የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የትውልድ እሪታ

                                      ቅዳሜ ነሐሴ ፬፣ ፳፻፯ ዓ/ም
ለትውልዳችን  ጩኽት ቤተክርስቲያን ምን ምላሽ፣ ምንስ መፍትኄ ይኖራት ይሆን…???
“አቤቱ እባክህ የሆነብንን አስብ፣ ዘመናችንን እንደ ቀድሞ አድስ…” ሰቆ ኤር. ፭፥ ፩ _ ፳፪
ለብዙ ዘመናት አንገታችንን የደፋን ህዝቦች ነን። ሺ ዘመናትን በሚያስከነዳው ዥንጉርጉር  ታሪካችን ከምንኮራበት ስልጣኔያችንና ጀግንነታችን ይልቅ የምናፍርበት ጉስቁልናችን፣ ስብራታችንና ኃፍረታችን አይሎብን በእጅጉ ተሸማቀናል፡፡ በሀገራችን ትናት በሆነው ዛሬም እየሆነ ባለው፣ በምናየውና በምንሰማው ነገር ሁሉ አንገተ ሰባራ ሆነናል። መቼ ነው ይህ ታሪካችን ተለውጦ ቀና ብለን የምንሄደው ብለን በብዙ ተስፋ አድርገናል፡፡ የብዙዎች ወገኖቻችን ደምም ለለውጥ፣ ለአዲስና ብሩህ ተስፋ በሀገራችን ተራሮችና ሸንተረሮች እንደ ውኃ ፈሷል፣ ብዙዎቻችንም ነፍሳችን እስክትዝል ለሀገራችን ለውጥ በብዙ አንብተናል፣ ወጥተናል ወርደናል፡፡ የለውጥ ያለህ በሚል ከልብ በሆነ ናፍቆትም ተቃጥለናል። ዛሬም በናፍቆት እንደተቃጠልን ዛሬም በናፍቆት ነፍሳችን እንደዛለች መሽቶ ይነጋል…
ይህችን በለውጥ ናፍቆት፣ የተስፋ ጭላንጭል ያለህ በሚል የዛለች ነፍሳችንን አይዞሽ የሚላት፣ የውስጣችንን ጩኽት የሚመልሱ፣ ስብራታችንን የሚጠግኑልን፣ ስማችንን የሚያድሱልንን እና የነገን ብሩህ ተስፋ ሊያሳዩን የሚችሉ እንደቀደሙት ዘመናት ያሉ ደጋግና ሁሉን በፍቅር ዓይን የሚያዩ የሃይማኖት አባቶች እንዲኖሩን ደጋግመን ተመኝተናል፤ ነገር ግን ዓይናችንን የጣልንባቸውም ሆነ በብዙ ተስፋ ያደረግናቸው የሃይማኖት አባቶቻችን ከዚህ የዘመናት እንቆቅልሾቻችን፣ ያለ ቅጥ ከረዘመው የጨለማው ዘመን ዥንጉርጉር ታሪካችን፣ ጉስቁልናና ውርደት ከተሞላው አስከፊ ዘመናችን መውጫ ቀዳዳ ሊያሳዩን ቀርቶ በሂደት የችግሩ መንስዔና ሰለባ የሆኑበትን በርካታ አጋጣሚዎችን እየመረረንም ቢሆን መራሩን እውነታ ለመቀበል የተገደድንበት በርካታ አጋጣሚዎች ትናትና አብረውን ነበሩ፣ ዛሬም አብረውን ቀጥለዋል::


