የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የቤተ ክርስቲያን ታሪክ/3

የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዘመን ሲከፈል
የቤተ ክርስቲያን ታሪክ የሚጀምረው በዘፍ. 3፡15 ላይ ለአዳም በተሰጠው የተስፋ ቃል ላይ ነው ። ቤተ ክርስቲያን ከአብርሃም እስከ መጥምቁ ዮሐንስ ዘመን በጠራ ዝግጅት ውስጥ ነበረች ። የቤተ ክርስቲያን መደበኛ ታሪክ የሚጀምረው ከጌታችን መወለድና በሥጋ መገለጥ አንሥቶ ነው ። ቤተ ክርስቲያን በበዓለ ሃምሳ ልደቷን አክብራ በዓለም ሁሉ ተሰራጭታለች ። የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከቤተ ልሔም እስከ ቀራንዮ ፣ ከካታኮምብ እስካለንበት ዘመን ድረስ ያለውን የምናይበት መጽሔት ነው ። ክርስትና የበቀለው በምድረ እስራኤል ጌታችን በተሰቀለበት በቀራንዮ ሳለ ለዘመናት እንደ ክርስትና መዲና ስትታይ የኖረችው ሮም ናት ። ይህም ቤተ ክርስቲያን ምን ያህል በሮማ መንግሥታት የፖለቲካ ተጽእኖ ውስጥ መውደቋን ያሳየናል ። ስለዚህ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከኢየሩሳሌም እስከ ሮም ያለውን የምንዳስስበትም ነው ። ቤተ ክርስቲያን በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች በዘመን ትከፈላለች፡-

1-  በተስፋ ዘመን የነበረች ቤተ ክርስቲያን ፤
2-  በፍጻሜ ዘመን ያለች ቤተ ክርስቲያን ።
በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በዋናነት የምናየው ቤተ ክርስቲያን የተከፋፈለችበትን ዘመንና ምክንያት ነው ። አንዲቷ ቤተ ክርስቲያን የተከፈለችበት ዘመን፡-
   1-  በ451 ዓ.ም በኬልቄዶን ጉባዔ ቤተ ክርስቲያን ለሁለት ተከፈለች ። በዚህም የምዕራቡ ራሱን ካቶሊክ ወይም ኩላዊ – የሁሉም ብሎ ሰየመ ። የምሥራቁም ኦርቶዶክስ የሚለውን የኒቅያ ስያሜ ያዘ ።
   2-  በ1054 ዓ.ም. ቤተ ክርስቲያን ለሦስት ተከፈለች ። በዚህም ካቶሊክና የምሥራቅ ኦርቶዶክሶች የተለያዩበት ነው ። የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ዋና የማዕዘን ድንጋይ የሆነውን “መንፈስ ቅዱስ ከአብ ይሠርጻል” የሚለውን የቀና ትምህርት “መንፈስ ቅዱስ ከአብና ከወልድ ይሠርጻል” በሚል አስተምህሮ በመለወጧ የግሪክና የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ተለያይተዋል ።
ማስታወሻ፡- ኦርቶዶክስ የሚለውን ስም የሚጋሩ ለሁለት ይከፈላሉ፡- የምሥራቅ ኦርቶዶክስና የኦሬንታል ኦርቶዶክስ ይባላሉ ። የምሥራቅ ኦርቶዶክስ የሚባሉት ግሪክ ፣ ሩሲያ ፣ ሰርቢያ ፣ ዩጎዝላቪያ ናቸው ። የኦሬንታል ኦርቶዶክስ የሚባሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ፣ የግብጽ/ኮፕት/ ፣ የሶሪያ፣ የአርመን ፣ የሕንድ ፣ የኤርትራ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ናቸው።
   3-  በ1517 ዓ.ም. በፕሮቴስታንት እንቅስቃሴ ቤተ ክርስቲያን ለአራት ተከፍላለች ። ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ተቃውሞ አድርገው የወጡ ሉተርና ተከታዮቹ ራሳቸውን ፕሮቴስታንት ብለው ሰይመዋል ። ፕሮቴስታንት ማለት ተቃዋሚ ማለት ነው ።
