የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የትውልድ መጠጊያ

“አቤቱ ፥ አንተ ለትውልድ ሁሉ መጠጊያ ሆንህልን።”
መዝ. 89 ፡ 1 ።

ከግብጽ ሕዝቡን እየመሩ የወጡት ሙሴና አሮን ናቸው ። በምድረ በዳ የተወለደው ትውልድ ስለ ግብጽም ስለ ከነዓንም አያውቅም ። በግብጽ የነበረውን መከራ በከነዓን ያለውን ደስታ ከመስማት ውጭ አልኖረውም ፣ ለመስማትም ትዕግሥት ያለው አይመስልም ። ከሚሊየን በላይ የሚሆነው ሕዝብ በሲና በረሃ ረግፎ ቀርቷል ። ወደ ከነዓን የሚገቡት ሁለት ሰዎች ኢያሱና ካሌብ ብቻ ናቸው ። በበረሃ የተወለደው ያ ትውልድ የመጨረሻ ትልቁ ዕድሜ 39 ዓመት የሞላው ፣ ከአርባ ዓመት በታች ነው ። በበረሃ የተወለደው ትውልድ በግብጽ የነበረውን ጡብን በደም ማቡካት አያውቀውም ። ለአንዲት ቁራሽ እንጀራ ቀኑን በሙሉ በጽኑ ሥራ መሰቃየትን ሲሰማውም ሊያምነውም አልቻለም ። በምድረ በዳ የተወለደው ያ ትውልድ በተአምራት በልቶ የሚያድር ነበር ። እንኳን ሊያርስ የእርሻ ቦታን አይቶ አያውቅም ነበር ። ያለፋበትንና ያልደከመበትን መና ከቤቱ ደጃፍ ላይ ያገኝ ነበር ። ታማኙ እግዚአብሔር ያለ እርሻና ጎተራ ፣ ያለ ኩሽና ይመግበው ነበር ። በመግቦቱ የማይታማው አምላክ ይመግባቸዋል ፣ የእነርሱ ሥራ እግዚአብሔርን ማምለክ ነበር ።

አገር የሌለው አገር ለማግኘት የሚጓዘው ፣ ያልጎደለበት ነገር ግን የሚወርሰውን ማርና ወተት የምታፈሰውን ምድር የሚሰማ ነበር ። በመከራ ያለፉት ወላጆቹ ነበሩ ። የእያንዳንዱን ቀን ቁርስ ለመብላት የዓመት ልፋት በየዕለቱ የሚለፉት ፣ በነጻነት ወጥቶ መግባት የተነፈጉት ፣ ልጆችን ወልደው ማሳደግ የተከለከሉት አባትና እናቱ ነበሩ ። ያ መካከል ላይ ነዋሪ ፣ በግብጽና በከነዓን መሐል የተገኘው ወጣት ግን በተአምራት የሚኖር ነበር ። ስላለፈው መከራ ለመስማት አይፈልግም ነበር ። አላየውም ፣ ደግሞም ጎድሎበት አያውቅምና የረሀብን ምንነት ለማወቅ መዝገበ ቃላት ያገላብጥ ነበር ። ከነዓን አይናፍቀውም ። ከከነዓን በተሻለ ቁጭ ብሎ ይበላልና ።

እንዲህ ያለ ትውልድ ብዙ አገራት ገጥሟቸዋል ። በቻይና ፣ በሕንድ ፣ በደቡብ ኮሪያ ፣ በጃፓን ፣ በራሽያ ፣ በአውሮፓ ፣ ከፊል በኢትዮጵያ ይህ ትውልድ እየመጣ ነው ። የምድረ በዳው ትውልድ ፣ በተአምራት የሚኖረው ትውልድ የብዙ አገራት ሥጋት እየሆነ ነው ። ስላለፈው መከራ ሲወራ እርሱን ለማሳቀቅ ተብሎ የተፈጠረ አስፈራሪ ፊልም አድርጎ ይመለከተዋል ። ደግሞም “የእኔ ችግር አይደለም ፣ ለምን ይነግሩኛል?” ብሎ በልቡ ይታዘባል ። የወላጆቹ መከራ ካለፈ ምናልባት የሠላሳ ዓመት ዕድሜ ያለው ሊሆን ይችላል ። እርሱ ግን “ሊያሳድጉኝ ካልቻሉ ለምን ወለዱኝ” ብሎ ራሱን ያዋድዳል ። ስላለፈው መከራ መስማት የማይፈልግ ፣ ስለ ነገ ተስፋም መፈንደቅ የማይችል ትውልድ የምድረ በዳው ትውልድ ነው ። ለአገሩ ቁጭት ፣ ለወገኑ ክብር ያጣ ፣ ጥቅሙን ጣዖት አድርጎ የሚያመልክ ፣ “ምን እሰጣለሁ ?” ሳይሆን “ምን አገኛለሁ?” በሚል ስሌት የሚጓዝ ፣ ትንሽ እንቅፋት ከገጠመው አማራጩ መሞት የሆነ ምስኪን ትውልድ እየፈላ ነው ።

