የዲ/ን አሸናፊ መኰንን ገጽ….. እሁድ ሚያዝያ ፬/፳፻፯ ዓ.ም
የዳግም ትንሣኤ በዓል በአብዛኛው የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ተከታዮች ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ካለው ጥልቅ መንፈሳዊ መልእክትና ድባብ ባሻገር በዋናነት ጎልቶ የሚታወቅበት ማኅበራዊ ፋይዳው ነው፡፡ ይኸውም በዚህ ዕለት አበ ልጆች፣ ቤተሰቦች፣ ዘመድ አዝማዶችና ወዳጆች በተለምዶ የአክፋይ በመያዝ የሚጠያየቁበትና ማኅበራዊ ግንኙነታቸውን ተጠናክሮ እንዲቀጥል መልካም አጋጣሚን የሚፈጥሩበት ዕለት ነው፡፡ የትንሣኤው ሰሞን የሠርጉ ግርግርና ሞቅታውም ሳይረሳ ማለት ነው፡፡
ዳግም ትንሣኤን ምክንያት አድርጎ ወዳጅ ከወዳጅ፣ ዘመድ ከዘመዱ፣ ቤተሰቦችና ጓደኛሞች መገናኘታቸውና መጠያየቃቸው ማኅበራዊ ትስስራችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየላላና እየፈራረሰ ላለብን ለእኛና ለሕዝባችን ቢያንስ በቋፍ ያለውን አብሮ የመብላት፣ ያለንን ተካፍለን በፍቅርና በሰላም ደስ ብሎን መኖር የምንችልበትን የቀደሙት ትውልዶች ያቆዩልንን ማኅበራዊ ትስስር የሚያድስ ስለሆነ ልናበረታታውና ተጠናክሮ እንዲቀጥልም የምንፈልገው ብቻ ሳይሆን እንድንተገብረው የሚገባን ቤተ ክርስቲያናችን ያቆየችልን መልካም የማኅበራዊ ኑሮ ሥርዓት እንደሆነ እገረ መንገዳችንን ለማስገንዘብ እንወዳለን፡፡
ይሁን እንጂ የዳግም ትንሣኤ በዓል ከዚህ ከላይ ካነሳነው ማኅበራዊው ፋይዳው በላቀ የክርስትናችን መሠረትና ዋልታ የሆነውን የጌታችንና የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤን በፍቅር መታዘዝ በሆነ እምነት የምንናገርበትና ለሰዎች ሁሉ የምናውጅበት አዲስ ቀናችን ነው፡፡ መጽሐፍ ለሕይወት የተሰጠንን የኢየሱስ ክርስቶስን ቅዱስ ሥጋውን በበላችሁ፣ ክቡር ደሙንም በጠጣችሁ ጊዜ ሞቱንና ትንሤኤውን ትመሰክራለችሁ እንዳለን፣ እኛም ዘወትር በቅዳሴያችን ጊዜ እንዲህ እንደምንል፡-
አሜን፣ አሜን፣ አሜን፣ ነአምን ወንትአመን፡፡ ይእዜኒ እግዚኦ እንዘ ንዜክር ሞተከ ወትንሣኤከ ንትአመነከ፡፡ ንዜኑ ሞተከ እግዚኦ ወትንሣኤከ ቅድስተ ነአምን ዕርገተከ ወዳግመ ምጽአትከ፣ ንሴብሐከ ወንትአመነከ ንስእለከ ወናስተበቁዐከ ኦ እግዚእነ ወአምላክነ፡፡
አሜን፣ አሜን፣ አሜን፣ እናምናለን፤ እንታመንማለን፡፡ አቤቱ አሁንም ሞትህንና ትንሣኤህን እያሰብን እናምንሃለን፡፡ አቤቱ ሞትህንና ቅድስት ትንሣኤህን እንናገራለን፣ ዕርገትህንና ዳግመኛ መምጣትህንም እናምናለን፡፡ እናመሰግንሃለን፣ እናምንሃለንም ጌታችንና አምላከችን ሆይ እንለምንሃለን፣ እንማልድሃለንም፡፡
