የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የቤተ ክርስቲያን ታሪክ /12

/አንብቡ ፣ አንብቡ ፣ አንብቡ ፣ ኧረ እባካችሁ አንብቡ !!!/
ሐዋርያው ጳውሎስ
ቅዱስ አውግስጢኖስ፡- “በእስጢፋኖስ ጸሎት ቤተ ክርስቲያን የጠፋውን ጳውሎስን አገኘች” ብሏል ። በኢየሩሳሌም የነበረው ስምንት ሺህ ሰዎችን ያቀፈው ማኅበረ እስጢፋኖስ ፣ ከእስጢፋኖስ ሞት በኋላ በተነሣው ስደት ወደ ሰማርያና ወደ ሌሎች ግዛቶች ተበተነ ። ተገልጋይ የነበረው ይህ ስምንት ሺህ ሰው ያቀፈው ማኅበር ስደት ሲመጣ ሁሉም አገልጋይ ሆነ ። በዚህም ቤተ ክርስቲያን ስምንት ሺህ ምስክሮችን አተረፈች ። የሐዋርያት ሥራ ጸሐፊ የሆነው ቅዱስ ሉቃስ፡- የተበተኑትም ቃሉን እየሰበኩ ዞሩ ይላል /የሐዋ. 8፡4/። ስለ ምግብ እደላ ቅሬታ የነበራቸው አሁን የባሰ ነገር ሲመጣ ለስደትም ቆራጥ ሆኑ ። እስጢፋኖስም ለምግብ እደላ ተመርጦ ታላቅ ምስክር ሆነ ። ትንሽ የሚመስለውን አደራ በጸጋ ስለተቀበለ ትልቅ ምስክር ሆነ ። በኋላ ቢመጣም ከሐዋርያት ቀድሞ ሰማዕት ሆነ ። በዚህም ቀዳሜ ሰማዕት ይባላል ። በትንንሽ ጉዳዮች ጠብ የምናበዛው ትልልቅ ስደቶች እስኪመጡ ነው ። መከራ የመትጋትና የመፋቀር አቅምን ይጨምራል ። ክርስቲያኖችም እንደ ጨው ዘር በሁሉ መበተን ጀመሩ ። የእስጢፋኖስ ሞት ብዙ ምስክሮችን አስነሣ ። ሊያጠፉት ሲሞክሩ የወንጌሉ እሳት ይበልጥ ነደደ ።

