“ፊተኛ ኑሮአችሁን እያሰባችሁ እንደሚያታልል ምኞት የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው አስወግዱ ፥ በአእምሮአችሁም መንፈስ ታደሱ፥ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ ።” ኤፌ. 4 ፡ 22-24 ።
“የወደቅህበትን ሳይሆን የተንሸራተትህበትን ቦታ ተመልከት” ይባላል ። መውደቂያው መጨረሻው ነው ። መነሻው ግን የተንሸራተቱበት ቦታ ነው ። መንሸራተት አቋምን ፣ አቋቋምን ፣ ጥንካሬን ፣ ጽናትን ፣ ድልን ፣ ክብርን መልቀቅ ነው ። ሰው የወደቀው የተንሸራተተ ጊዜ ነው ። አቋሙን የቆሙ ለመሰሉ ሰዎች አሳልፎ ከሰጠ ፣ በጸጋ ሳይሆን በባለጸጋ እንደሚኖር ካሰበ ፣ የሰበከውን እውነት ከካደ ፣ ለመሰከረው ሐቅ ይቅርታ ከጠየቀ ፣ ከብዙኃኑ ላለመለየት ሰግዶ ከኖረ ፣ እውነታን በአሉታ ከለወጠ ተንሸራቷል ፣ ግቡም ውድቀት ብቻ ነው ። መንሸራተቻውን ካወቅን ውድቀቱን መተመን አያቅተንም ። ከውድቀቱ ለመነሣትም የተንሸራተተበትን ቦታ ማየት አለበት ። ሲገላበጡ መኖር ግን ለቂጣ እንጂ ለሰው አይመጥንም ። ስህተትን አርሞ ትክክለኛ ቦታ ላይ መቆም ግን የሰውነት መገለጫ ፣ የመኖር ዋጋ ነው ። የምንኖረው ለማልማት ብቻ ሳይሆን ያጠፋነውንም ለማስተካከል ነው ። ኑሮ የትላንት አጨዳ ፣ የነገ ዘር ያለበት ነው ።
ብዙ ሰው ስለ ትላንቱ ሲያስብ ጤነኛ አስተሳሰብ አይሰማውም ። የትላንቱን ላለ ማሰብም ራሱን በሱስ ውስጥ ይደብቃል ። እርሳስ ከላዩ ላጲስ አለው ። ሰው ሲጽፍ ይሳሳታል ተብሎ ባይገመት ኖሮ ላጲስ አይሠራም ነበር ። ሰው የሰውን መሳሳት ካወቀ ሁሉን የሚያውቀው አምላክ የበለጠ ያውቃል ፣ ይራራልም ። የስህተቱ ላጲስም ንስሐ ይባላል ። በትላንቱ ኖሮ እስረኛ መሆን አይገባም ። እገሌ ምሥጢሬን እንዳያወጣብኝ እያሉ ዘላለም ባሪያ ከመሆን ስህተትን አምኖ መመለስ የተሻለ ነው ። ሰውን በስህተቱ ለመግዛት የሚፈልጉ የዲያብሎስ የውስጥ ካድሬዎች አሉ ። ጥፋቱም ልማቱም የባለቤቱ ጉዳይ በመሆኑ መፍራት አይገባውም ። በዚህ ዓለም ላይ የሚያስፈራን እግዚአብሔር ብቻ ሊሆን ይገባዋል ። በትላንት ስህተት እየተሰቃዩ መኖር ዕለት ዕለት ራስን መመረዝ ነው ። ሺህ ሞት ማለት በትላንቱ ስህተት ራስን መቅጣት ነው ። ትልቁ ቅጣት ከደረጃ መውረዳችን ነው ። ራስን በራስ መቅጣት ግን ፍትሐ እግዚአብሔርን መጋፋት ፣ ለስርየት የፈሰሰውን የክርስቶስን ደም ችላ ማለት ነው ። ትላንት ያልበደለ ጻድቅ ፣ ነገ የማይቀደስ ኃጥእ የለም ። የትላንቱን ግን መማሪያ ማድረግ ተገቢ ነው ። ስህተት ለብልሆች የሚማሩበት የተግባር ትምህርት ቤት ነው ።
