መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » ማርያም » የተመረጠች እመቤት ማርያም (የመጨረሻው ክፍል)

የትምህርቱ ርዕስ | የተመረጠች እመቤት ማርያም (የመጨረሻው ክፍል)

የተመረጥሽ እመቤት ማርያም ሆይ ! ቃልን ወልደሽ ዝም ማለትሽ ይደንቃል ። እረኞችም ሰብአ ሰገልም ቢመጡ ሁሉንም በተቀደሰ ዝምታ አስተናገድሽ ። እረኛን አልናቅሽም ፣ ሰብአ ሰገልን በተለየ ክብር አላከበርሽም ። እግዚአብሔርን ትወጃለሽና ሁሉን አስተካክሎ መመልከትን መረጥሽ ። የእግዚአብሔር ሰው ሁለት ሚዛን የለውምና ። ሰዎች ስለ ልደቱ ብርሃን ሲያስቡ አንቺ ግን የመስቀሉ ጥላ እየታየሽ አርምሞን ገንዘብ አደረግሽ ። ሞትን የሚያስቡ እንደ ልባቸው አይናገሩም ። በልደቱ ከአሕዛብ ወገን የሚሆኑ ሰብአ ሰገል ተገኙ ፣ በሞቱም ሮማዊው መቶ አለቃ አመነ ። ብዙ የተደረገላቸው አይሁድ ግን አልተገኙም ። ብዙ ያደረጉለት ሰው ፣ ብዙ ያሳጣል ። ትንቢትም ፣ ምልክትም ፣ ምስክርነትም የአይሁድን ልብ መነቅነቅ አልቻለም ። አንቺ ግን ከአይሁድ ወገን ነሽና አይሁድን መራገም ዕዳ ያመጣል ። ለዚህ ዓለም ማመን ፣ ለዚህ ዓለም መሰልጠን እግዚአብሔር በአይሁዳውያን ሠርቷል ። ከሕዝብ ከአሕዛብ ቢወለድ ጠሉት ፣ ለሕዝብ ለአሕዛብ ቢሰቀል ናቁት ። እግዚአብሔር የእኛ ብቻ ይሁን ብለው የሃይማኖት ዘረኛ ሆኑ ። በዚህም ከእግዚአብሔር ተለያዩ ። የልጅሽ መወለድ ለመላእክት ዝማሬ ብቻ ሳይሆን ጥቅምም ነው ።

የተመረጥሽ እመቤት ማርያም ሆይ ! ቅዱሳን መላእክት የፍቅር ሠራዊት ናቸውና በአዳም መዳን ደስ ተሰኝተዋል ። ደግሞም የአምላካቸውን ፊት ለማየት ጓጉተዋልና የአምስት ሺህ ዓመት ናፍቆታቸው ተፈጽሞ ፣ አምላክ በሚታይ ሥጋ ሲገለጥ ቤተ ልሔምን ሁለተኛ ሰማይ አደረጓት ። ደግሞም ያለ ሰው መዳን መንግሥተ ሰማያትን አይወርሱምና ለክብር ከፍታ ፣ ግዕዛን ላላቸው ፍጥረታት የተዘጋጀውን ርስት ለመውረስ የክርስቶስን መወለድ ይናፍቁ ነበር (1ጴጥ. 1 ፡ 12) ። በልደቱ አጠገብ አንቺና ዮሴፍ ነበራችሁ ፣ በመስቀሉ አጠገብም አንቺና ዮሐንስ ነበራችሁ ። የዓለሙ ሁሉ ፈጣሪ በልደቱና በሞቱ ታማኝ ወዳጅ አንቺን አገኘ ። በመጀመሪያው ምጽአቱ ኮከብ እየመራ ሰብአ ሰገልን አደረሳቸው ፣ በዳግም ምጽአቱ ከዋክብት ይረግፋሉ ።

የተመረጥሽ እመቤት ማርያም ሆይ ! ያልተማሩ እረኞችና ሁሉንም አናውቅም የሚሉ ጠቢባን በልደቱ ተገኙ ። በልደቱ የተጋበዙት ብቁዎች ሳይሆኑ ፣ ራሳቸውን በልክ ያዩ ትሑታን ናቸው ። እርሱ ወደ ነገሥታት ቤት አልሄደም ፣ ነገሥታት ግን ያለበት ድረስ መጡ ። በዚህም የነገሥታትን ቤት ደጅ እንዳይጠኑ ፣ የመኳንንትም አጫዋች እንዳይሆኑ አገልጋዮችን መከረ ። ሕይወት ቀድሞ ሞት ይከተላል ፣ ይህ የዚህ ዓለም ሥርዓቱ ነው ። በክርስቶስ ግን ሞቱ ቀድሞ ሕይወቱ ተከተለ ። በሕይወቱ ካዳናቸው በሞቱ የተቤዣቸው በለጡ ። በሕይወቱ ኢየሩሳሌምን ፣ በሞቱ ዓለምን ተቤዠ ። ለግሪክ ጠቢባን ሞት መጨረሻቸው ነበር ። ለክርስቶስ ግን የአገልግሎቱ መጀመሪያ ሆነ ። በልደቱ ቀን ሞቱ መነገሩ ሞቱ ቀድሞ ሕይወቱ ተከተለ ። ሞቱ ቀድሞ ትንሣኤው ለዘላለም አበራ ።

