የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የተመኘነውን ሳይሆን የጀመርነውን ባርክልን

“የሰማይ አምላክ ያከናውንልናል፥ እኛም ባሪያዎቹ ተነሥተን እንሠራለን” ነህ. 2፡20
ሰው ቢያስብም መፈጸም ባንተ ነው ። አሳብም መፈጸምም ባንተ ነው ። ሰው ሺህ ቢመክር ግቡን የሚመታው አንተ ካለህበት ነው ። ብዙ ጅምር ጥቂት ፍጻሜ ባላት አገሬ እባክህን መከናወንን ስጠን ። በአገሬ የገባው ክፉ መውጫ አጥቶ ይንሰራፋል ፣ መልካሙ ግን ዕድሜው አጥሮ ትዝታ ይሆናል ። ከሌላው የተቀበልነውን ክፉ ያቀበሉን ቢተውት እንኳ እኛ አንተወዉም ፣ መልካሙን ግን ለመርሳት ፈጣን ነን ። ደጎች ሲጠቁ ይህች ዓለም ለደግ አትሆንም እንላለን እንጂ ለፍትሕ አንጮኽም ፣ ክፉዎች ሲያጠቁ ግን እናዜምላቸዋለን ። የሃምሳ ዓመት ዕድሜ ያለው ጅምር እየጠፋ ሁልጊዜ ፈርሰን የምንሠራ ነን ። ዓለም የተፈጠረው እኔ ስወልድ ነው የሚል ብዙ ወገን እያፈራን ነው ። እባክህን ነገ እንዳይጠፋን ትላንትን ማሰብ ስጠን ። ዛሬ እንዳያልፈን በነገ ብቻ መመኘትን አርቅልን ።
በባዕድ ምድር ላይ ፣ አገር አልባ ሁነው ፣ የፈረሰችውን ኢየሩሳሌም እያሰቡ የሰማይ አምላክ ያከናውንልናል እያሉ እንደ ተነሡ እንደ ነህምያና የእምነት ጓዶቹ አበርታን ። አገር እያለን ስደተኞች ፣ ጸጋ እያለን ተመጽዋቾች የምንሆንበት ዘመን ያብቃ ። ራሳችንን በጦር የምንወጋበት ፣ አካላችንን ከፍለን ሁለት ቤት የምናደርግበት ስቃይ ይቁም ። ስለ ድንበር የለሽ ግንኙነት እያወራን ፣ ዓለም አቀፍ ርእስ ይዘን በሰፈር የተለያየነውን፣ የምንኖረውና የምናወራው የተለያየውን እኛን ይቅር በለን ። የፈጠርከው የሰው ልጅ ስለ ተፈጥሮ በተመስጦ በሚያጠናበት ጊዜ እኛ ገና ጭቃ እናቦካለን ፣ የወንድማችንን መልክም በምናቦካው ጭቃ እናቆሽሻለን ። ጌታ ሆይ አንገት የደፉ አዋቂዎች ፣ የተሸማቀቁ እውነተኞች ቀና የሚሉበት ዘመን ይምጣ ። የክፉዎችና የሐሰተኞች ዘመን ያብቃ ። አንተ የሰማይ አምላክ ታከናውንልናለህና ተነሥተን እንድንሠራ እባክህ እርዳን ። ተቀምጠን የምንመኝ ፣ ሳንነቃነቅ አሳብ የምንሰጥ ነንና ከዚህ የምኞት ጀግንነት አውጣን ። አንተ እርምጃን ትባርካለህ ፣ የተዘራንም ታሳድጋለህ ። የሰማይ አምላክ ያከናውንልናል ፣ እኛም ባሪያዎቹ ተቀምጠን እንመኛለን የምንለውን ምስኪኖች እባክህ አስበን ። 

መንገድ ሰጥተኸን መንገድ የምንፈልግ ፣ ሁሉን ሰጥተኸን ምንም እንደሌለን የምንፋጠጥ ነንና ዓይነ ልቡናችንን አብራልን ። አገራችን ሰው ፣ ሰው በመሆኑ ብቻ የሚከበርባት ምድር ትሁንልን ። ሽማግሌ በምድሩ አብቀልልን ። የእርስ በርስ ዕድር ለዚህ ካደረሰን ላቅ ብለው የሚመክሩንን እባክህ አሥነሳልን ። የምናፍረው ፣ በፍቅር የምንፈራው ሰው አብዛልን ። እርስ በርስ ቁመት ከመለካካት በትሕትና እውቀትን መፈለግ ይሁንልን ። የምታውቀውን ማንነታችንን ነገርንህ ። ላንተ መንገር ኑዛዜ ነውና ይቅር በለን ። አገራችንን በመልካም አስብልን ። ተነሣን ስንል ከሚያስቀምጠን ፣ ቀና አልን ስንል ከሚሰብረን ነገር ለዘላለሙ ፍታን ። ሥልጣን ያንተ ነውና ለዘላለሙ አሜን ።

ያጋሩ