እንደ ቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት ዳግም ትንሣኤ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከትንሣኤው በኋላ በተዘጋ ደጅ በደቀ መዛሙርቱ መካከል ተገኝቶ «ሰላም ለእናንተ ይሁን!» ብሎ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ ውስጥ ለነበሩ ተከታዮቹ ሰላምን ያወጀበትና በዚህ ቀንም ጌታችን ከሙታን ከተነሳ በኋላ ለሐዋርያቱ ሲገለጽላቸው በሥፍራው ላልነበረው ዲዲሞስ ቶማስ ጌታችን ድንቅ የሆነውን ትንሣኤውን የገለጸበትን ዕለት የምናስብበት መታሰቢያ ቀን ነው፡፡
አስቀድሞ በመጽሐፍ ስለ እርሱ እንደተጻፈው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ከተነሳ በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ለደቀ መዛሙርቱና በተለይም ደግሞ ከትንሣኤው በኋላ መነሳቱን በወሬ ብቻ ለሰማውና በሐዋርያቱ ለተነገረው ለቶማስና አብረውት ለነበሩ ሌሎቹም ሐዋርያት ባሉበት «ሰላም ለእናንተ ይሁን!» በማለት ተገለጸላቸው፡፡ ወንጌላዊው ዮሐንስ በወንጌሉ እንደጻፈለን፡- ሌሎቹም ደቀ መዛሙርት ቶማስን ጌታን አይተነዋል አሉት፣ እርሱ ግን፡- የችንካሩን ምልክት በእጆቹ ካላየሁ ጣቴንም በችንካሩ ካላገባሁ፣ እጄንም በጎኑ ካላገባሁ አላምንም አላቸው፡፡ (ዮሐ 20፣24-25)
እናም ሐዋርያው ዮሐንስ እንደሚነግረን፡- «ከስምንት ቀን በኋላ ደቀ መዛሙርቱና ቶማስ በአንድነት በተሰበሰቡበት ፣ ደጆች ተዘግተው ሳለ ኢየሱስ መጣ በመካከላቸውም ቆሞ፡- «ሰላም ለእናንተ ይሁን» አላቸው፡፡ ከዚያም በኋላ ቶማስን፡- «ጣትህን ወደዚህ አምጣና እጆቼን እይ፣ እጅህንም አምጣና በጎኔ አግባው፣ ያመንህ እንጂ ያላመንህ አትሁን አለው፡፡» (ዮሐ 20፣ 25-29)፡፡ ኢየሱስ ቶማስ በወደደውና በፈለገው መንገድ አይቶ በተጨባጭም መንገድ አረጋግጦ ትንሣኤውን ይመሰክር ዘንድ ፈቀደለት፡፡ እናም በተቸነከሩ እጆቹና ጎኖቹ እጁን ያሰገባ ዘንድ አልከለከለውም፡፡
የቶማስ የእምነት አቋም ማመን ለእኔ በመስማት ሳይሆን፣ በዓይኔ አይቼ፣ እንደውም ማየትም ብቻ ሳይሆን ከመስማትም ከማየትም ውጪ ደግሞ ጆሮዬ የሰማውን፣ ዓይኖቼ ያዩትን እውነት በእጆቼ ዳስሼና ነክቼ ነው የሚል ዓይነት ነው፡፡ እናም በጭራሽ የጌታውን ትንሣኤ በመስማትና በማየት ብቻ አምኖ ላለመቀበል የቆረጠ ይመስላል ተጠራጣሪው ቶማስ፡፡ ምናልባት ቶማስ በዘመናችን እንዳሉት የዓለማችን ጠቢባንና ሳይንቲስት «ማየት ማመን ነው!» በሚል ብቻ ላይ የቆመ የእምነት አቋም ብቻ የነበረው ሰው አልነበረም፣ ከማየትም ድንበር አልፎ ጨብጦና ዳሶ ማመን የሚፈልግ ሰው እንጂ፡፡
