የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የቤተ ክርስቲያን ታሪክ/7

አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት
ደቀ መዝሙር የተማሪነት ስም ሲሆን ሐዋርያ ደግሞ የተልእኮ ስም ነው ። ደቀ መዝሙር አዳሪ ተማሪ ፣ የመምህሩን ሕይወትና እውቀት የሚካፈል ፣ እንደ ልጅ የሚያገለግል ፣ እንደ ሕፃን የሚጠይቅ ፣ “ተናገር በከንፈሬ ፣ ተቀመጥ በወንበሬ” ተብሎ የሚሾም ፣ ተተኪ ፣ እጩ መምህር ፣ ከመምህሬ በፊት ያድርገኝ ብሎ የሚዋጋ ወታደር ፣ የእገሌ ተማሪ ነኝ ብሎ የእውቀት አባቱን ስም የሚያስጠራ ፣ በመከራና በጭንቅ ጎዳና ነፍሱን የሚያጠግብ ፣ የዲያቆን የጳጳስ መነሻ ማለት ነው ። ሐዋርያ የሚለው ቃል ደግሞ ሒያጅ ፣ መንገደኛ ፣ ገስጋሽ ፣ መልእክተኛ ማለት ነው ። በምሥጢራዊ ትርጉሙ ደግሞ የክርስቶስ አፍ ፣ ባለ አደራ ፣ ባለሥልጣን ፣ ክርስቶስን በዓይኑ አይቶ በጆሮው ሰምቶ ሊመሰክርለት የወጣ ማለት ነው ። እስራኤል በ12 የነገድ አለቆች እንደ ተመሠረተች ቤተ ክርስቲያንም በአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ተመሥርታለች ።

አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ዝርዝራቸው በአራት ስፍራ ላይ ተቀምጦል ። /ማቴ. 10፡2-4 ፤ ማር.3፡16-19፤ ሉቃ. 6፡13-16 ፤ የሐዋ. 1፡13/ ። አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት አብዛኛዎቹ የተጠሩት ከገሊላ አውራጃ ነው ። የተጠሩበት ነገድም ጴጥሮስና እንድርያስ በአባታቸው ከነገደ ሮቤል በእናታቸው ከነገደ ስምዖን ናቸው ። ያዕቆብና ዮሐንስም በአባታቸው ከነገደ ይሁዳ በእናታቸው ከነገደ ሌዊ ናቸው ። ፊልጶስ ከነገደ ዛብሎን ፣ በርተሎሜዎስ ከነገደ ንፍታሌም ፣ ቶማስ ከነገደ አሴር ፣ ማቴዎስ ከነገደ ይሳኮር ፣ ያዕቆብ ወልደ እልፍዮስ ከነገደ ጋድ ፣ ስምዖን ቀነናዊ ወይም ናትናኤል ከነገደ ብንያም ፣ ታዴዎስ የተባለው ልብድዮስ ከነገደ ዮሴፍ ፣ በይሁዳ ምትክ የገባው ማትያስ ከነገደ ዳን ናቸው ። የአስቆሮቱ ይሁዳም ከነገደ ዳን ነበር።
በዚህ አገላለጽ መሠረት አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ከአሥራ ሁለቱ ነገደ እስራኤል ተጠርተዋል ። ተደራራቢ ስም ያላቸው አሉ ። ይህም በአይሁዳውያን የተለመደ ነው ። አይሁዳውያን ብዙ አገዛዞችን ስላስተናገዱና በብዙ አገሮች ተበትነው ስለኖሩ አንዱን ሰው በዕብራይስጥና በግሪክ ስም መሰየም የተለመደ ነው ። ለምሳሌ፡-
1-  ጴጥሮስ፡- ስምዖን ኬፋ ይባላል ። ስምዖን ወላጆቹ ያወጡለት ሲሆን ከነገደ ስምዖን ስለተወለደ የወጣለት ስም ይመስላል ። ጴጥሮስና ኬፋ ተመሳሳይ ትርጉም ሲኖራቸው ጴጥሮስ በግሪኩ ፣ ኬፋ በአራማይክ ሲሆን ትርጉሙ ዓለት ማለት ነው ። ይህን ስም ያወጣለት ጌታችን ነው ።