ሙሴ የእግዚአብሔር ሰው ፣ የሕዝብ አባት ፣ መልካም መሪ ነበር ። ያለ አገር ሕገ መንገሥት የተቀበለ ፣ ያለ እርሻ ሕዝብ ሲበላ ያየ ፣ ያለ ኢኮኖሚ አርባ ዓመታት ያስተዳደረ ቅን ሰው ነው ። ይህ ሙሴ ሚሊየን ሲወለድ ሚሊየን ሲሞት አይቷል ። የታሪኩን ሰፊነት ለማወቅ ከዘጸአት እስከ ዘዳግም ያለው የአርባ ዓመት የሙሴ የአመራር ዘመን ነው ። አራት መጻሕፍት አርባ ዓመታትን ሲዘግቡ ሰፊ ነገር እንዳለ እንረዳለን ። የዘፍጥረት መጽሐፍ አንድ ቢሆንም የሚተርከው የአራት ሺህ ዓመታትን ታሪክ ነው ። ሙሴ የእኛ ሰው ቢሆንና ልጅ ቢወልድ “ብዙ አየሁ” ብሎ ይሰይመው ነበር ። ይህ ሙሴ፡- “አቤቱ ፥ አንተ ለትውልድ ሁሉ መጠጊያ ሆንህልን” ብሎ ዘመረ። አገር ያልነበረው ያ ትውልድ አገሩ እግዚአብሔር ነበረ ። የጦር ሠራዊት ወይም መከላከያ ያልነበረው ያ ትውልድ መጠጊያው እግዚአብሔር ነበረ። ከመሠረታዊ ፍላጎት አንዱ መጠጊያ ነው ። ሰውም እንስሳም መጠጊያ ይፈልጋል ። አንዳንድ መጠጊያዎች ከፍራሽ ስፍራ ፣ ከባዶ ሜዳ ያልተሻሉ ናቸው ። ትምህርት ቤቶች የብልግና ተቋም ሲሆኑ የፈረሱ መጠጊያ ናቸው ማለት ነው ።

ትውልድ የዘመን በረዶ አለበትና መጠጊያ ይፈልጋል ። ትውልድ ፋሽን ፣ ሱስ ፣ አምባገነን መሪዎች የአካልና የሥነ ልቡና እስረኛ ሊያደርጉትን ይፈልጉታልና መጠጊያ ይሻል ። ትውልድ ከመነሻ እየራቀ ጦርነት ይበዛበታልና ፣ የበጋው ሐሩር የክረምቱ ቍር ያስጨንቀዋልና መጠጊያ ይፈልጋል ። ሥጋ ፣ ዓለምና ሰይጣን ያሳድዱታልና መጠጊያ ይፈልጋል ።

እግዚአብሔር የትውልድ መጠጊያ ሲሆን ትውልድ በነጻ ሕይወትን ይማራል ። ስለ ነገ ተስፋ ይኖረዋል ። ነገን በማበላሸት ዛሬን መኖር አይሻም ። “ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር” እንደሚባለው “ሁሉም ነገር ወደ መዝናናት ግንባር” ወደሚል ቀውስ ውስጥ አይገባም ። የጉርምስና ዘመናቸውን ሳያውቁት ያለፈላቸው ወጣቶች ካሉ እነርሱ እግዚአብሔር ቤት የተጠጉ ናቸው ። እስከ ማታ በሰላም የዋሉ ከተገኙ በጠዋቱ እግዚአብሔርን የተተገኑ ናቸው ። እግዚአብሔር የትውልድ መጠጊያ ነው ። አንዳንድ ትውልድ ምቾትን መቋቋም አቅቶት ፣ መና ሰልችቶት ራሱን ለማጥፋት ይፈልጋል ። በጣም ደስ ሲለውም ሲከፋውም የኃጢአት አምሮቱን ይወጣል ። በሰበብ ከማምለክ በሰበብ መበደል ይቀናዋል ። ትውልድ መጠጊያ ያስፈልገዋል ። የምድር ጠቢባንን ከተጠጋ ከሀዲ ይሆናል ። አክተሮቹን ከተጠጋ አስመሳይ ሰው ይሆናል ። ፖለቲከኞቹን ከተጠጋ ጥይት ማብረጃ ይሆናል ። መተተኞችን ከተጠጋ በአጋንንት እርዳታ የሚያምን ይሆናል ። የወላጆቹን የኑሮ ዘይቤ ከተጠጋ ዘረኛና ትዕቢተኛ ይሆናል ። የትውልድ መልካም ጥጉ እግዚአብሔር ብቻ ነው ።

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መስከረም 29 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