የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የተሰበረ ልብ

“የተሰበረ እጅ ሊሠራ ይችላል ፣ የተሰበረ ልብ ግን ከቶ አይችልም ።” /ፐርሺያን/

የልብ ስብራት በተለያየ መንገድ ይመጣል ። የመጀመሪያው ተስፋ በማጣት ሲሆን ሁለተኛው በንስሐ ስሜት ነው ። በንስሐ ልብ የሚመጣው የተሰበረ ልብ እነቅዱስ ዳዊትም አግኝተውታል ። በንስሐ መንፈስ የሚመጣው የተሰበረ ልብ ቅዱስ ኀዘንን የሚወልድ ነው ። ይህ ቅዱስ ኀዘንም ያለፈውን በደል የሚያጥብ ፣ ለሚመጣው የቅድስና ዝግጅት የሚያደርግ ነው ። ይህ የንስሐ ልብ የበደሉትን መካስ ፣ የቀሙትን መመለስ ያለበት ነው ። ይህ የንስሐ ልብ የዓለምን ከንቱነት ተረድቶ ሰማይን መናፈቅ ነው ። ይህ የንስሐ ልብ በበደል ቍራኛ ፣ በኃጢአት እስራት ፣ በሱስ ባርነት ላሉት ወገኖች የሚያለቅስ ነው ። ይህ የንስሐ ልብ ገነትን ከማጣት በላይ እግዚአብሔርን ማጣት ከባድ መሆኑን ተረድቶ ለፍቅረ እግዚአብሔር የሚያነባ ነው ። በንስሐ ልባቸው የተሰበረ የደስታ ዘይትን ይቀባሉ ።

የልብ ስብራት ተስፋን የሚያሳጣ ከሆነ ከቅዱስ ኀዘን ውጭ ነው ። ይህ የልብ ስብራት በማያቋርጥ ኀዘን ውስጥ ማለፍ ፣ ትካዜን ጓደኛ እንባን ቀለብ ማድረግ ፣ የመሸነፍ ስሜት ፣ የአልኖርም ባይነት ድምፅ ፣ በገዛ መብት መፍራት ፣ በሰዎች ይሁንታ ሕይወት ትቀጥላለች ብሎ ማሰብ ፣ ያለንን ብዙ ሳይሆን የጎደለንን ጥቂት መቍጠር ፣ ሁሉን ትቶ ለመሄድ መሰናዳት ፣ የዓመቱን በዕለት ለመናድ መፍቀድ ፣ የእኔ ጉዳይ ሳይሆን አብዛኛውን ነገር የራሱ ጉዳይ ብሎ መተው ፣ የሾፌር ወንበር ላይ ተቀምጦ መሪውን መልቀቅ ፣ ተጨማሪ ኀዘን እንጂ ደስታን ላለመስማት መጣር ፣ በቀትር ጨለማ ፣ በብርሃን ጽልመት ውስጥ ማለፍ ፣ አይነጋም በሚል ስሜት መወጠር … ነው ። በዚህ ስሜት ውስጥ የሚያልፍ ሰው ሆደ ባሻነት ያጠቃዋል ። ለማልቀስ ገለልተኛ ስፍራ ይፈልጋል ። አትንኩኝ ባይ ስስ ይሆናል ። በትንሽ ነገር ይከፋል ። ቃላትን መቆርጠም ፣ አማርኛን መሰንጠቅ ይጀምራል ። ድሮ ለቀልድ የሚናገሩትን ነገር አሁን የጠብ ርእስ ያደርገዋል ። ሁሉም ሰው በሰላም እየኖረ እኔ ብቻ ተጎድቻለሁ ይላል ። ሰማይ ያደመበት ፣ እግዚአብሔርም ትቶት የሄደ ይመስለዋል ። ስሜቱ ተለዋዋጭ ነው ። በትንሽ ምክር ወደ ራሱ ይመለሳል ። መልሶ ችግሬ የሚለውን ነገር ያስባል ። ችግር ያለው ነገር በትክክል ችግር መሆኑን መገንዘብ ያቅተዋል ። እንቅፋት ሲመታው ድንጋዩን እንደ ደመኛው ያየዋል ። ከፍጥረት ጋር ይጋጫል ። ዝናቡም ፀሐዩም ያበሳጨዋል ።

