የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የቤተ ክርስቲያን ታሪክ /17/

/አንብቡ ፣ አንብቡ ፣ አንብቡ ፣ ኧረ እባካችሁ አንብቡ !!!/
የዳክዮስ ዘመን
የዳክዮስ ዘመን 249-251 ዓ.ም ነው ። የዳክዮስ ዘመን ከሌሎቹ የመከራ ዘመናት ልዩ የሚደርገው ከሮማ አማልክት ውጭ ወይም ቄሣሮችን ከማምለክ በቀር ሌላ አምልኮት መፈጸም በሞት ያስቀጣል የሚል አዋጅ የወጣበት ዘመን ነው ። ክርስትናው እስከ ዛሬ በአንዱ ግዛት መከራ ሲጸና ወደ ሌላው ግዛት በመሄድ ዕረፍትና ፋታ የነበረው ሲሆን አሁን ግን ከቀድሞ በበለጠ ለክርስቲያኖች የስደትና የሞት ዘመን መጣ ። አረማውያንና አይሁዳውያን እስከ አሁን እምነታቸውን በሚመለከት ችግር አልገጠማቸውም ነበር ። ዳክዮስ ግን ከሮም የቄሣር አምልኮት ውጭ ማምለክ ሞት ያስከትላል የሚል አዋጅ ስላመጣ ሁሉም የተጨነቁበት ዘመን ነበር ። ክርስቲያኖችን በእምነታቸው ምክንያት የነበራቸው ብቸኛ መንገድ ስለ ሃይማኖታቸው መሰየፍ ሆነ ። ዳክዮስም ሕፃናትን እንኳ ሳይተዉ ሁሉንም በሰይፍ ስለት ፣ በእሳት ግለት አጠፋቸው ። ከእርሱ በኋላ የተነሡም በዚሁ መንገድ እንዲሄዱ መንገዱን ከፈተ ። ዳክዮስ ክርስቲያኖች ለሮማ አማልክት እንዲሰግዱና እንዲሠዉ እንቢ ካሉ ንብረታቸው እንዲዘረፍ ፣ ከዚያም ባሻገር ለአንበሶች እየተጣሉ እንዲበሉ ፣ በእሳት እንዲቃጠሉ አደረገ ። ክርስቲያኖችም ለጣዖታት መስገዳቸውን የሚከታተል ቡድን ተቋቋመባቸው ። አንዳንድ ክርስቲያኖችም ፈርተው ሰገዱ ፣ ሌሎችም ጉቦ እየከፈሉ ሰግደዋል እንዲሉላቸው ባለሥልጣኖችን መማጸን ጀመሩ ፣ ሌሎችም በቆራጥነት ክርስቲያኖች የታሰሩበት እስር ቤት ሮጠው በመግባት በፈቃዳቸው ለሰማዕትነት ተዘጋጁ ፣ አንዳንዶችም አገር እየለቀቁ ዕረፍት ያለበት ስፍራ ሸሹ ። በዚህ በዳክዮስ ዘመን የታወቁ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ሰማዕት ሁነዋል ። የሮሙ ኤጲስ ቆጶስ  ፋቢያኖስ ፣ የአንጾኪያው ኤጲስ ቆጶስ ባቢላስ ፣ የኢየሩሳሌሙ ኤጲስ ቆጶስ እለእስክንድሮስ ፣ በሮም ጦር ሠራዊት አዛዥ የነበረው ሰማዕቱ መርቆሬዎስ የተሠየፉበት ዘመን ነው ።
ከዳክዮስ በኋላ የነገሠው ጋሉስ ሲሆን 251-253 ዓ.ም ነው ። ስደቱ የበረደ ይመስላል ። ከቄሣር ጋሉስ በኋላ ቫሌርያን ከ253-260 ዓ.ም የነገሠ ሲሆን መከራው እንደገና ቀጠለ ። 257 ዓ.ም መከራውን አቀጣጠለው ። ዳክዮስ እንዳደረገው ጳጳሳትና ቀሳውስትን በማስወገድ ክርስትናን ማጥፋት ይቻላል ብሎ ያሰበ ቄሣር ነው ። ከዚህ ዘመን በኋላ ለ43 ዓመታት ማለትም ከ260-303 ስደቱ ቆመ ። ጋሊኑስ /260-268/ የተባለው ቄሣርም ክርስትናን እውቅና ያለው ሃይማኖት አድርጎት ነበር ። በዚህ ዘመን አብያተ ክርስቲያናት መታነጽ ፣ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን በይፋ መፈጸም ጀመሩ ። ነገር ግን በክርስቲያኖች መካከል እርስ በርስ መለያየት ተከሰተ ። የመለያየቱ አንዱ መነሻ ክርስትናን ክደው ወደ ጣዖት አምልኮ ሄደው የነበሩ ፣ ጉቦ ሰጥተው ያመለጡ ንስሐ በመግባት ሲመጡ ያልጸኑ ክርስቲያኖች የሚል ስም እየተሰጣቸው እንደገና እነርሱን መቀበል የለብንም የሚል ጠብም መወጋገዝም መነሣት ጀመረ ። አንዳንዶች ብርቱ ቅጣት ይሰጣቸው ፤ ሁለተኛዎቹ ደግሞ የዕድሜ ልክ ንስሐ ይሰጣቸው ፤ ሦስተኛዎቹ ደግሞ ዳግም ይጠመቁ በማለት ጥላቻቸውን ማራመድ ጀመሩ ። በመጨረሻ ጥምቀት አንድ በመሆኑ ዳግም ጥምቀት ቀርቶ በንስሐ እንዲመለሱ ተደረገ ። ቀጥሎ የምናየው የዲዮቅልጥያኖስን ዘመን ነው ።
ይቀጥላል
ዲአመ

ያጋሩ