“በበጎ ፈቃዱ እንደ ወደደ ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ለእርሱ ልጆች ልንሆን አስቀድሞ ወሰነን ።” ኤፌ. 1 ፡ 5 ።
እስካሁን ያለነው ቍጥር 5 ላይ ነው ። እግዚአብሔር እኛ ለመፍጠር ፣ እኛ ለማዳንና በልጅነት ጸጋ ለመቀበል ያስገደደው ነገር የለም ። የራሱ ፍቅር ግድ አለው እንጂ ። በራሱ ስለወደደን በእኛ አልጠላንም ። አስገድዶ ግን አያጸድቀንም ። በረከቱ ከእርሱ ሲሆን የመቀበያው እጅ ግን የእኛ ነው ። ቁም ነገራችን አስገደደው እንዳንል ገና ሳንፈጠር ወደደን ። ስለ ፍቅራችን ሞተ እንዳንል ጠላቶቹ ሳለን ነፍሱን ሰጠን ። እርሱ ንጉሥ ሳለ በባሪያ ወግ አልፈጠረንም ። መልኩን ፣ ጠባዩን የምንካፈል ፣ ርስቱን የምንወርስ ልጆቹ አድርጎ ፈጠረን እንጂ ። ወላጆቻችን እኛን እንደሚወልዱ አያውቁም ነበር ። የይሁዳ እናት ይሁዳን እንደምትወልድ ብታውቅ ኖሮ አትወልደውም ነበር ። እግዚአብሔር ግን ይሁዳን አውቆት እንዲወለድ አደረገው ። ወላጆች በቁማቸው ንብረታቸውን ለማውረስ ይቸገራሉ ። ሲሞቱ ግን ልጆች እንዲወርሱ ይናዘዛሉ ። እግዚአብሔር ግን ሞት የሌለበት ሳለ መንግሥቱን ያወረሰን ትልቅ አባታችን ነው ።
ዳግም ልደት ብለን ስንናገር ዳግም ያሰኘውን ሁለት ነገሮች ማንሣት እንችላለን ። ቀዳሚ በሌለበት ዳግም አይባልምና ። የመጀመሪያው አዳም ሲፈጠር የልጅነት ሀብት አግኝቶ ነበር ። ከሀብታት ሁሉ የልጅነት ሀብት ወይም ሀብተ ወልድና ስመ ክርስትና ይበልጣል ። ሌሎች ሀብታት ሁሉ የሚገኙት በዚህ ምክንያት ነውና ። የልጅነት ሀብት ከምድራውያን አማንያን ፣ ከሰማያውያን ቅዱሳን ጋር ቤተሰብ የሚያደርገን ነው ። እግዚአብሔር ሥራውን በእኛ የሚጀምረው በልጅነት ነው ። አዳም ግን ይህን ሲፈጠር በንፍሐተ መንፈስ ቅዱስ ያገኘውን ልጅነት በበደል ምክንያት አጎሳቆለው ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ራሱን ቤዛ አድርጎ በመስጠቱ ይህ ልጅነት ተመለሰ ። የእግዚአብሔር መንፈስ ሳይሆን የእግዚአብሔር ልጅ ሥጋ መልበሱ ልጅነታችንን ለመመለስ ማሰቡን የሚያሳይ ነው ። በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ልጆቹ የሆንበት ምሥጢር ዳግም ልደት ተብሎ ይጠራል ። በቀዳማዊ አዳም ቀዳማዊ ልጅነትን ስናጣ በዳግማዊ አዳም በክርስቶስ ዳግም ልደትን አገኘን ። እርሱ ከአብ ያለ እናት ከድንግል ያለ አባት በመወለዱ ሁለት ልደታትን ገንዘብ አድርጓል ። ሁለት ልደትን ገንዘብ ያደረገው ለዳግም ልደት አበቃን ።
ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ብቻ ሳይሆን የእግዚአብሔር መንግሥት አማናዊት ጥላ ወደምትሆን ቤተ ክርስቲያን የምንገባው በዳግም ልደት ወይም በመጠመቅ ነው ። ዳግም ልደት የሚያሰኘው ሁለተኛው አመክንዮ ከእናት ከአባታችን ተወልደን ይህን ዓለም ያየንበት ጸጋ እንደ ቀዳማዊ ልደት ይቆጠርና ከውኃውና ከመንፈሱ የተወለድንበት መንፈሳዊ ልደት ደግሞ ዳግም ልደት ይሰኛል ። ለመወለድ ሁለት ነገሮች መተባበራቸው ግድ ነው ። እንዲሁም በመንፈሳዊ ዓለም ከማኅፀነ ዮርዳኖስ ፣ ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ እንወለዳለን ። በሥጋ ተወልደን ይህን ዓለም እንዳየን ፣ በመንፈስ ተወልደን መንፈሳዊውን ዓለም እናያለን ። /የበለጠ ለመረዳት “ኒቆዲሞስ” የተሰኘውን የዲያቆን አሸናፊ መኰንን መጽሐፍ ያንብቡ ።/
የእግዚአብሔር አሳቡ ከልካይ ፣ ተጋፊ ፣ ሻሪ የለውም ። ስለዚህ አስቀድሞ ለልጅነት አስቦን ሳለ ከባሪያ እንኳ አንሰን ተገኘን ። ስለ ተፈጠርን እንኳ መገዛት ሲገባን ስለ ተወደድንና ልጆች ስለሆንም መታዘዝ አቃተን ። በዚህ ምክንያት በዳግም ልደት ልጆቹ የምንሆንበትን መንገድ አዘጋጀ ። እግዚአብሔር እኛን ለማዳን አስቦ አልቀረም ። በመስቀል ላይ በመሞት ፍቅሩን ገለጠልን ። አሳብ ወደ ተግባር ካልተለወጠ ሰውን ማዳን እንደማይቻል አስተማረን ። ወደ ተግባር ሲለወጥ ደግሞ ዝቅ ማለት ፣ መሰቀልና መሞት ያስፈልጋል ። ብዙ አሳብ አለኝ እያሉ ስለ ራእያቸው የሚናገሩ ሰዎች አሉ ። የማይታየው አምላክ የሚታይ ሥጋ የለበሰው ረቂቁ አሳብ መግዘፍ ስላለበት ነው ። የአሳብ ቸርነት ለችግረኛ ጥርኝ ውኃ አይወጣውም ። የአሳብ ፍልሚያ ምርኮኛውንና የኃጢአት ባሪያ የሆነውን የሰው ልጅ ነጻ አያወጣውም ። ከሺህ አሳብ አንድ ተግባር ሕይወት ትለውጣለች ። ጉዞ እስካልተጀመረ ሁሉም ነገር ሩቅ ነው ። ያየነው የሚታየን መንገድ ስንጀምር ነው ። እግዚአብሔር ሰውን ከአፈር ፈጥሮ ልጁ አደረገው ። ሰው ለራሱ ሰው ፣ ለእግዚአብሔር ልጅ ሆነ ። ጭቃን ልጄ ያለ አምላክ ቡሩክ ነው ። ጭቃ የሆነውን ኃጢአት የሚያላቁጡትን አንሥተን ልጄ ማለት ዛሬ የቀረልን ጸጋ ነው ። የሰው ሕይወት ሲለወጥ ከማየት የበለጠ ደስታ የለም ።
ከቤተሰቦቻችን ስንወለድ አናውቃቸውም ፣ አናምናቸውም ፣ አንወዳቸውም ነበር ። ሁሉም ነገር ከእነርሱ ሆኖ ቆይቶ አወቅናቸው ፣ አመናቸው ፣ ወደድናቸው ። እንዲሁም በልጅነታችን ብንጠመቅም ኑሮአችን በቤቱ ነውና እግዚአብሔርን እያወቅነው ፣ እያመነው ፣ እየወደድነው እንመጣለን ። ሰይጣን እንኳ በማለዳ መግባት አስፈላጊ መሆኑን አውቆት ከመጠመቁ በፊት ለእኔ ልጃችሁን ስጡኝ የሚላቸው ወገኖች አሉ ። ልጆቻቸውን ወደ ጥምቀት ያላቀረቡ ፣ በጠዋት እንዲገቡ ያላደረጉ እስከ ማታ ሊያጡአቸው ይችላሉ ። ደግሞ ክርስቶስ የሞተውና የተነሣው ለሕፃናትም ነው ። የክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ መመስከሪያ የሆነው ጥምቀትም ለሕፃናት ይገባል ።
የኤፌሶን መልእክት ትርጓሜ /11
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
የካቲት 17 ቀን 2014 ዓ.ም.
እባካችሁ ለሌሎች አካፍሉት