የተሰበረ ልብ በተለያየ መንገድ ይመጣል ። ብዙ ለፍቶ ጥቂት ማትረፍ ባለመቻል ፣ ሰዎችን ከልብ ቀርቦ የአፍ ምላሽ ብቻ በማግኘት ፣ ተለዋዋጭ ሰዎችንና ተነዋዋጭ ዓለምን መታገሥ ባለመቻል ፣ ሰዎች በሀብታቸውና በሥልጣናቸው ተመክተው በሚናገሩት ትርፍ ንግግር ፣ በከንቱ ነገር ተመክተው በሚለፈልፉ እግዚአብሔር የለሾች ፣ ያለውን መልክና አቅም በማጣቱ ምክንያት ፣ አጽናኝ ሁሉ አቍሳይ ሲሆንበት ፣ ዙሪያው ገደል ፣ መንገድ ሁሉ እሾህ ሲመስለው ፣ የጸሎቱ መልስ ሲዘገይና ጠላቶቹ የበለጡት ሁኖ ሲታየው ፣ የበሽታ ስሜት ሲጫነውና ለራሱ ማልቀስ ሲጀምር … የልብ ስብራት ይመጣል ።

የልብ ስብራት ገለልተኛ ያደርጋል ። መሸነፉንና ማልቀሱን ሰዎች ያወቁበት ከመሰለው ተጨማሪ ኀዘን ይገጥመዋል ። የልብ ስብራት ረጅም ልቅሶ ነው ። ስለዚህ ያደክማል ። እንባም ያልቃልና ኀዘኑ የፍግ እሳት ሁኖ ውስጥ ውስጡን ይበላዋል ። ሥራውን መሥራት እየተሳነው ይመጣል ። የሚታየው ራእዩ ሳይሆን ጥቁር መጋረጃ ነው ። ሰዎችን በጣም ተቀያሚ ይሆናል ። ፍቅር የሚሰጡትን ሰዎችም ማመንና መቀበል ይቸግረዋል ። ግብታዊ ውሳኔ ይወስናል ። ሁሉም ነገር ድብልቅልቅ ቢል እያለ ይመኛል ። መሰልቸቱ እያየለ ይመጣና ዓላማውን በምስር ወጥ መሸጥ ይጀምራል ። እግዚአብሔርን ስለሚቀየም መጸለይ ይሳነዋል ።

የልብ ስብራት ባልታሰበ ሰዓት ሊመጣ ይችላል ። የሚወዱትን ድንገት ሲያጡ ቀና ያለው አንገታቸው ዘንበል የሚል አያሌ ናቸው ። ተቀጣጣይ ችግሮችም ወደ ልብ ስብራት ያደርሳሉ ። ትንንሽ ችግሮች በጊዜው ካልተፈቱ ትልቅ ይሆናሉ ። ከልብ ስብራት ለመውጣት በወዳጅነቱ ወደ ጸናው እግዚአብሔር መመልከት ይገባል ። እግዚአብሔር የባረካቸውን ደጋግ ሰዎችንም ማግኘትና መተንፈስ አስፈላጊ ነው ። አሳብ ቢበታተንም መጸለይ ፣ ካሉበት አካባቢ ዞር ለማለት መሞከር ፣ የቅዱስ መንፈስን እርዳታ መለመን ፣ “የእግዚአብሔር መንፈስ ሆይ የመቆም አቅም ሁነኝ” ብሎ መማለድ ይገባል ። ከሁሉ በላይ የበደልንበት ነገር ካለ ንስሐ መግባት ፣ የጌታችንን አማናዊ ሥጋና ደም መቀበል ያስፈልጋል ።

እስከ መጨረሻው ቀን ድረስ መኖር ይገባል ። ከቀኑ በፊት በተስፋ ቢስነት መሞት አይገባም ። እጃችንን የሰበሩት ልባችንን እንዲሰብሩት መፍቀድ የለብንም ። አዎ ፋርሳውያን እንዲህ ይላሉ፡- “የተሰበረ እጅ ሊሠራ ይችላል ፣ የተሰበረ ልብ ግን ከቶ አይችልም ።”

ከልብ ስብራት ውጡ ፣ በጨለማው ላይ ይብራ ያለው እግዚአብሔር በልባችሁ ላይ ያብራ !

የብርሃን ጠብታ 21

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ኅዳር 2 ቀን 2014 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