የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የቤተ ክርስቲያን ታሪክ

ታሪክ ምንድነው ?
የነገሮች መጀመሪያ በኦሪት ዘፍጥረት ፣ የነገሮች ፍጻሜ በዮሐንስ ራእይ ተገልጧል መጽሐፍ ቅዱስ ፍጥረት ጅማሬና ፍጻሜ እንዳለው ሲናገር ፈጣሪ ግን ጅማሬና ፍጻሜ የሌለው መሆኑን ይናገራል ለሁሉም ነገር ጅማሬና ፍጻሜ የሰጠው እግዚአብሔር ነው ። በጅማሬና በፍጻሜ መካከል ያለው ታሪክ ይባላል ። ብዙ ጊዜ ሲነገር እንደምንሰማው “የታሪክ ባለቤት ሕዝብ ነው” ይባላል ፣ የታሪክ ባለቤት ግን እግዚአብሔር ነው ። በዚህ ዓለም ላይ ታሪክ የሌለው ማንም የለም ። ግለሰቦች ፣ ማኅበራት ፣ ቤተሰብ የራሳቸው የሆነ ታሪክ አላቸው ። በቀደመው ዘመን ወላጆች ለልጆቻቸው የዘር ሐረጋቸውን ጽፈው ይሰጡ ፣ በቃል ያስጠኑ ነበር ። ትልቅም ይሁን ትንሽ ሁሉም ሰው የራሱ ታሪክ እንዳለው ያሳያል ። በርግጥ “የዓለም ታሪክ የጥቂት አባገነኖች ታሪክ ነው” ተብሎ በምሬት ይገለጻል ። ታሪክ ግን የቤተ መንግሥትን ውሎ ማጥኛ ብቻ ሳይሆን በዚያ ዘመን የነበረውን ማኅበራዊ መስተጋብር ፣ ሥልጣኔና የሕዝቡን የአኗኗር ሁኔታ ማንሣት አለበት ። የታሪክ ሙሉ ሥዕል ያለውም በዚህ ነው ።

“ታሪክ ላይ መቆየት አመድ ላይ መንከባለል ነው” ተብሎም ሲነገር ይሰማል ። ታሪክ ለዛሬ ያለውን አስተዋጽዖ ማየት ካልቻልንም አታላይ ሁኖ ዛሬን እንዳንኖር ያደርገናል ። ግሪኮች አሁን ያሉበት የኢኮኖሚ ውድቀት ላይ የደረሱት “መላው አውሮፓ ጫካ በሚኖርበት ዘመን ዲሞክራሲንና ፍልስፍናን ለዓለም ያስጠናን እኛ ነን” በሚል ትምክሕት ስለተቀመጡ ነው ። ታሪክ ቁጭት ፈጥሮ የበለጠ ካላሠራ በርግጥም አመድ ላይ መንከባከብ ነው ። ታሪክን ስናጠና መታወስ ያለበት ነገር ሁላችንም በታሪክ ፊት መሆናችንን ነው። ዛሬም ታሪክ ናት ። እኛም አንድ ቀን ታሪክ እንሆናለን ። በሌላ አገላለጽ የዛሬ ሰው ፣ የነገ ታሪክ ነን ። ትላንት ባጎደሉት የምንወቅሳቸው ባለታሪኮች አሉ ፣ እኛም ካልሠራን ነገ ላይ እንዲህ እንወቀሳለን ማለት ነው ። በርግጥ ታሪኬ እንዲያምር ብሎ የሚሠራ ሰው ተዋናይ እንጂ እውነተኛ አይደለም ። መሥራት ያለብን ለእግዚአብሔር ክብር ፣ ለወገናችን ጥቅምና ለኅሊና እርካታ ብቻ ነው ። ዛሬ የሠራነው ለነገ ተርፎ ታሪክ ከሆነ መልካም ነው ። ሥራችን ግን በእግዚአብሔር ፊት ይታወሳልና ደመወዝን ከእርሱ ብቻ እያሰብን መሥራት ይገባናል ።
“የቤተ ክርስቲያንን ታሪክ የማያነብ ሰው በታሪክ ውስጥ የተፈጸሙትን ስህተቶች ለመድገም የተፈረደበት ነው” ይባላል ። ከታሪክ የማይማር ሰው ከጉዳቱ የሚማር ልፋተኛ ሰው ነው ። የቤተ ክርስቲያንን ታሪክ ማጥናት ለጥቂት ሰዎች የሚያስፈልግ ብቻ ሳይሆን ክርስቲያን የሆነ ሁሉ ሊያውቀው የሚገባ ሐቅ ነው ። ክርስትናን በተከፈለለት ዋጋ ልክ ለመያዝ ታሪክን ማወቅ ያስፈልጋል ። የችግሮችን ምንጭ አውቆ መፍትሔ ለማፈላለግ ታሪክን ማወቅ ወሳኝ ነው ። ታሪክ ትላንትን የምናይበት መስተዋት ነው ። ታሪክን ወደ ኋላ መልሰን ማረም ባንችልም ታሪክ ከጥፋቱም ከልማቱም ጋር የሚጠቅመን ስንማርበት ብቻ ነው ። ትላንት የሌለው ዛሬ ፣ ነገ የሌለውም ዛሬ የለም ። ትላንት የሌለው ዛሬ ዓለምን ዛሬ የጀመረ ያስመስለዋል ። አምባገነኖች የሁሉም ነገር መነሻ እኛ ነን ስለሚሉ ትላንት የሌለውን ዛሬ በመፍጠር የተካኑ ናቸው ። ራሳቸውን እግዜር ስለሚያደርጉም አምባገነኖችና አግም አደጎች ለነገ ታሪክ አይጨነቁም ። ዓለም የምታልፈው እኔ ያልፍኩ ቀን ነው ብለው ያስባሉና ። ዛሬ ታሪክ እናጠናለን ፣ ነገ ታሪክ ሁነን እንጠናለን ። ታሪክ አንድ ታላቅ ተቆጣጣሪ እንዳለው እንረዳለን ፣ እርሱም የዘመናት አምላክ እግዚአብሔር ነው ።
ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ ስለ ታሪክ አጻጻፍ የተናገሩትን ማንሣት ጠቃሚ ነው፡-
1-  ታሪክን መማር ለሰው ሁሉ ይበጃል ። ለቤተ መንግሥት መኰንን ይበልጥ ይበጃል ።
2-  የታሪክ ትምህርት የሚጠቅመው እውነተኛ ሲሆን ነው ይላሉ ። በመቀጠል  እውነተኛ ታሪክ ለመጻፍ ሦስት ነገሮች ያስፈልጋሉ ይላሉ፡-
2.1- ተመልካች ልቡና
2.2- የማያደላ አእምሮ
2.3- የጠራ የቋንቋ አገባብ ።
ነጋድራስን እንዲህ እንዲናገሩ ያደረጋቸው አንዱን ባለ ታሪክ ክንፍ ቀረሽ መልአክ ፣ ሌላውን ጭራቅ አድርጎ የመጻፍ አባዜ ስላለና ስላሳዘናቸው ነው ። ሰው ደግ ብቻ ፣ ሰው ክፉ ብቻም አይደለምና ታሪክ ሚዛናዊ መሆን አለበት ። ወገናዊነት ታሪክን ያበላሻል ። ወገናዊነት ጥላቻን በትውልድ መካከል ይፈጥራል ።
ይቀጥላል
ሐምሌ 2 ቀን 2011 ዓ.ም.
ዲአመ
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