የቤተ ክርስቲያን ታሪክ አከፋፈል
ቤተ ክርስቲያን ሦስት ዓይነት የታሪክ አከፋፈሎች አሏት፡-
1-  የጥንት ቤተ ክርስቲያን ታሪክ
2-  የመካከለኛው ዘመን የቤተ ክርስቲያን ታሪክ
3-  የኋለኛው ዘመን ወይም አዲሱ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ
የጥንት ቤተ ክርስቲያን ታሪክ
የጥንት ቤተ ክርስቲያን ታሪክ የተለያየ አከፋፈል አለው ። ታሪካዊ ክስተቶች ልባቸውን እንደ ገዛው መጠን ዘመኑን በተለያየ መንገድ ይከፋፍሉታል።
1-  ከ33 ዓ.ም. እስከ 313 ዓ.ም ይህ ዘመን ከጌታችን ሞትና ትንሣኤ እስከ ቆስጠንጢኖስ መንገሥ ወይም ቤተ ክርስቲያን ነጻነት እስካገኘችበት ድረስ ያለው ነው ። ይህ ዘመን የግሪካውያንና የሮማውያን ሥልጣኔ ተቀላቅሎ ዓለምን የሚገዛበት ጊዜ ነው ።  ግሪካውያን የኃይል በትራቸው ከእስክንድር በኋላ ሲያበቃ ጥበባቸው ግን ዓለምን መግዛት ጀመረ ። ይህም አካልን ከመግዛት የሰውን መንፈስ ወደ መግዛት የተሻገሩበት ነው ። በዚህ ዘመን ሮማውያን በሥልጣን ፣ ግሪኮች በጥበብ ዓለምን ይገዙ ነበር።
2-  ከ33-451 ዓ.ም. ይህም ከጌታችን ሞትና ትንሣኤ እስከ ኬልቄዶን ጉባዔ ያለው ጊዜ ነው ። የጥንቷን ቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንዲህ የሚከፍሉ አሉ ። 451 ዓ.ም ቤተ ክርስቲያን ለሁለት የተከፈለችበት ትልቅ ታሪካዊ ሁነት ያለበት ነው ።
ምዕራባውያን ለጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ የራሳቸው አከፋፈል አላቸው።
1- ከ33 ዓ.ም. እስከ 590 ዓ.ም ። ይህም ከጌታችን ሞትና ትንሣኤ ትልቁ ጎርጎርዮስ ጳጳስ እስከሆነበት ያለው ዘመን ነው ።
     2- ከ33 ዓ.ም. እስከ 476 ዓ.ም ። ይህ ጊዜ ከጌታችን ሞትና ትንሣኤ የሮም መንግሥት እስከ ወደቀበት ያለውን የሚከልል ነው ። ከሰሜን አውሮፓ የፈለሱ አረመኔዎች የሮምን መንግሥት የጣሉበት “የሮም አወዳደቅ” ተብሎ የተጠራበት ዘመን ነው ። ይህ ዘመን የሮማና የግሪኮች የዘመናት አገዛዝ ስፍራ የለቀቀበት በመሆኑ ለጥንቷ ቤተ ክርስቲያን እንደ መክፈያ ያዩታል ። እንግዲህ ምዕራባውያን የጥንቷን ቤተ ክርስቲያን ዘመን በሁለት እይታ እንደሚያዩት ልብ በሉ ።
ማስታወሻ፡- ዓለምን ይገዛ የነበረው የቄሣሩ መንግሥት ፣ የሮሙ ኃያል ለዚህ ዓለም አቀፍ ግዛቱ የሰጠው ስያሜ “ፓክሳ ሮማና” የሚል ነው ። ትርጉሙም፡- “ሮም ለዓለም ያመጣችው ሰላም” የሚል ነው ። ይህ ከአምስት መቶ ዓመታት በላይ የሰለጠነው የሮማ ግዛት በመስከረም 4 / 476 ዓ.ም. በድንገት ፈራረሰ ። ይህ የታፈረና የተፈራ መንግሥት እዚህ ግባ በማይባሉ ወራሪዎች ፈርሷል ። ምክንያቱ ምን እንደሆነ ቢጠና በዋናነት የሮማ መንግሥት ውስጥ ሥር የሰደደው የሞራል ውድቀት ነው ። ከዚያ ጊዜ አንሥቶ ለግለሰቦች ፣ ለማኅበራትና ለአገር ውድቀት ማሳያ ጥቅስ የሆነው “የሮም አወዳደቅ” የሚል ነው ።
በሁሉም አከፋፈል ውስጥ የጥንቷ ቤተ ቤተ ክርስቲያን በውስጡ ሦስት ዘመኖች አሉት፡-
1-  ዘመነ ሐዋርያት
2-  ዘመነ ሰማዕታት
3-  ዘመነ አበው
ዘመነ ሐዋርያት