የተመረጥሽ እመቤት ማርያም ሆይ ! ዓለም ሁሉ ክርስቶስ በታሪክ የነበረ መሆኑን ፣ የሰቀሉትም እነርሱ እንደ ገደሉት ያምናሉ ። ደግ እንደ ነበር ብዙዎች ይናገራሉ ። ደግ የሆነ እርሱ የባሕርይ አምላክ እንደሆነ ተናግሯል ። “እኔና አብ አንድ ነን” ብሏል ። ደግ ማለት እውነት የሚናገር ነው ። ደግ ከሆነ ፣ ሁሉም በደግነቱ ካመኑበት ፣ ደጉ ክርስቶስ አምላክ ነኝ ሲል መቀበል አለባቸው ። ድንግል የሁሉ ናት ። ሕፃንም የሁሉ ነው ። በዓለም ላይ ያሉ ሰዎች ደናግልን ይጠብቃሉ ፣ ሕፃንም የእገሌ ነው አይባልም ። ድንግል ሆይ የሁሉ እናት ነሽ ። ልጅሽም የሁሉ ጌታ ነውና በሕፃን መልክ ተገለጠ ። በእርሱ የማያምኑ ዕድላቸውን ባዶ ነው ። አዳም ከጎኑ ያለ እናት ሔዋንን አስገኘ ፣ አንቺ ያለ አባት ክርስቶስን ወለድሽ ። ሴቶች ሁሉ ስሙንና ጾታውን የማያውቁትን ልጅ ይፀንሳሉ ። አንቺ ግን ስሙንም ፣ ፆታውንም የምታውቂውን ፀነስሽ ። ስሙም ኢየሱስ ይባላል ። ከዘላለም በሥላሴ መንግሥት የተሰየመ ፣ በቅዱስ ገብርኤል ላንቺ የተገለጠ ድንቅ ስም ነው ።

የተመረጥሽ እመቤት ማርያም ሆይ ! ሔዋን በገነት ወደቀች ። አንቺ ግን በምድር ላይ በሃይማኖት ጸናሽ ። ሔዋን የቀዳማዊ አዳም እንቅፋት ሆነች ፣ አንቺ ግን የዳግማዊ አዳም አገልጋይ ሆንሽ ። አዳም ጌትነትን ሽቶ ወደቀ ፣ ክርስቶስ በትሑት ሥጋ ተገልጦ አዳነ ። ከፍታን የሚመርጡ ይዋረዳሉ ። መጨረሻው ላይ የቆሙ ያላቸው መንገድ ወደ መጀመሪያው መውረድ ነው ። አዳምም ወደ መጣበት አፈር ተመለሰ ። ጽርሐ አርያምን በጉልበት ተመኘ ፣ መኖሪያው መቃብር ሆነ ። የዘላለም ተራሮችን ያቋረጡ እግሮች መሄድ የማይችሉ የሕፃን አእጋር ሁነው ተገለጡ ። አዳምን የሠሩ እጆች በሠሩት ፍጥረት ተገፉ ። ለድሆች አንደበት የሆነው ፣ ሄሮድስ ሲያሳድደው ዱዳ ሕፃን ሁኖ ተሰደደ ። በበጉ ራስ ላይ ሊቀ ካህኑ እጁን ይጭናል ። አሁን ግን በጉም ካህኑም ራሱ የሆነው ክርስቶስ በፈቃዱ ሊሞት ከድንግል ተወለደ ። በግ ሁኖ የመጣው ክርስቶስ በበጎች ማደሪያ በበረት ተወለደ ። እረኛው ለእረኞች ተገለጠ ። የነገሥታት ንጉሥ የሚገባውን ስግደት ከሰብአ ሰገል ተቀበለ ። የሴት ልጅ መባል ስድብ ነበረ ፣ እርሱ ግን የሴት ዘር ተብሎ መጣ ። በዓለም ላይ ያለ አባት ያደገ እንጂ ያለ አባት የተገኘ ልጅ የለም ። ክርስቶስ ብቻ የሴት ዘር ሁኖ መጣ ። ክርስቶስ በምድር ላይ የሴት ዘር ተብሎ ፣ በአባታቸው የተጠሩትን ኃያላን አሸነፈ ።

አንቺን የመረጠ አንድ አብ ቡሩክ ነው ፣
አንቺን የወደደ አንድ ወልድ ቡሩክ ነው ፣
አንቺን ያከበረ አንድ መንፈስ ቅዱስ ቡሩክ ነው !

ስለ ልደቱ የተናገርነው ምሥጢር ተፈጸመ ።
ስለ ሰማችሁን እግዚአብሔር ይስማችሁ !

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥር 9 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ

አዳዲስ መጻሕፍት

ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ

ለምድራችንና ለአገልግሎታችን በረከት የሆነ መጽሐፍ
የመጀመሪያ እትም ጥቅምት 2016 ዓ.ም

1ኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ – ክፍል አንድ

የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 2013 ዓ.ም

ምክር አዘል መጽሐፍ

የመጀመሪያ እትም