ልዑለ ባሕርይ ክርስቶስ ኢየሱስም ይህን የቶማስን የእምነት አቋሙን አልናቀም በሚወደውና በሚፈቅደው መንገድ አይቶ፣ ዳሶና ጨብጦ ትንሣኤውን አረጋግጦ ያምንበት ዘንድ በፍቅር እና በርኅራኄ በመልካሚቱ እጁ ዘንድ ተወው፡፡ ቶማስም በማመንና ባለማመን ማዕበል ውስጥ ሆኖ እየዋዠቀ ዳግመኛ በፍቅር በቆሰሉ በጌታችን በተወጋ ጎኖቹና በችንካሮቹ ውስጥ እጁን ለማስገባት አላመነታም፡፡ እናም እጁን ሰደደ… ከዳሰሰው ጌታ ዘንድም በፍቅር የሆነ የእምነት ኃይል መላው እርሱነቱን ነዘረው… እናም በታላቅ ድምጽ ጌታዬ አምላኬም ሲል ጮኸ ቶማስ፡፡
ዛሬ እንደ አዲስ በዘመናችን የሰለጠነው «ማየት ማመን ነው!» የሚለው የምድራችን ጠቢባንና ሳይንቲስቶች ፍልስፍና በቶማስ እና በቶማሳውያኑ ዘንድ ብዙም ወኃ የሚያነሳ አይመስልም፡፡ ምክንያቱም ለቶማስና ለቶማሳውያን ለማመን ከመስማትና ከማየት በላይ ያዩትን በደንብ ጨብጦ፣ ዳሶ በማረጋገጥ እንጂ እንዲሁ በማየት ብቻ ማመን እንዲህ እንደ ዋዛ የሚቀበሉት ነገር አለመሆኑን የተገለጸበት የቶማስውያኑ አቋም ለዚህ ለዛሬው ትውልድም የሚያስተላልፈው መልእክት፣ የሚነግረን ትልቅ ቁም ነገር አለው፡፡
የዘመናችን ጥበብና ፍልስፍናም፡- «እምነት ከመስማት ነው መስማትም ከእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡» (ሮሜ 10፣17)፡፡ ከሚለው ሕያውና የእውነት ቃል አንጻር በተቃራኒ የቆመ ስለሆነ ብዙዎች ቅዱስ ቃሉ ሰለ እርሱ ስለ ጌታችንና አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ የሚናገረውን ለመስማት፣ ሰምቶም አምኖ ለመቀበል ይቸገራሉ፡፡ ጌታ ግን የተነገራቸውን የእውነትና የጽድቅ ቃል ሰምተው በሰሙትም ቅዱስ ቃል በፍቅር በሆነ መታዘዝ በእምነት ዓይን የሚያዩትን እንዲህ ሲል በምስጋና ቃል ተናግሮላቸዋል፡- «ሳያዩ የሚያምኑ ብጹዓን ናቸው፡፡» (ዮሐ 20፣29)፡፡
አዎን ይህ ቃል የተነገረው ለእኛም ነው፣ የወንጌሉን የምሥራች ሰምተን በእግዚአብሔር ሕያው ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ ላመንን፤ ክርስትና በኢየሩሳሌም ገና በሁለት እግሩ ሳይቆም በእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ክርስትናን በጃንደረባው አማካኝነት የተቀበለችው ሀገራችን ኢትዮጵያ በሐዋርያት ሥራ እንደተጻፈለት ጃንደረባው ከኢየሩሳሌም መሳለም ጉዞው መልስ በኋላ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መከራ፣ ሕማም፣ መከራና ሞት በእርሱ ቁስል ስለመፈወሳችን ስለ በደላችንም ስለመድቀቁ የሚናገረውን የኢሳይያስ መጽሐፍ ስለማን እንደሚናገር ባይገባውም፣ ባያስተውለውም ዝም ብሎ በሰረገላው ላይ ሆኖ ያነብ ነበር፡፡