ይህም ከ33-100 ዓ.ም ያለውን ጊዜ የሚከልል ነው ። የመጨረሻው ሐዋርያ ወንጌላዊው ዮሐንስ ዕረፍት በ97 ዓ.ም ገደማ ነውና ይህ ዘመን ዘመነ ሐዋርያት ይባላል ።
ዘመነ ሰማዕታት
ከ100 – 313 ዓ.ም ያለው ጊዜ ነው ። 313 ዓ.ም. ቆስጠንጢኖስ የሃይማኖት ነጻነት ያወጀበት ዘመን ነው ።
ዘመነ አበው
ከ313-451 ዓ.ም ያለው ነው ። ይህ ዘመን ታላላቅ አባቶች የተነሡበት  በፍልስፍና ፣ በሕግ ፣ በተፈጥሮ ሳይንስ ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ፣ በንግግር ችሎታ በጣም የመጠቁ መምህራን የተነሡበት ዘመን ነው ።
የመካከለኛው ዘመን የቤተ ክርስቲያን ታሪክ
 የምዕራባውያን አከፋፈል ከ590-1517 ዓ.ም ያለው ነው ። ይህም ታላቁ ጎርጎርዮስ ጳጳስ ከሆነበት ፕሮቴስታንት እስከ ተነሡበት ጊዜ ነው ። የሌሎች አከፋፈል ከ313-1453 ዓ.ም. ድረስ ያለው ነው ። ይህም ቆስጠንጢኖስ የሃይማኖት ነጻነት ካወጀበት እስከ ቊስጥንጥንያ በቱርኮች መውደቅ ያለውን ጊዜ የሚከልል ነው ይላሉ ።
ማስታወሻ- ቊስጥንጥንያ ዛሬ ቱርክ ተብላ የምትጠራዋ ናት ። ትልቅ የሃይማኖት መዲና ነበረች ። የሮማ መንግሥት ዓለምን በሚያስተዳድርበት ዘመን ሁለተኛዋ መናገሻ ከተማ ነበረች ። ቁስጥንጥንያ የቢዛንታየን ነገሥታት የነበሩባት የሮም መንግሥት መናገሻ ያደረጋት በመጨረሻ በቱርኮች በመወረር የሃይማኖት ደብዛዋ የጠፋች አገር ናት ። ቢዛንታየን መንደር ሲሆን የነገሥታት ዘር የሚወጡበት ስፍራ ስለነበር የቢዛንታየን ነገሥታት በሚል ሲጠራ ኑሯል ።
በቊስጥንጥንያ የነበረው በስድስተኛው ክፍለ ዘመን በቅድስት ሶፊያ ሃጊያ የተሠራ ትልቅ ቤተ ክርስቲያን የእስላም መስጊድ በመሆን እስከ 1935 ዓ.ም. ቢቆይም ከዚህ ጊዜ በኋላ ግን ሙዝየም ሁኗል ። ክርስትና በዚህ ቦታ ላይ ክፉኛ የተጎዳበት ስለሆነ በ1453 ዓ.ም የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ሁለተኛው የዘመን ምዕራፍ ሊሆን ችሏል ። 476-1453 ዓ.ም. ያለው የመካከለኛው ዘመን የቤተ ክርስቲያን ታሪክ የጨለማው ዘመን በማለት ይጠሩታል ። ይህ ዘመን የሮማ መንግሥት የወደቀበት ፣ ሁከት የበዛበት ፣ ቤተ ክርስቲያን የተከፋፈለችበት ዘመን በመሆኑ የጨለማ ዘመን የሚል ስያሜ ሊያገኝ ችሏል።
ማስታወሻ፡- ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በ1957 ዓ.ም. ከእንግሊዟ ንግሥት ከኤልሳቤጥ ጋር ሁነው የመረቁት የአክሱም ጽዮን ቤተ ክርስቲያን የተሠራው በሃጊያ ሶፊያ ቤተ ክርስቲያን ቅርጽ ነው ። የቅድስት ሶፊያ ቤተ ክርስቲያን በስድስተኛው ክፍለ ዘመን በንጉሥ ዮስጢንያኖስ የተሠራ ነው ።
የኋለኛው/ አዲሱ/ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ
ከ16ኛው ክፍለ ዘመን እስካለንበት ዘመን ድረስ ያለውን የሚጠቀልል ነው ። ይህም ዘመን ቤተ ክርስቲያን ከሦስት ወደ አራት የተከፈለችበት ዘመን ነው ። ከዚያ በኋላ ግን ቊጥር ወደሌለው የፕሮቴስታንት መከፋፈል ፣ ልክ የሌላቸው አብያተ ክርስቲያናት ፣ ዶክትሪኖችና ዶግማዎች የተነሡበት ነው ።
ይቀጥላል
አንብቡ ፣ አንብቡ ፣ አንብቡ ኧረ እባካችሁ አንብቡ !!!
ዲአመ 
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