ስለ እናት ምድራችን ኢትዮጵያ ሲነሳ መቼም ቢሆን በብዙዎች አእምሮ የሚከሰተው ምስል የጦርነት አውድማ፣ አኬልዳማ_የደም ምድር፣ ህዝቦቿ በርሃብና በድርቅ የተጎሳቆሉ፣ ከጠኔ የተነሳ አንጀታቸው ከሆዳቸው ጋር የተጣበቀ ምስኪን ህፃናት፣ አንጀት ድረስ ጠልቆ የሚሰማ የልብ ሀዘን በገጻቸው ጎልቶ የሚታይ፣ ተስፋቸው የነተበባቸው፣ ምሬትና እሮሮ የሚንበብባቸው የአርጋውያን አባቶችና እናቶች ምስል ናት እናት ሀገር ኢትዮጵያ… በእኛና በሌሎች ዓይን ስትታይ… ተስፋዋን የተነጠቀች፣ ልጆቿ የመከኑባት፣ ሳታጣ ያጣች፣ የወላድ መካን… ባለዥንጉርጉር መልክ ናት እናት ምድራችን ኢትዮጵያ… ይህች የትላንትነዋ ኢትዮጵያ ደግሞ ክብሯም ሆነ ውርደቷ የቤተክርስቲያናችን ግዙፍ የታሪክ አካል እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡
ይሄም ጹሁፍ ቤተክርስቲያን መንፈሳዊና ሰማያዊ እንደመሆኗ በእግዚአብሔር ፍቅር፣ ጥበብና ማስተዋል ትላንት በሆነው ዛሬም እየሆነ ባለው ነገር ትውልዱ ለሚያነሳው ጥያቄና እንቆቅልሽ መልስ መስጠት የሚገባት እንደሆነች ለማስታወስ በቅንነት መንፈስ የተፃፈና የትውልዳችንን ጩኽት ለማስተጋባት የሚሞክር ጹሁፍ  ነው፡፡   
በአንድ ወቅት በቀድሞ የቀ.ኃ.ስ ዩኒቨርስቲ በአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪ የነበሩት ዶ/ር ኃይሉ አርዓያ ለዚህች አኬልዳማ ለሆነችው ኢትዮጵያችን፣ በረሃብና በወረርሽኝ፣ በእርስ በርስ ጦርነት በየዘመናቱ የአብራኳን ክፋዮች ለሞት እየገበረች የወላድ መካን ለሆነችው፣ ተስፋ፣ ሠላም እና ብልጽግና የራቃትን የእሳቸውን ዘመን ኢትዮጵያን፡- ‹‹ዘመን የሞተባት፣ የመከነች፣ ፍሬ አልባ››ሲሉ በመረረና ቁጭት በሞላው ስሜታቸው ተማሪ በነበሩበት ዘመናቸው በተቀኙት ቅኔያቸው የዛን ጊዜዋን እምዬ ኢትዮጵያን እንዲህ ነበር የገለጿት/የሳሏት፦ የዛሬዋስ ኢትዮጵያ ከአራት አስርት ዓመታት በኋላ እንዴት ትገለጽ ይሆን…???
ይኽው ትታያለች ለህዝብ በይፋ፣
ጥቁር ተከናንባ ጥቁር ተጎናጽፋ።
እኔስ መስሎኝ ነበር ዘመድ የሞተባት፣
የእናት ሞት የአባት ሞት፣
የልጅ ሞት ያጠቃት፣
ለካ እሷስ ኖራለች ዘመን የሞተባት።
                                በዶ/ር ኃይሉ አርዓያ (አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ በ1950ዎቹ)
የዘመን ተሃድሶ የናፈቃትን፣ ይህችው ዘመን የሞተባትን ምስኪን እናት ምድራችን እምዬ ኢትዮጵያ በእግዚአብሔር ምሕረትና ይቅርታ ትታሰብ ዘንድ የልጆቿን በደል በመግለጥ ለንሰኃ እና ለይቅርታ ጥሪ ታደርግ ዘንድ የሚገባት የሰላም፣ የእርቅና የፍቅር ቤት የተባለች ቤተክርስቲያንም ለምድራችን/ለሀገራችን ጨውና ብርሃን ለመሆን በእጅጉ አቅም አጥታ ደክማለች… መሪዎቿም በበርካታ ችግሮች ተጠላልፈው ከዓለም መፍትኄ ፈላጊዎች ሆነዋል፡፡