ቅዱስ እስጢፋኖስ በድንጋይ ሲወገር የወጋሪዎቹን ልብስ ይጠብቅ የነበረው የኋላው ጳውሎስ የፊቱ ሳውል ነበር ። ቅዱስ እስጢፋኖስ በድንጋይ ሲወግሩት፡- ተንበርክኮም፡- ጌታ ሆይ፥ ይህን ኃጢአት አትቍጠርባቸው ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ/የሐዋ. 7፡60/ ። ቅዱስ እስጢፋኖስ በዚህ ጌታውን መሰለ ። ይህ ጸሎት የጳውሎስን ልብ ነክቶታል ፣ ደግሞም የሚመለስበትን ጸጋ ልኮለታል ። ለዚህ ነው ቅዱስ አውግስጢኖስ፡- “በእስጢፋኖስ ጸሎት ቤተ ክርስቲያን የጠፋውን ጳውሎስን አገኘች” ያለው ።
ቅዱስ ጳውሎስ የወጋሪዎቹን ልብስ ይጠብቅ የነበረው በሁለት መንገድ ነው ። የመጀመሪያው ሰውነቱ ደቃቃ ስለነበር እነዚያን ጽኑ ድንጋዮች የማንሣት አቅም የለውም ። ሁለተኛው የወጋሪዎቹ አለቃ ስለነበር ትእዛዝ ሰጪ በመሆኑ ነው ። ከእስጢፋኖስ ሞት በኋላ ማኅበሩ ተበተነ ። ኢየሩሳሌምን ሲያጡ ኢትዮጵያን አተረፉ ። ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ተጠምቆ ፣ ክርስትናን ወደ ኢትዮጵያ ቤተ መንግሥት ይዞ የገባው በዚህ ጊዜ ነው ። ለምግብ እደላ ከተመረጡት ዲያቆናት አንዱ ፊልጶስ የኢትዮጵያዊውን በጅሮንድ አጠመቀ ። ጠላት አንድ ርስት ሲያሳጣ ሌላ ርስት ይገኛል ። ያን ጊዜ የተተከለች የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አሁንም አለች ። ሳንሄድሪን የተባለው ትልቁ የዚያን ጊዜ የዓለማችን ግዙፉ ሸንጎ ጳውሎስም በአባልነት የታቀፈበት ነበር ።ይህ ሸንጎ በመላው ዓለም በሚገኙ አይሁዳውያን ላይ በሃይማኖት ጉዳይ ሥልጣን አለው ። ይህ ሸንጎ በደማስቆ የሚገኙ ምኩራቦች ስደተኛ ክርስቲያኖችን እየያዙ በጳውሎስ እጅ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲያመጡና ፍርድ እንዲሰጥ ለጳውሎስ ደብዳቤ ጻፈለት ። ጳውሎስም እስከ ደማስቆ ድረስ በመንገዱ ያሉትን ክርስቲያኖች እያሰረ ጉዞውን ቀጠለ ። ወደ ደማስቆም ሲቃረብ ጌታ በብርሃን ጸዳል ተገናኘው ። የሞተው ክርስቶስ የተነሣም መሆኑን ከራሱ ድምፅ አረጋገጠ ። በመስቀል ላይ የሚሞት በእግዚአብሔር የተረገመ ነው ፣ እንዴት በእርሱ ታምናላችሁ ? እያለ ያሳድድ የነበረው ጳውሎስ ሞትን አሸንፎ ተነሣ መሆኑን ፣ የሰማይን መጋረጃ ገልጦ ሲያናግረው ደነገጠ ። ገዳይ ሁኖ ወደ ደማስቆ እየገባ ያለው ጳውሎስ ክርስቲያን ሁኖ ገባ ።
ሐዋርያው ጳውሎስ የራሱን ሕይወት በሚመለከት በአጭሩ የገለጠው በፊልጵ. 3፡5-11 ላይ ነው ። በዚህ ክፍል ላይ ያለፈውን ፣ የአሁኑንና የወደፊቱን ምርጫውን ይናገራል ። ያለፈው ሕይወቱ እስራኤላዊ ፣ ዕብራዊ ፣ ፈሪሳዊ ፣ ሕግ አክባሪ ፣ ቤተ ክርስቲያን አሳዳጅ ነበረ ። የአሁን ሕይወቱ ደግሞ የሚጎዳውን ነገር ብቻ ሳይሆን የሚጠቅመውንም ስለ ክርስቶስ የተወ ፣ የእምነትን ጽድቅ የተቀበለ ነው ። የወደፊቱ ምርጫው ደግሞ ክርስቶስንና የትንሣኤው ኃይል ማወቅ ፣ መከራውን መካፈል ፣ ወደ ሙታን ትንሣኤ መድረስ ፣ በሞቱ ክርስቶስን መምሰል ነው ።
ጳውሎስ በሮም ግዛት ውስጥ በጠርሴስ የተወለደ ከዳዊት ቤት ታማኝ ከነበረው ከነገደ ብንያም የተገኘ ነው ። የቀድሞ ስሙ ሳኦል ነው ፤ ይህም ዕብራዊ ስም ሲሆን ጳውሎስ ደግሞ ሮማዊ ስሙ ነው ። የእስራኤል የመጀመሪያው ንጉሥ ሳኦል ነው ። የእስራኤል የመጀሪያው ንጉሥ ሳኦልና የአዲስ ኪዳኑ ጳውሎስ ተመሳሳይ ነገር ነበራቸው፡-
1-  የሁለቱም ስማቸው ሳኦል ነው ።
2-  ሁለቱም የተገኙት ከታማኙ ከብንያም ነገድ ነው ።
3-  ንጉሥ ሳኦል አህያ ፍለጋ ወጥቶ ንጉሥ ሁኖ የቀረ ነው ፣ ጳውሎስም ክርስትናን ሊያጠፋ ወጥቶ ሐዋርያ ሁኖ የቀረበት ነው ።
ጳውሎስ በሮም ግዛት በጠርሴስ ቢወለድም ቤተሰቦቹ ዕብራይስጥንና የአይሁድን ልማድ በቅጡ ያስጠኑት ሰው ነበር ። የግሪክ ቋንቋም ተናጋሪ ነበር ። በልጅነቱ ወደ አይሁድ ምኩራብ ተወስዶ የዕብራይስጥን ፊደልና የብሉይ ኪዳንን ንባብ እስከ አሥራ ሁለት ዓመቱ ድረስ ከተማረ በኋላ በአሥራ ሁለት ዓመቱ የአካለ መጠን ዕድሜ ነውና ፋሲካን አክብሮ በዚያው የብሉይ ኪዳንን ትምህርት በትርጓሜ ለማጥናት በኢየሩሳሌም ኖሯል ። በኢየሩሳሌምም ሲኖር አባቱ ይከተለው የነበረውን የፈሪሳዊ የሃይማኖት ቡድን ተቀላቅሏል ። ጳውሎስ በሠላሳ ዓመቱም የአይሁድ ሸንጎ አባል ሁኖ ተመርጧል ።