2-  ዲዲሞስ ወይም ቶማስ ። ቶማስ በአራማይክ ሲሆን ዲዲሞስ በግሪክ ነው ። የሁለቱም ትርጉም መንታ ማለት ነው ።

3-  ማቴዎስ፡- ሌዊ የሚል ስም አለው ። ቀራጩ የሚል የስም ቅጥያም አለው ። ማቴዎስ መጠሪያው ሲሆን ሌዊ የቤተሰብ ስም ነው ።
ሐዋርያት የተለያየ ስያሜ አግኝተዋል ። “የምሥጢር ደቀ መዛሙርት” የሚባሉ ጴጥሮስ ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ ናቸው ። ማር. 5፡37 ፤ ሉቃ. 8፡51 ፤ ማቴ. 17፡1 ። “አእማድ” ወይም ምሰሶዎች ተብለው እነዚህ ሦስት ደቀ መዛሙርት ተጠርተዋል ። /ገላ. 2፡9 /። ደቀ መዛሙርቱ የአብዛኛዎቹ ሙያ ተመሳሳይ ነው ። ጴጥሮስና እንድርያስ ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ ፣ ፊልጶስና ናትናኤል ዓሣ አጥማጅ ሲሆኑ ፤ ትንሹ ያዕቆብና ይሁዳ እንጨት ጠራቢ ናቸው ። ማቴዎስ ቀራጭ ነው ። በሐዋርያት ወንድማማቾች የሆኑ ሦስት ጥንዶች አሉ፡- ጴጥሮስና እንድርያስ ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ ፣ ትንሹ ያዕቆብና ይሁዳ ናቸው ። ይሁዳ ያልነው ጌታን የሸጠው አይደለም ።
በአዲስ ኪዳን በብዛት ስሙ የተጠቀሰው ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ሲሆን በፈጣንነቱና በተቀበለው አደራ እንደ ሊቀ ሐዋርያት ይታያል ። ከሐዋርያትም በቶሎ የሞተው ትልቁ ያዕቆብ ወይም የዘብዴዎስ ልጅ ነው ።በሄሮድስ አግሪጳ ዘመን በ44 ዓ.ም. ነው ። /የሐዋ. 12፡2 /። ሁሉም ሐዋርያት ዓለምን በዕጣ ተከፋፍለው ወንጌልን ሰብከዋል ። በሰማዕትነትም ተጋድሎአቸውን ፈጽመዋል ። ቅዱስ ጴጥሮስ በ67 ዓ.ም. በሮም የቁልቁሊት ተሰቅሎ ተጋድሎውን ፈጽሞአል ። ይህም ሐምሌ አምስት ቀን ይታሰባል ። ቅዱስ ጳውሎስም በዚሁ ቀን ከጴጥሮስ ጋር የሞተ ሲሆን አሟሟቱም አንገቱን በሰይፍ ተቀልቶ ነው ። ጴጥሮስ በቫቲካን ኮረብታ ፣ ጳውሎስ በኦስቲያ መንገድ መቀበራቸውን በሁለተኛው ክፍለ ዘመን የነበረው ጋይዮስ መስክሯል ። እንድርያስ በፍልስጤም ፣ በእስኪስያ ፣ በስራኪ ፣ በመቄዶንያ ፣ በትንሽዋ እስያ ፣ በግሪክ አስተምሮ የቊስጥንጥንያን ቤተ ክርስቲያን መሠረተ ። ፓትራ በምትባል አገር ሲያስተምር በመስቀል ላይ ተሰቅሎ በደንጊያ ተወግሮ ሞቷል ። የራስ ቅሉም በ1208 ዓ.ም. በመስቀል ጦረኞች ወደ ሮም ተወስዶ የነበረ ሲሆን በ1964 ዓ.ም ለግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ተመልሷል ። ቶማስ በፋርስ በህንድ አስተማረ ። ማቴዎስ በፍልስጤም ፣ በኢትዮጵያና በፋርስ እንዲሁም በመቄዶንያ አስተማረ ። ፊልጶስ በትንሽ እስያ በፍርግያ አስተማረ ። በርተሎሜዎስ በሕንድና በአርመን አስተማረ ። ናትናኤል በመስጴጦምያ ፣ በግብጽ ፣ በሰሜን አፍሪካ ሰበከ ። ትንሹ ያዕቆብ ወይም ወልደ እልፍዮስ በፋርስና በግብጽ አስተማረ ። ማትያስ በግብጽ ፣ በቀጰዶቅያ ፣ በኑብያ ሰበከ ።
ይቀጥላል
አንብቡ ፣ አንብቡ ፣ አንብቡ ፣ ኧረ እባካችሁ አንብቡ !!!
ዲአመ 
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