የእግዚአብሔር መንፈስ ፊልጶስን ወደዚህ ኢትዮጵያዊ ሰው ቀርቦ እንዲያነጋግረው ሲመራውና ፊልጶስም ከሚያነበው ከኢሳይያስ መጽሐፍ ጀምሮ ሙሴ በሕግ መጻሕፍት ነቢያትም በትንቢታቸው ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ የተናገሩትን ከመጀመሪያው ጀምሮ በተረጎመለት ጊዜ የሰማውን አምኖ ተቀበለ እናም በመጨረሻ እንዲህ ሲል መሰከረ፡- «እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ አምናለሁ ከመጠመቅስ የሚከለክለኝ ምንድነው…» ባለ ጊዜ ፊሊጶስም፡- «በፍጹም ልብህ ብታምን ተፈቅዶልሃል በማለት አጠመቀው፣ በልቡም ደስ ብሎት መንገዱን ሄደ ይለናል…፡፡ ሐኪሙና ታሪክ ጸሐፊው ወንጌላዊው ሉቃስ፡፡ (ሐዋ 8፣26-40)፡፡
ዛሬም እኛ ስለ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጽሐፍ የተጻፈውንና የሰማነውን አምነን በመቀበል ከብፁዓን ጎራ እንሰለፍ ዘንድ የጌታችን ሞቱን ትንሣኤውንና ዳግም ምጽአቱን በመናገር የቀደሙ የእምነት አርበኞች አባቶቻችንን ልንመስላቸው ይገባል፡፡ በጭንቀትና በሁከት ውስጥ ያለችው ዓለም ሁሉ ስለ ሰው ሁሉ ልጆች ኃጢአት ሲል የሞተውን በሦስተኛው ቀን ሞትን ድል አድርጎ የተነሳውን ሕይወት፣ ትንሣኤና ሰላም የሆነውን የኢየሱሰስ ክርስቶስን የምስራቹን ዜና ወንጌሉን ልትሰማ ይገባታል፣ ጊዜውም አሁን ነው፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች በጻፈላቸው መልእክቱ ይበልጥ ለማወቅ እስከ ሞት ድረስ የተመኘው የትንሣኤውን ኃይል ለማወቅ እንደሆነ ይናገራል። «… እርሱንና የትንሣኤውን ኃይል እንዳውቅ በመከራውም እንድካፈል ወደሙታንም ትንሣኤ ልደርስ ቢሆንልኝ በሞቱ እንድመስለው እመኛለው፡፡» ፊል 3፡11፡፡ የእውነተኛ የእግዚአብሔር ባሪያዎች ጥማት ይህ ነው። መከራውን ለመካፈልና የትንሣኤውን ኃይል ለማወቅ። ዓለም ከተፈጠረበት ዳግመኛም ከሚያልፍበት ኃይል ይልቅ የትንሣኤው ኃይል ልዩ ነው፡፡ ይህ ዓለም ሰይጣንና ሞት የተሸነፉበት ነውና፡፡ ዛሬስ ያለን የእግዚአብሔር አገልጋዮች ምኞታችን ምን ይሆን? ለብዙዎች ትንሣኤ ዝክር (መታሰቢያ) እንጂ ዛሬም በሕይወታቸው የሚሠራ ኃይል መሆኑን አያውቁም፡፡ ስለዚህ እንደ ጳውሎስ ይህን ለማወቅ መናፈቅ ይገባናል። መጽሐፍም ሲወቅስ «የአምልኮ መልክ አላቸው ኃይሉን ግን ክደዋል ይላል፡፡» 2ጢሞ 3፡5፡፡
ትንሣኤው ከአምልኮ ሥርዓት በዘለቀ ትልቅ የሆነ መንፈሳዊ ፋይዳ አለው፡፡ ዛሬም ከሞተ ማንነትና ሥራ ነጻ የሚያወጣ የእግዚአብሔር ኃይል ነው፡፡ «አንተ የምትተኛ ንቃ፣ ከሙታንም ተነሣ፡፡ ክርስቶስም ያበራልሃል፡፡» ኤፌ 5፣14፡፡ እንግዲህ ትንሣኤውን ስናስብ ኃይሉን በማወቅና በመረዳት ሊሆን ይገባል፡፡ ከተቀመጥንበትም ሆነ ከተኛንበት እንዲሁም ለሞት ካንቀላፋንበት ማንነታችን የሚያነሳንና ታጥቀን እርሱን ለማገልገል የሚያበቃን የትንሣኤው ኃይል ነው፡፡
በፍቅር ለይኩን
በፍቅር ለይኩን
የትንሣኤው ኃይል ከሁላችን ጋር ይሁን!