የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የትውልድ መጽሐፍ

“የዳዊት ልጅ የአብርሃም ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ትውልድ መጽሐፍ” /ማቴ. 1፡1 /
የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ አንድ ከብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ግማሽ ያህሉን የሚጠቅስ ነው ። የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ አንድን በትክክል ማጥናት ከኦሪት ዘፍጥረት እስከ መጽሐፈ ዕዝራ ያሉትን ታሪኮች ማወቅ ነው ። የማቴዎስ ወንጌል ከምርኮ በፊትና ከምርኮ በኋላ ያሉትን ታሪኮች ስለሚያነሣ አሁንም በጥልቀት ሲጠና መላው ብሉይ ኪዳንን ይጠቅሳል ማለት ነው ። ብሉይ ኪዳን ከዘፍጥረት እስከ መጽሐፈ አስቴር ያለው ታሪኩ ሲሆን ከመጽሐፈ ኢዮብ እስከ ትንቢተ ሚልክያስ ያለው ደግሞ በውስጡ የተፈጸሙ ታሪኮች ፣ ጥበብና ትንቢት ያሉበት የመጻሕፍት መዝገብ ነው ። በዚህ አካሄድ ስናየው የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ አንድ መላው ብሉይ ኪዳንን ይተርካል ማለት ነው ።
ቅዱስ ማቴዎስ ወንጌሉን መጻፍ ሲጀምር፡- “የዳዊት ልጅ የአብርሃም ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ትውልድ መጽሐፍ” በማለት ነው ። ይህ ሦስት ነገሮችን ያስገነዝበናል ። የመጀመሪያ እግዚአብሔር መጻሕፍትን ያከብራል ። የአገራችን ሊቃውንትም “በቃል ያለ ይረሳል ፣ በመጽሐፍ ያለ ይወረሳል” ይላሉ ። መጽሐፍ እውቀትን ቋሚ ያደርጋል ፣ ደግሞም የሰውን የመርሳት ጠባይ ያግዛል ፣ ከዚህ በላይ ለትውልድ ማውረስ የሚገባን መጽሐፍን ነው ። ሁለተኛው ቅዱስ ማቴዎስ ወንጌሉን እንዲህ ብሎ መጀመሩ ጌታችን በሰው የትውልድ ሐረግ ውስጥ ገብቶ መቆጠሩን የአይሁድም የሮማውያንም የሕዝብ ቆጠራ መጽሐፍ እንዳወቀው ያስረዳል ። ሉቃስ በሮማውያን የዓለም አቀፍ መዝገብ ላይ ጌታችን እንደ ተቆጠረ ሲገልጥ ማቴዎስ ደግሞ በአይሁዳውያን የእምነት መዝገብ ላይ እንደ ተቆጠረ ያስረዳል ። ታሪካችን ውስጥ ክርስቶስ በመግባቱ  በአዳም ረክሶ የነበረው ታሪካችን እንደገና ተቀደሰ ። ቅዱስ ማቴዎስ ከአብርሃም መጀመር ሲገባው የዳዊት ልጅ ብሎ መጀመሩ ሌላው አስደናቂ ነገር ነው ። ጻድቁ አብርሃም ከዳዊት ስምንት መቶ ዓመት ርቆ የነበረ ነው ። ማቴዎስ ግን የዳዊት ልጅ የአብርሃም ልጅ በማለት መጻፍ ጀመረ ።
የዳዊት ልጅ በማለት መጻፍ የጀመረው ለምንድነው ስንል የማቴዎስ ወንጌል ስለ ክርስቶስ ዘላለማዊ መንግሥት የሚናገር መጽሐፍ ነው ። በዚህም የአንድ ንጉሥ መገለጫዎች በእያንዳንዱ ምዕራፍ ተጠቅሷል ። አንድ ንጉሥ ትውልደ ሐረገ አለው ። ጌታችንም ትውልደ ሐረጉ ተጠቅሷል ። የይሁዳ ነገድ ንጉሥ የሚወጣበት ዘር ነው ። ጌታችንም ከይሁዳ ነገድ ተወልዷል ። ንጉሥ ሲወለድ ነገሥታት ደስታቸውን ይገልጻሉ ፤ ጌታችን ሲወለድ ሰብአ ሰገል ደስታቸውን ለመግለጥ መጥተዋል ። ንጉሥ መንገድ ጠራጊ አለው ፤ መጥምቁ ዮሐንስም የጌታችን መንገድ ጠራጊ ነው ። ንጉሥ አዋጅ አለው ፣ የሸፈተን በሰላም ግባ ይላል ፤ ጌታችንም ንስሐ ግቡ ብሎ የኃጢአት ሽፍቶችን ጠርቷል ። ንጉሥ ሕገ መንግሥት አለው ። ጌታችንም በተራራው ስብከቱን የመንግሥቱን መርሕ ገልጧል ። ንጉሥ እስረኞችን ይፈታል ። ጌታችንም በደዌና በአጋንንት እንዲሁም በኃጢአት የታሰሩትን ፈትቷል ። … ንጉሥ ተተኪውን ያሳውቃል ፣ ጌታም ደቀ መዛሙርትን ሹሟል ። ስለዚህ ስለ ንጉሡና ስለ መንግሥቱ ጠባይዐት የሚናገረው የማቴዎስ ወንጌል የዳዊት ልጅ በማለት መጀመሩ ትክክል ነው ።
የትውልድ መጽሐፉ ብዙ ስሞችን ዘርዝሮ ክርስቶስን ሲያገኝ ያበቃል ። ክርስቶስ የመላው ብሉይ ኪዳን ፍለጋ ማብቂያ ነው ። የእርካታም ጥጉ ነው ። በትውልድ መጽሐፉ ውስጥ ብዙ ስህተት የፈጸሙ ሰዎች ተጠቅሰዋል ። ለምሳሌ ዳዊት ከቤርሳቤህ ሰሎሞንን ወለደ ይላል ። ይህ የዳዊት የውድቀት ታሪኩ ነው ። እነዚህ ሁሉ ድካሞች ቢኖሩም ክርስቶስ ግን ሁሉን ይቀድሳል ። የትውልድ መጽሐፉ ውስጥ ጻድቃን ፣ ደካሞች ፣ ጸጋ የጋረዳቸው ሰዎች አሉ ። ከሁሉ በላይ ግን ሁሉን የሚቀድሰው ክርስቶስ ተወስቷል ።
የትውልድ መጽሐፍ መልካምም ክፉም ያደረገ ይሰፍርበታል ። ደጉም ሆነ ክፉው ታሪክ ትምህርት እንጂ መብል አይሆንም ። ታሪክ በደግነቱም በክፋቱም ያስተምራል ። ታሪክ ላይ ቆይቶ መጣላት ግን አመድ ላይ መንከባለል ነው ። እኛም በታሪክ ፊት ነንና በጎ ልንሠራ ይገባናል ። የታሪክ ባለቤት ሕዝብ ነው እንላለን ፣ የታሪክ ባለቤት ግን እግዚአብሔር እንደሆነ ማቴዎስ ይነግረናል ።
ዛሬም እየተጓዘ ያለው የትውልድ ሐረግ ክርስቶስ ዳግመኛ ሲመጣ ይቆማል ። በሰማይም ዝና ፣ ባለጠግነት ፣ ዘር ፣ ጎሣ አይቀጥልም ። በሰማይ የሚቀጥለው በሥላሴ ማመን ብቻ ነው ።
አቤቱ የልቡና ጆሮአችንን ክፈትልን አንተን ብቻ እንሰማ ዘንድ ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