ጌታችን በተጠመቀ ጊዜ ሰማይ ተከፈተ ፣ መንፈስ ቅዱስ ወረደ ። ሰማይ በሰው ላይ ተዘግቶ ነበር። ወደ ተዘጋ ሰማይ ብዙ ጸሎት ቀረበ ፣ ብዙ መሥዋዕት ዐረገ ፤ ድኅነት ግን ሊመጣ አልቻለም ። አሁን ሰማይ ተከፈተ ፣ ሰማይ በተከፈተበት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የሚያርገው ጸሎት ግዳጅ የሚፈጽም ፣ ስርየት የሚያሰጥ ነው ። ሰማይ ሲከፈት “ልጆቼ” የሚል የፍቅር ድምፅ ይሰማል ፣ በእናንተ ደስ ይለኛል የሚል መልእክት ይመጣል ። በነቢዩ፡- “እግዚአብሔር በሕዝቡ ተደስቶአልና” ይላል (መዝ. 149 ፡ 3)። አባት ልጆቹን ሲያይ ፣ ንጉሥ ሕዝቡን ሲያይ ደስ ይለዋል ። እግዚአብሔርም እኛን ሲያይ ደስ ይለዋል ። ውሉደ እግዚአብሔር ፣ ሕዝበ እግዚአብሔር ነን ። እርሱም ሰማያዊ አባት ፣ ዘላለማዊ ንጉሥ ነው ። የንጉሥ ልጅ አባቱን እየወደደ ያከብረዋል ፣ እያከበረ ይወደዋል ። በዚህ ዓለም ላይ “ደምበኛ ንጉሥ ነው” የሚሉን የጉርሻና የገበያ ፍቅረኞች አሉን ። በዚህ ዓለም ላይ ቢልዬ እያሉ የቢል ወጪአቸውን ስለምንጋራ የሚወዱን ይኖራል ። በእውነት የሚወደን “ልጆቼ” ብሎ የሚጠራን ግን አንድ አለ ። እርሱም እግዚአብሔር ነው ። ለመሞታችን ሳይሆን ላስቀረነው ጥቅም የሚያለቅሱ ሊኖሩ ይችላሉ ። እግዚአብሔር ግን ለሞታችን ያዝናል ፣ ለውድቀታችንም ትንሣኤን አዘጋጅቷል ።
ብዙዎችን ያሳዘንን ፣ እናት አባትን ሳይቀር ያስለቀስን ፣ በፍቅር የቀረቡንን በብልጠት የተወዳጀን ፣ የሚጠብቁንን መምህራን አንገት ያስደፋን ልንሆን እንችላለን ። በእኛ የሚያዝን እንጂ የሚደሰት ላይኖር ይችላል ። እግዚአብሔር ግን መጀመሪያ በህልውናችን ደስ ይለዋል ፣ ቀጥሎ በመመለሳችን ደስ ይለዋል ። እንደ ገናም በቃሉ በመኖራችን ደስ ይለዋል ። ዮርዳኖስ እግዚአብሔር ሰውን በልጅነት ፍቅር የሚፈልግበት ፣ በእኛ ለመደሰት የሻተበት ነው ። ሺህ መሥዋዕቶች ደስ አያሰኙትም ። የተሰበረ ልብ ፣ እርሱን በማፍቀር የሚደረግ አገልግሎት ግን ደስ ይለዋል ። ሰው እንኳ ሲጋብዘን “ከፍትፍቱ ፊቱ” እንላለን ። እግዚአብሔርም ከስጦታችን በፊት እኛን ይፈልገናል ።
መቼ ነው ፣ ኧረ መቼ ነው ጌታዬ ፤
እንደ ቃልህ የሚሆን ጉዞዬ ።
አበባ ሲታሽ ይሸታል ፣ ሽቱ ሲሰበር ያውዳል ፣ ብርቱካን ሲጨመቅ ያረካል ። ሰውም የንስሐ መንፈስ ሲኖረው መንፈሳዊ ውበትን ያገኛል ። የሰውን መልክ የሚጎዳው ንስሐን የሚጠላው ትዕቢቱ ነው ።
የጠቆረ ሰማይ ፣ የተዘጋ አርያም ብዙዎችን ቀና እንዳይሉ አድርጓል ። ዛሬ ግን ሰማይ ተከፍቷል ። መንገደ ሰማይ በንጉሥ ተመርቆ ተከፍቷል ። በንጉሥ ተመርቆ የተከፈተ መንገድ ለመንገደኛ ሁሉ ክፍት ነው ። ጌታ በትሕትና ወደ ዮርዳኖስ በሄደ ጊዜ ሰማይ ተከፈተ ። አዳም በትዕቢቱ የገነትን በር ዘጋ ። በትዕቢት የተዘጋ ሰማይ በትሕትና ይከፈታል ። እውነተኛ ትሕትናም ስህተትን አምኖ ከሰው ጋር በይቅርታ ፣ ከእግዚአብሔር ጋር በንስሐ መታረቅ ነው ። “መንፈሴ በሥጋ ለባሽ ላይ አይኖርም” ተብሎ ነበር ። ደግሞ “ሥጋ በለበስ ሁሉ ላይ ከመንፈስ አፈስሳለሁ” ብሎ ተስፋ ሰጥቶ ነበር ። መንፈስ ቅዱስ በአምሳለ ርግብ በመውረድ ርግማን መነሣቱ ፣ ተስፋ መፈጸሙ ተረጋገጠ ። መንፈስ ቅዱስ የሰላምና የደኅንነት ምልክት በሆነች በርግብ አምሳል ወረደ ። በዚህም አካል ያለው መሆኑ ታወቀ ። ሉቃስ ወንጌላዊ፡- “መንፈስ ቅዱስም በአካል መልክ እንደ ርግብ በእርሱ ላይ ወረደ፤” ብሏል (ሉቃ. 3 ፡ 22) ። ኖኅ በውኃ ላይ ተንሳፎ ነበር ። የጥፋት ውኃ መጕደሉን ያወቀው ርግብ የወይራ ቀንበጥ ይዛ በመጣች ጊዜ ነው ። መንፈስ ቅዱስም ሞተ ባሕር ፣ ፈለገ እሳት መጉደሉን ሊያበሥር በአምሳለ ርግብ ወረደ ።
ዓለም ሰላምን ከጦርነት ስትፈልግ ኖራለች ። ጦርነት አንዱን ገድሎ ሌላውን የማሳረፍ ጊዜያዊ ሙከራ ነው ። ሰላም የጦርነት ውጤት አይደለም ። በጦርነት የሚገኝ ሰላም ያሸነፍነው አቅም እስኪያገኝ ብቻ የሚቆይ ነው ። ሰላም እግዚአብሔርን የማወቅ ውጤት ነው ። አስቂኞች ፣ መድኃኒቶች ፣ ሱሶች ፣ መሪዎች የሚሰጡት ሰላም ይኖራል ። ጊዜያዊ ማደንዘዣ ነው ። እውነተኛ ሰላም የሚገኘው ከእግዚአብሔር ብቻ ነው ። ዓለም የእግዚአብሔርን ሰላም ይፈልጋል፣ እግዚአብሔርን ግን አይፈልግም ።
ላለፈው አንድ ወር በጥምቀት ዙሪያ ሲጻፍ የነበረው ተፈጸመ !
እግዚአብሔር በብርሃኑ ይባርካችሁ !
የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም.
ዲ/ አሸናፊ መኰንን