የትላንት ስህተቶች በአብዛኛው ያለ ማወቅ ውጤቶች ናቸው ። አለማወቅ ዲያብሎስ የሚገዛበት ትልቅ ግዛቱ ነው ። እርሱ የጨለማው ገዥ ነው ሲባል የማታ ገዥ ማለት አይደለም ። አደንቁሮ የሚገዛ ማለት ነው ። አለማወቅ ውስጥ ሁልጊዜ መታለል አለ ። ሔዋን በመታለል ቀዳሚ ነበረች ። እግዚአብሔርን በሙሉነት አላወቀችውም ነበር ። በመከልከሉ ውስጥ ፍቅሩን እንደሚገልጥ አላስተዋለችም ። የምንወደው ሰው የሚከለክለን ነገር ካለ ባይገባንም መታዘዝ መልካም ነው ። ሔዋንም ለምን ሳትል ብትታዘዝ የሞት በር አትሆንም ነበር ። ትእዛዙን ከአዳም ስለሰማችው የአዳም ቃል አደረገችው ። አዳም ግን ከእግዚአብሔር ስለሰማ ይፈራ ነበር ። ሔዋንን ላለማስቀየም ሲል በላ ። እግዚአብሔርን ያስወጡበት ፍቅር እርስ በርስ የሚካሰሱበት ሆነ ። ለመፋቀርም ፣ ተጣልቶ ለመታረቅም እግዚአብሔር ያስፈልጋል ። ትላንት ባለማወቅ ምክንያት የበሽታ እራት ፣ የጓደኞች መጫወቻ ሆነን ይሆናል ። ያንን አያሰብን ከዳግም ውድቀት መታቀብ ይገባናል ። ትላንት ከተማሩበት አልከሰሩበትም ። አባቶች ካህናት ቀብር ላይ ሲጸልዩ፡- “የሞቱትን ነፍስ ይማርልን ፣ ከዳግም ኀዘን ይጠብቀን” ይላሉ ። ለሞትንበት ዘመን ምሕረት ፣ ለዛሬው ዘመን ከዳግም ውድቀትና ኀዘን መትረፍ ይገባናል ።
ሰው ከበደል በፊት አንድ ነበረ ። ስሙም “አዲሱ” ነበረ ። ሁልጊዜ እየታደሰ የሚኖር ፍጡር ነበር ። ከበደል በኋላ ግን “አሮጌው” ተባለ ። እርጅና የነበረንን ውበትና አቅም ማጣት ነው ። ኃጢአትም መንፈሳዊ ውበትንና የአምልኮ አቅምን ይጎዳልና አሮጌ ሰው ያደርጋል ። አሮጌውን ፊት ለማስወገድ የሚሠሩ ፣ አሮጌውን የቆዳ ሸካራ በማንሣት ለስላሳነትን የሚጎናጸፉ አሉ ። ታዲያ ፀጉሩ ሲቆረጥ ፣ ጥፍሩ ሲላጥ ይቀበራል ። አሮጌውን ሰው ለማስወገድ ሕመም አለው ። ውበት ከሕመም ነጻ አይደለምና ። ሴቶች ፀጉር ሲሠሩ በእሳት ወይንም በሚያምም ሹሩባ ነው ። አሮጌውን ሰው ለማስወገድም ለሚያምም ሥርዓት መገዛት ግድ ይላል ። ማስወገድ ይገባል ። ቆፍሮ መቅበር ፣ ገለል ማድረግ ሳይሆን ማስወገድ ያስፈልጋል ። ሰው በመለወጡ ውስጥ የራሱ ድርሻ አለው ። በፈቃዳችን ያዳነን በፈቃዳችን ይቀድሰናልና ። አሊያ ዕቃ የሚያስውብ አምላክ የለንም ።
በአእምሮ መንፈስ መታደስ ደስ ይላል ። አዲስ እውቀትና አዲስ ደስታን ወደ ሕይወት መጋበዝ ነው ። ብዙ ሰው ራሱን ማደስ ሲያቅተው ሃይማኖትን አድሳለሁ ይላል ። ራስን በቅድስና ማደስ ይገባል ። ሕይወታችንን የምንጠብቀው በመታደስ ነው ። የአዲሱ ሰው መልክ ጽድቅ ቅድስናና እውቀት ነው ። አዳም የተፈጠረው ከዚህ ውበት ጋር ነው ። ወደ ጥንተ ተፈጥሮ እንድንመለስ ክርስቶስ ቤዛችን ፣ መንፈስ ቅዱስ ቀዳሻችን ሁኗል ። ንስሐ መግባት ፣ ወደ ክርስቶስ ሥጋና ደም መቅረብ ይገባናል ። መለወጥ እፈልጋለሁ ግን ቆይ የሚል ሰው መለወጥ አይፈልግም ። ለትላንት ብናረፍድም ለነገ ግን አላረፈድንም ። የትላንት ሥራ ዛሬ ከያዘን ፣ የዛሬ ተግባርም ለነገ ስንቅ ይሆነናል ።
ንጹሕ የምስጋና መሥዋዕት ፣ የማይፈጸም ውዳሴ ለገናናው እግዚአብሔር ይሁን !
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ኅዳር 5 ቀን 2014 ዓ.ም.