የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የተሸፈነ ክህደት

“እነርሱም፦ አንቺ ቤተ ልሔም ፥ የይሁዳ ምድር ፥ ከይሁዳ ገዢዎች ከቶ አታንሽም ፤ ሕዝቤን እስራኤልን የሚጠብቅ መስፍን ከአንቺ ይወጣልና ተብሎ በነቢይ እንዲህ ተጽፎአልና በይሁዳ ቤተ ልሔም ነው አሉት ።” ማቴ. 2፡5-6 ።
ይህንን ትንቢት ከነቢዩ ሚክያስ ጠቅሰው ለሄሮድስ የነገሩት የካህናት አለቆችና ጻፎች ናቸው ። ሄሮድስ ክርስቶስ የት እንደሚወለድ የጠየቃቸው መሢሑን ለማግኘት ናፍቆ አይደለም ፣ መንግሥቴን የሚቀናቀን መጣብኝ ብሎ ነው ። የካህናት አለቆችና ጻፎችም ትንቢት ጠቅሰው መናገራቸው ሄሮድስ እንዲያምንና እንዲቀበል አይደለም ። እርሱም መንግሥቱን የዘላለም አድርጎት እየደነበረ ነው ፣ እነርሱም መጻሕፍትን ማወቅ ሥራቸው አድርገውት እየተናገሩ ነው ። የሚጠይቀው ሄሮድስ እውነትን እየፈለገ አይደለም ፣ በተቃራኒው እውነትን ለመግደል እያሰበ ነው ። በዚህም ጥያቄ የሚጠይቁ ሁሉ የእውነት ረሀብ ያለባቸው ሰዎች አይደሉም እንድንል ያደርገናል ። ጥያቄ የሚጠይቁ እውነተኛ ጠያቂዎች ከሆኑ መልሱ ሲነገራቸው ያርፋሉ ። መልሱ ካላሳረፋቸው ጥያቄው አልገባቸውም ፣ ወይም ጥያቄ የላቸውም ፤ አሊያም ጥያቄው በውስጡ ተንኮል ያዘለ ነው ። እንዲህ ዓይነት ሄሮድሳዊ መንፈስ በየዘመናቱ ሲያውክ ኑሯል ።
የካህናት አለቆች የመጽሐፍ ክፍል ፣ ትንቢትና ምሳሌን በደንብ ያውቃሉ ። ያንንም ይናገራሉ ። ነገር ግን መንፈሳዊ ጥማት የላቸውም ። ተግባራቸውን እንደ ሥራ እንጂ እንደ አገልግሎት አያዩትም ነበር ። ለሚጠይቁአቸው መልስ ይሰጣሉ ፣ ዓላማቸው ግን ሰዎች በመልሱ እንዲያርፉና እንዲድኑ አልነበረም ። እነርሱም እንጀራ የመብላት እንጂ የማረፍ አሳብ የላቸውም ። ስሜት አልባና ሙት መንፈስ ይዞ መጻሕፍትን መተረክ በጣም ከባድ ነው ። እንዲህ ያለው ማንነት የሰዎችን መዳን የማይናፍቅ ፣ የራሱን የክብር ቦታ የሚያስጠብቅ ነው ። በእግዚአብሔር ቤት ለሚያልፍ ዓለም ብቻ መኖር መክሰር ነው ። ሕይወት የሌለው ደረቅ ንባብም ሌሎችን አያድንም ። ምክንያቱም ሄሮድስ ጥቅሱን ከሰማ በኋላ ነፍሰ ገዳይ ሆነ እንጂ አልተለወጠም ። የእግዚአብሔርን ቃል በምን መንፈስ እንናገራለን ? በምን መንፈስ እንሰማለን ? ብለን ራሳችንን መጠየቅ ያስፈልጋል ። ባለ ማስተዋል መናገር ለአጥፊዎች የጥፋት ካርታን በእጃቸው ማስጨበጥ ነው ። ጌታችን፡- “በእግራቸው እንዳይረግጡት ተመልሰውም እንዳይነክሱአችሁ ፥ የተቀደሰውን ለውሾች አትስጡ ፥ ዕንቁዎቻችሁንም በእሪያዎች ፊት አትጣሉ” ያለው ለዚህ ነው /ማቴ. 7፡6/ ። ባለ ማስተዋል መስማትም ነፍሰ ገዳይ የሚያደርግ ነው ። ለዚህም ጥቅስ እየጠቀሱ የሚሳደቡና የሚገድሉ ሰዎችን ማሰብ በቂ ነው ። የእግዚአብሔርን ቤት እንደ ምድራዊ ርስት ብቻ ይዞ መቀመጥ አሳዳጅና ነፍሰ ገዳይ ያደርጋል ።
የሚገርመው ሄሮድስ በምንም መንፈስ ይጠይቅ የካህናት አለቆች ግን ደግመው ስለ ጉዳዩ ማሰብ አልፈለጉም ። ጌታችን በምድር ሹሞች ሁለት ጊዜ ያህል ማለትም በልደቱና በስቅለቱ ተፈተነ ። አማኝ ነን በሚሉ የካህናት አለቆች ግን ዘመኑን በሙሉ ተሞገተ ። በእምነት ካባ ውስጥ ያለ ከሃዲነት በቀላሉ አይድንም።
አቤቱ ወደ አንተ መልሰን እኛም እንመለሳለን ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