ሐዋርያው ጳውሎስ ጠባዩ የሚያስገርም ነበር ። እውቀትን የሚወድ ሰው ነበር ። በዚያ ዘመን የነበረውን የግሪክ ፍልስፍና የሚያውቅ ተራማጅ ሰው ሲሆን የያዘውን የማይለቅ የሃይማኖት ሰው ነበረ ። ሐዋርያው ጳውሎስ የያዘውን ነገር በጥብቅ የሚይዝ የዓላማ ሰው ነበረ ። ለኦሪቱ ያሳየውን ኃይል ወንጌል ላይ ደግሞታል ። ምንም እንኳ የራሱ አገረ ስብከት በውል ባይታወቅም አሕዛብን በወንጌል የደረሰ ሰው ነበር ። ሰብኮ ዞር የሚል ሰው ሳይሆን ቤተ ክርስቲያንን የሚተክልና አለቃ ሹሞ የሚሄድ ሰው ነበር ። እውነትን በፍቅር የሚገልጥ ሰው ፣ የሰዎች መለወጥ ግድ የሚለው ፣ የሚያስተምራቸው በስማቸው የሚጠራና የማይረሳ ፣ በቃል ያገለገላቸውን በጸሎት የሚያገለግል ፣ መከራና ፈተና እጅ የማያሰጠው ፣ ለሁሉ ዝቅ የሚል ፣ የሹም ፊት የማያፍር ፣ በሸንጎ ተከስሶ ወንጌል የሚሰብክ ፣ ትልቁን ሐዋርያ ጴጥሮስን የሚገሥጽ ፣ የግንባር ሥጋ ተብሎ የሚጠራ ሰው ነበር ። ትሕትናውም ወደር የሌለው ፣ የትላንት ሕይወቱ የመጣበት መንገድ በመሆኑ ሲናገረው የማያፍር ስልጡን ሰው ነበር ፤ አንድ ነገርንም ቶሎ የማይቀበል ከተቀበለም ቶሎ የማይለቅ ሰው እንደሆነ ታሪኩ ያሳየናል ። ክርስትናንም ሲቀበል የአሁን እውቀቱን ከቀድሞ የብሉይ ኪዳን እውቀቱ ለማስታረቅ ሦስት ዓመታት በዐረብ ምድር ጥናት ያደረገ ሰው ነው ። ከሰው ይልቅም ለእግዚአብሔር ደስታ የሚኖር በመሆኑ ከማስመሰል ሕይወት ነጻ ነበር ። በስብከቱም መላውን ግሪክን ፣ ታናሽዋን እስያ ፣ ሮምን ፣ በመጨረሻም እስፓኝን የደረሰ ትልቅ ሐዋርያ ነው ። ድንግላዊና እንደ እግዚአብሔር ቃል ለመኖር የሚሻ ሰው ነበር ። ዘረኝነትን ድል የነሣ ፣ ማንንም ሳይንቅ ሰውን በክርስቶስ የተቀበለ የአሕዛብና የአይሁድ ወዳጅ የነበረ ፣ ግዛቱን ያላጠበበ ሰው ነበር ። በዚያ ዘመን የነበሩትን ብቻ ሳይሆን እኛንም በመልእክቱ የሚያገለግለን አሥራ አራት የጽድቅ መልእክቶችን የጻፈ ሰው ነው ። በእስረኝነቱ ወራትም ኃያል የሚሆኑ አራት መልእክታትን ጽፎአል ። እስረኝነት ያላቆመው ሰው ነበር ። በ67 ዓ.ም. አንገቱን በሰይፍ ተቀልቶ ሰማዕት ሁኗል ፤ በሮም ኦስቲያ መንገድም ተቀብሯል ።
ከመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ሲተላለፍ የነበረውን ትውፊት በማሰባሰብ የጳውሎስን ተክለ ቁመና የምሥራቅ ቤተ ክርስቲያን አባቶች እንዲህ ይገልጹታል፡- የሐዋርያው ጳውሎስ ተክለ ሰውነት ጭንቅላቱ ትልቅና ራሰ በራ ነበር ። የሁለቱ ዓይኖቹ ቅንድቦች የገጠሙ ነበሩ ። ዓይኖቹም ሁልጊዜ የበሩ ነበሩ ። አፍንጫው ትልቅና ቀጥ ብሎ የወረደ ፣ ጽሕሙ ረጅምና ሪዙም ረጃጅም ናቸው ፤ አንገቱ አጠር ያለ ሁኖ ትከሻው ክብና ጎባባ እግሮቹም ደግሞ ከጉልበቱ ላይ የተቃረቡ ነበሩ ። ቁመቱ አጠር ያለ ደንዳና ሰው እንደነበር ይነገርለታል ። በቤተ ክርስቲየን ታሪክ ውስጥ ከሚነሡ ታላላቅ አባቶች አንዱ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ነው ። በረከቱ አይለየን ።
ይቀጥላል
ዲ.አ.መ

ያጋሩ

ያግኙን

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ስልክ ፡ +251930006086                             +251911699907

ኢሜል፡ ashumekon@gmail.com

የገጹ ዓላማ

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።

አሸናፊ መኮንን
Ashenafi Mekonnen
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
Commercial Bank of Ethiopia
1000165078482

አቢሲኒያ ባንክ
Bank of Abyssinia
23202573

ሕብረት ባንክ
Hibret Bank
1030416569497017

ወጋገን ባንክ
Wegagen Bank
0870286030101

አዋሽ ባንክ
Awash Bank
01320034656200

በማህበራዊ ሚዲያ ይወዳጁን።

copyright @ 2021 ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን 
በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።