ቬስፓስያን ሲታሰቡ ይኖራሉ ። ኔሮን ቄሣር ከ60 ዓ.ም ጀምሮ በእስራኤል ላይ ጭቆና አብዝቶ ነበር ። በዚህ ምክንያት የቀናተኞች ወይም የቀነናውያን አርበኞች ግንባር ከ66 ዓ.ም ጀምሮ የነጻነት ትግል ጀመረ ። በዚህም መቅደሱንና ኢየሩሳሌም ነጻ አወጣ ። ኔሮን ቄሣርም ይህን ጉዳይ ያበርድ ዘንድ በጀነራል ቬስፓስያን የሚመራ 60 ሺህ ጦር ወደ ኢየሩሳም ላከ ። ጦሩም ኔሮን ቄሣር ሮም ላይ ራሱን እንዳጠፋ ሲሰማ ወደ ሮም ተመለሰ ። ከ68 ዓ.ም እስከ 69 ዓ.ም ሮምን ሦስት ቄሣሮች እየተፈራረቁ ቢያስተዳድሯትም ሥልጣኑ ሊረጋ አልቻለም ። በ69 ዓ.ም ግን በሕዝብ ምርጫ ኢየሩሳሌምን ለመውረር የሄደው ጀነራል ቬስፓስያን ቄሣር ተብሎ ነገሠ ። ቬስፓስያንም ቄሣር ተብሎ ሲነግሥ የተወዉን ኢየሩሳሌምን የማውደም ተግባር እንዲያስፈጽም ጀነራል የነበረውን ልጁን ቴቶን/ጥጦስን/ ላከ ።
ጀነራል ቲቶም ኢየሩሳሌም የደረሰው ሰማንያ ሺህ ሠራዊት እየመራ ነው ። ኢየሩሳሌምንም ደብረ ዘይት ተራራ ላይ ሁኖ ለመቆጣጠር ጀመረ ። እጅ እንዲሰጡ ዓመፀኞቹን ጠየቀ ። እነርሱ ግን እንኳን እጅ ሊሰጡ እጅ ለመስጠት ያመነታውን ባሰቃቂ ሁኔታ መግደል ጀመሩ ። በሚያዝያ ወር የፋሲካ በዓል እንዳለፈ እልቂቱ ጀመረ ። በመከበቡ ምክንያት ሕዝቡ በረሀብ አለቀ ። በረሀብም 11 ሺህ ሰው ረገፈ ። በዚህ ምክንያት የጥጦስ ሠራዊት ሰብሮ ገባ ። ቤተ መቅደሱን አፈረሰ ፣ ኢየሩሳሌምንም አቃጠለ ። አንድ ሚሊየን አንድ መቶ ሺህ ሕዝብ እንደ ከብት ታረደ ። የመጀመሪው መቅደስ ባቢሎናውያን ያፈረሱት በነሐሴ ወር ነበር ፤ ሁለተኛውም መቅደስ በነሐሴ ወር 70 ዓ.ም ፈረሰ ። ቬስፓስያንን ለማስደሰትና ድሉንም በሮም ለማክበር 700 የአይሁድ ምርኮኞች ወደ ሮም ተወሰዱ ። የኢየሩሳሌምን መጥፋት አስቀድሞ ጌታ በማቴዎስ 24 ላይ ተናግሮ ነበርና ከ64 ዓ.ም ጀምሮ ክርስቲያኖች ወደ ፔላ ቀበሌና አሥር ከተሞች ወደሚባሉት ሸሽተው አምልጠዋል ። ያን ጊዜ የፈረሰች እስራኤል እንደገና የተመሠረተችው በግንቦት ወር 1948 እ.አ.አ. ነው ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