“በሕይወትህ ዕድሜ ሁሉ ማንም አይቋቋምህም፤ ከሙሴ ጋር እንደ ሆንሁ እንዲሁ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ አልጥልህም፥ አልተውህም።” ኢያ 1፥5 ::
በተራራው ላይ ከነበረው ሙሴ ፣ ከሕዝቡ ጋር የነበረው ኢያሱ ያሳዝን ነበር። ኢያሱ ከሚሊዮን ሕዝብ ጋር ነበረ፣ ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር ነበረ። ኢያሱ ብዙ የሥራ ዘመን አለው፣ ሙሴ ግን ሩጫውን ፈጽሟል። ኢያሱ ለውጊያ ይነቃቃል፣ ሙሴ ግን ጋሻና ጦሩን ሰቅሏል። ኢያሱ በዚህ ወቅት የነበረበት ስሜት ምንድነው? በዚህ ጥቅስ ውስጥ ብቻ የተወሰኑ አሳቦችን ማየት ይቻላል። ኢያሱ ከፀጉር የሚበዙ ጠላቶችን መቁጠር ደክሞት ነበር። ጠላት ብቻ ሳይሆን ጠላቶች ነበሩት። የግሉ ሳይሆን ቤተሰቡንና ሕዝቡን የሚያሳድዱ ጠላቶች ነበሩት። ያለ አገር ሕዝብን መምራት ፣ ያለ እርሻ ያንን ወፈ ሰማይ ለመመገብ ማሰብ በሥጋዊ ዓይን አድካሚ ነው። ጠላቶቹ ስሙን የሚያጠፉ ቀላል ጠላቶች ሳይሆኑ ሕይወትን የሚቀጩ ፣ ያለ አገርና ያለ ህልውና የሚያስቀሩ ነበሩ። እግዚአብሔር የጠላቶቹን ብዛት ፣ የድላቸውን ዘመን አልቆጠረም። “በሕይወትህ ዘመን ሁሉ ማንም አይቋቋምህም” በሚል ኪዳን ምዕራፉን ዘጋው ። ጠላት አይኖርብህም አላለውም፣ አያሸንፉህም አለው እንጂ። ብዙ ሕዝብ ቢከበን በዙሪያችን እንጂ በውስጣችን መሆን አይችልምና የብቸኝነት ስሜት ይኖረናል። በብዙ ውጊያዎች ባለ ድል የሆንበት፣ ብዙ ኒሻን የደረደርንበት ታሪክም ዛሬ ላይ የመኖር አቅም ላይሆነን ይችላል። ብዙዎችን አበርትተን እኛ ግን ድካም ተሰምቶን ይሆናል። ጦርነቱን ለእርሱ፣ ድሉን ለእኛ የሚጽፍ ወዳጅ አለን። የተሸነፈን ጦር ለመማረክ ጀግና መሆን አይጠበቅም። የወደቀን ለመርገጥ ስመ ጥር መሆን አያሻም። አይዟችሁ ይላል የሐዲስ ኪዳኑ ኢያሱ ፣ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ:-
“በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።” ዮሐ. 16:33::
በብዙ ነገሮች ባለ ድል አይደለሁም ፣ ውጥኔ አልተሳካልኝም ፣ ምኞቴ ምኞት ሆኖ ቀረ፣ የበዪ ተመልካች ነኝ ፤ የዕድሜዬ አስኳል፣ የሥራው ጊዜ አለፈ ካላችሁ ፣ ፀሐይን በገባዖን ሰማይ ያቆመ፣ ሠርካችሁን ማለዳ የሚያደርግ ጌታ አለ! ማንም እንዳይቋቋመን አድርጎ የብረት አጥር ይሆንልናል።
የኢያሱ ሁለተኛው ጭንቀት ከሙሴ ጋር የነበረው እግዚአብሔር ከእኔም ጋር ይሆናልን? የሚል ነበረ። የተለያዩ ሰዎች በቅብብሎሽ ሥራውን ቢሠሩትም አሠሪው ግን አንድ እግዚአብሔር ነው። እግዚአብሔር ታሪክን የመራ አምላክ ቢሆንም ታሪክ ላይ የቀረ አምላክ አይደለም። ከሙሴ ጋር የነበረው እግዚአብሔር ከኢያሱ ጋር አለ። ከአባቶቻችን ጋር የነበረው እግዚአብሔር ከእኛ ጋር መኖሩን የምንጠራጠርበት ጊዜ ብዙ ነው ። ሌላው ይቅርና የልጅነታችን አምላክ ዛሬ ገሸሽ ያለን እየመሰለን የልጅነቴ አምላክ ፣ የሕፃንነቴ አፍቃሪ ወዴት ነህ? እንለዋለን። እግዚአብሔር ትቶኛል የሚል ድምፅ በየዘመናቱ ይሰማል። የመተዉ ድምፅ ስሜት ነው፤ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር መሆኑ ግን እውነት ነው። “አምላኬ አምላኬ ስለምን ተውኸኝ?” የሚለው በመስቀል ላይ የተሰማ ድምፅ ነው። የዘመናት የሰው ልጆች ጩኸት በሰማይ መሰማቱን ለማረጋገጥ ጌታ ይህን ድምፅ አሰማ። መለኮቱ ተለይቶት ያሰማው ድምፅ አልነበረም። ሰማይ የጠቆረባቸው ፣ ምድር የከዳቸው፣ ሁሉ የፈረደባቸው፣ ከጲላጦስ እስከ ማልኮስ ፣ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ሁሉ የተነባበረባቸው ምስኪኖች እንዲጽናኑ ፣ የመተዉ ስሜታቸው በክርስቶስ በርኅራኄ እንደ ተሰማ ለመግለጥ ይህ ጩኸት አስተጋባ ። ይህ ጩኸት ዳዊት በቤተ መንግሥት ውስጥ ሆኖ የጮኸው ጩኸት ነው (መዝ 21፥1) ።
“አልጥልህም” የሚለው የተስፋ ቃል አገልጋይ ለነበረው ለኢያሱ ትልቅ የብርታት ድምፅ ነው። አገልጋይ ብዙዎችን አጽናንቶ እርሱ ግን የመጣል ስሜት የሚያሰቃየው ነው። ኢያሱ ሚሊዮን ሕዝብ እንደ ዜጋ፣ እንደ አማኝ፣ እንደ ወታደር ከቦታል። በውስጡ ግን የመጣል ስሜት ያሰቃየዋል። ለመኖር አስፈላጊው ነገር ግብአቱ ሳይሆን የመኖር ዋጋው ነው። ዋጋው ካልመጣለት ቀኑ ጨለማ ነው። ኢያሱ ደክሞኛል ቢል ሕዝቡ የሚለው አንድ ነገር ነው ፦ “እናንተ አገልጋዮች እኛን እያበረታችሁ ደከመን የምትሉት ትውልድን ተስፋ ለማስቆረጥ ነው ወይ? የዛሬ አገልጋዮች ቃላችሁና ኑሮአችሁ የተለያየ ነው ፣ ይህን በነሙሴ አላየንም”የሚል የፍርድ ድምፅ ይሰማል። ኢያሱም:- “ለአንድ ቀን እንኳ ደከመኝ የማለት መብት የለኝም ወይ?” ይላል። በዚህ ዘመን ምንደኛ ፣ ጥቅም ተኮር አገልጋዮች ሲከበሩ ፣ መስቀል የተሸከሙ ግን ተጠልተዋል:: ብርቅዬ እንስሳትን ብናስባቸውም ሄደን አናያቸውም። እውነተኛ አገልጋዮች እንደ ብርቅዬ እንስሳት ይታሰባሉ እንጂ ማንም አይረዳቸውም።
“አልተውህም” ይህ ድምፅ የመተዉ ስሜት ውስጥ ለነበረው ኢያሱ ትልቅ መልስ ነው። እግዚአብሔርም ሰውም ትቶኛል የሚል ብዙ አልቃሾች በምድር ላይ አሉ። በልጆቻቸው፣ በደከሙለት ሕዝብ የተተዉ የመሰላቸው በአስጨናቂ ስሜት ውስጥ ያልፋሉ። አንዳንድ ሰዎች “እኔ የምናገረው የራሴን ነው አልተዋችሁም” ይሉናል። እግዚአብሔርም እኔ የምናገረው የራሴን ነው አልተውህም ይለናል።
ውድ ወገኖቻችን !
ዐርባ ዓመት ተዋግቶ አንድ ዓመት መታገሥ ሲያቅት፣ የበረከቱ መዳረሻ፣ የከነዓን ድንበር ላይ ትጥቅ ሲላላ እግዚአብሔር አልጥልህም፣ አልተውህም ይላችኋል። የጠላት ብዛት እግዚአብሔር ለእኛ ያሰበውን አያስቀርበትም። አሳባችንን የሚረዳ ባይኖር፣ ሁሉ ያደመብን መስሎ ቢሰማን የማይኖር ቀን አልተሰጠንም። ገና ባልመጣው ነገ፣ ባልጨበጥነው ዘመናችን እግዚአብሔር ወዳጃችን ነውና በርቱ!
ለተሰማችሁ የድካም ስሜት ቃለ እግዚአብሔርን ተከታተሉ፣ ጸልዩ፣ የእግዚአብሔር ሰዎችን አግኙ ፣ ሌሎችን አበርቱ ፤ ያቆማችሁትን ሥራ አሁን ጀምሩ ! ያን ጊዜ ራሳችሁን በብርታት ውስጥ ታገኙታላችሁ!
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ነሐሴ 27 ቀን 2016 ዓ.ም.