የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የቤተ ክርስቲያን ታሪክ /9

የሃይማኖትና የፖለቲካ ቡድኖች
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንግድነት ወደ ምድር ሲመጣ በምድረ እስራኤል ሰባት የሚጠጉ የሃይማኖትና የፖለቲካ ቡድኖች ነበሩ ። እነዚህ የሃይማኖት ቡድኖች የራሳቸው የሆነ ተጽእኖ የነበራቸው በመሆኑ በቤተ ክርስቲያን የታሪክ ሂደት ውስጥ የሚጠቀሱና የሚጠኑ ሁነዋል ። የብሉይና የሐዲስ መጻሕፍትን ለመረዳት ስለ እነዚህ ወገኖች ማወቅ ይጠቅማል ። እነዚህ በታሪክ ውስጥ ብቻ የሚጠቀሱ ሳይሆን በየዘመናቱ ብቅ የሚሉ አመለካከቶችን የያዙ ቡድኖች ነበሩ ። ክርስትና ከእነዚህ የሃይማኖት ቡድኖች በምን እንደሚለይ ለማወቅ ስለ እነርሱ ማወቅ በእጅጉ ያስፈልገናል ። እነዚህ የሃይማኖት ቡድኖች፡-
1-  ፈሪሳውያን
2-  ሰዱቃውያን
3-  ፀሐፍት
4-  ኤሤያውያን
5-  ሄሮዳውያን
6-  የአይሁድ ሸንጎ
7-  ቀነናውያን በመባል ይታወቃሉ ።

1- ፈሪሳውያን
ፈሪሳዊ የሚለው ቃል በዕራይስጡ “ፓራሽ” ከሚል ቃል የወጣ ሲሆን ትርጉሙም “የተለየ” ማለት ነው ። ፈሪሳውያን ስለ ሃይማኖታቸው ፣ ስለ አገርና ስለ ቅድስና እንደሚያስቡ የሚናገሩ ናቸው ። ፈሪሳውያን እምነታቸው ተጽፎ በተገኘው በብሉይ ኪዳን ላይ ይመሠረታል ። በተጨማሪም የሽማግሌዎች ወግ /ሥርዓተ ረበናት/ የሚባለውን ይቀበላሉ ። ፀሐፍትና ረቢ የሚባሉ ሰዎች በተናገሯቸው አባባሎች እምነታቸውን ያጠናክራሉ ። በሙታን ትንሣኤ የሚያምኑ ሲሆን የሰው ልጅ ከትንሣኤ በኋላ በዚህ ዓለም እንዳለው ኑሮ ይቀጥላል ብለው ይቀበላሉ ። በቅዱሳን መላእክትና በርኩሳን መናፍስት መኖር ያምናሉ ። የነፍስን አለመጥፋትና ከሞት በኋላ ሕይወት እንዳለ ይቀበላሉ ። ፈሪሳውያን ቅድስናቸውን ለመጠበቅ በሚያደርጉት ጥረት እንደ እነርሱ ጥብቅ ያልሆኑትንን አይሁድ በንቀት እየተመለከቱ ኃጢአተኞች ሲሏቸው አሕዛብን ግን ጥላቸው እንኳ ያረክሰናል እያሉ ይሸሹአቸው ነበር ። የእግዚአብሔርን ቃል በልብሳቸው ላይ ጭምር በመጻፍ ቃሉ ከልባቸው ሞልቶ በልብሳቸው የፈሰሰ ነው እንዲባል ይፈልጋሉ ። ጌታችን በተወለደበት ዘመን ስድስት ሺህ የሚያህሉ ፈሪሳውያን ነበሩ ። ትልቁ የመለያ ጠባያቸው ነገሮችን ማገናኘት ነው ። ኑሮአቸው ድህነት ያጠላበት ሲሆን እውቀታቸውም መጠነኛ ነበር ። በኋላ ላይ ከእነዚህ ወገኖች ተከፍለው በኩምራን ገዳም መሥርተው የሚኖሩ ኤሤያውያን የሚባሉ ነበሩ ። በምድረ እስራኤል የነበሩት ሁለት ታላላቅ የሃይማኖት ቡድኖች ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ነበሩ  ። ሁለቱም የሃይማኖት ቡድኖች የተመሠረቱት ከክርስቶስ ልደት በፊት በሁለተኛው ክፍለ ዘመን ላይ ሲሆን የተመሠረቱበት ምክንያትም የግሪክ  ተጽእኖ በአይሁድ መካከል መከፋፈልን በመፍጠሩ አንድነትን ለመጠበቅ ሲባል ነው ። ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ሃይማኖታዊ ልዩነት የነበራቸውና የማይስማሙ ነበሩ ። ኒቆዲሞስና ቅዱስ ጳውሎስ ፈሪሳውያን ነበሩ ።
ታልሙድ የተባለው የአይሁድ መጽሐፍ እንደሚናገረው ፈሪሳውያን ሰባት ምድብ ነበራቸው ፡-
1-  ፈሪሰ- ትከሻ፡- በሰው ፊት ብቻ ሕጉን ጠባቂ የሚመስሉ፤
2-  ፈሪሰ-ይቅርታ፡- ሕጉን ሲሽሩ ሰው ደካማ ነው በማለት ራሳቸውን ይቅር የሚሉ ፤
3-  ፈሪሰ-ዓይን አፋር፡- ሴት ላለማየት የሚጠነቀቁ ፤
4-  ፈሪሰ-መጻጕዕ፡- አንገታቸውን ስብር አደርገው ከሰው ጋር የሚገናኙ፤
5-  ፈሪሰ-ሚዛን፡- ከእግዚአብሔር ጋር ሂሳብ የሚተሳሰቡ ፤ መልካም ሲሠሩ ከእግዚአብሔር ዘንድ ዕዳ ኖሮባቸው እንደሆነ ያወራርዱታል፤
6-  ፈሪሰ-ፈሪ፡- የእግዚአብሔር ቊጣ ድንገት ቢመጣ እያሉ የሚጨነቁ፤
7-  ፈሪሰ- ፈሪሀ እግዚአብሔር፡- መልካም ቢሠሩ እግዚአብሔር ስለረዳን ነው ብለው የሚያምኑ ሕጉን ለመፈጸም ቢያቅታቸው ደካማነታቸውን የሚያምኑ ናቸው ።
2- ሰዱቃውያን
የካህኑ የሳዶቅ ዘር ነን በማለት ስማቸውን ሰዱቃውያን ወይም ሳዶቃውያን ብለው ሰይመዋል ። እነዚህ ወገኖች በቅንጦት የሚኖሩ ፣ በኢየሩሳሌም አካባቢም ኑሮአቸውን መሥርተው ቤተ መቅደሱን መንከባከብና ማስተዳደር ዋነኛ ሥራቸው ነበር ። ጌታችን በምድር ላይ በነበረበት ዘመን ቊጥራቸው አነስተኛ ቢሆንም በፖለቲካና በሃይማኖት ጉዳይ ተሰሚነታቸው ከፍተኛ ነበር ። ብዙዎቹም ካህናት ነበሩ ። በነበራቸውም ሀብትና ዝና ሊቀ ካህናት ከእነርሱ ወገን ይመረጥ ነበር ። ከፍተኛ ውሳኔ በሚወሰንበት የአይሁድ ሸንጎ ውስጥ የሚበዙት ሰዱቃውያን ሲሆኑ ዝናቸውና ሀብታቸው እንዳይነካ ከሮማውያን ጋር ተስማምተው የሚኖሩ ነበሩ ። ለራሳቸውም ጥቅም ሲሉ በሕዝቡ መካከል ሰላም እንዲኖር ይጥሩ ነበር ። ሀብታሞች በመሆናቸው ድሆችን ይንቁ ነበር ።
ሰዱቃውያን እምነታቸው ፡-
·        በመሢሕ መምጣት አያምኑም ፤
·        በሙታን ትንሣኤ አያምኑም ፤
·        በመጨረሻ ቀን ሰው በፍርድ እንደሚለይ አያምኑም፤
·        በሰው ላይ የሚደርሰው ማንኛውም ነገር በእርሱ ደግና ክፉ ተግባር ላይ ይመሠረታል ይላሉ፤
·        አምስቱን ብሔረ ኦሪት ማለትም ከዘፍጥረት እስከ ዘዳግም ያለውን ብቻ ይቀበላሉ ። ተጽፎ ያልተገኘ አይቀበሉም ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