ለትውልድ ተስፋ የሚሆን ራዕይ ያላቸው ፍቅርን፣ ርኅራኄንና ይቅርታን የተሞሉ፤ እውነተኛ፣ ለሀገርና ለህዝብ የሚራሩ፣ የወንጌል ባለአደራዎች፣ የፍቅር አርበኛ የሆኑ፣ ከከበበን ድቅድቅ ጨለማ አውጥተው የተስፋ ጭላንጭል ሊያሳዩን የሚችሉ የሃይማኖት አባቶች አድራሻው የት እንደሆነ ግራ ተጋብተናል… ልክ እንደ ሊቀ ነቢያት ሙሴ፦
“አቤቱ እባክህ ይህን ህዝብ በምድረ በዳ ባዝኖ፣ መክኖና ፍሬ አልባ ሆኖ ከምታጠፋው እኔን ከሕይወት መጽሐፍ ደምስሰኝ የሚሉ…”  ቅጥረኞች ሳይሆኑ ለመንጋው ነፍሳቸውን እንኳን ለመስጠት ወደኋላ የማይሉ፣ እንደ ነቢየ እግዚአብሔር ኤርምያስ እንባቸውን እያፈሰሱ፦
አቤቱ እባክህ የሆነብንን ተመልከት፣
ስድባችንንም እይ።
ርስታችንም ለእንግዶች፣ ቤቶቻችን ለሌሎች ሆኑ።
ድሃ አደጎችና አባት የሌለን ሆነናል፣
እናቶቻችንም እንደ መበለቶች ሆነዋል…” ሰቆ. ኤር. ፭፥ ፩ _ ፳፪ እያሉ በፍቅር የሚያነቡ የእምነት አርበኞች፣ የወንጌል ባለአደራዎች፣ የእውነተኞች፣ የቅዱሳን አባቶቻችን መገኛቸው ወዴት ይሆን ወገኖቼ…???
እስከመቼስ ያለራዕይ እንቅበዘበዛለን፣ እስከ መቼስ በጉስቁልና በውርደት ዘመናችን በከንቱ ያልፋል፣ እስከመቼስ እረኛው እንደሌለው መንጋ ያለ መሪ በምድረ በዳ እንባዝናለን፣ ስብራታችንና ጉስቁልናችንስ እስከ መቼ ከእኛው ጋር ይዘልቃል… የብሩህ ዘመን ጀምበር ለዘቀዘቀባት እናት ምድራችን፣ ጠብ፣ ክርክርና መለያየት ለነገሰባት እናት ቤተክርስቲያናችን ትንሣዔን የሚያሳየን የፍቅርና የይቅርታ መልእክተኛ የሆነ አባት መቼ ይሆን ይኽው እኔ አለሁላችሁ የሚለን… በንስሐ እንባ፣ በተሰበረ ልብ፣ በተዋረደ መንፈስ እና በእውነተኛ ልባዊ ፍቅር ወደ አባቶቻችን አምላክ የጸጋ እና የምሕረት ዙፋን ሥር የሚያቀርበን…???
በእርግጥም የብሩህ ዘመን ጀምበር ላዘቀዘቀብንና ዘመን ለሞተበት ለትውልዳችን፤ ጠብ፣ ክርክርና መለያየት ለነገሰባት እናት ቤተክርስቲያናችን በነፍሱ የተወራረደ፣ በክርስቶስ ኢየሱስ በሆነ ፍቅርና ርኅራኄ_ በይቅርታ ልብ ተሸክሞን ወደ ልዑል አምላካችን እግዚአብሔር የሚያቀርበን፣ ከእኛም ጋር በአንድ ልብ ሆኖ፦
አቤቱ አንተ ለዘላለም ትኖራለህ፣
ዙፋንህ ከትውልድ እስከ ትውልድ ነው፣
ስለ ምን ለዘላለም ትረሳናለህ?
ስለምንስ ለረጅም ዘመን ትተወናለህ?
አቤቱ ወደ አንተ መልሰን እኛም እንመለሳለን፣
ዘመናችንን እንደ ቀድሞ አድስ። ሰቆ. ኤር. ፭፥ ፳ _ ፳፪  
እያሉ ለእናት ምድራችንና ለቤተክርስቲያን ሰላም፣ አንድነት እና ፍቅር የሚማልዱ፣ ለሞቱብን ዘመኖቻችን ትንሣዔ በጸሎት የሚያተጉን የፍቅርና የይቅርታ መዝገብ የሆኑ ሐዋርያዊ አባቶችን ያበዛልን ዘንድ እና በእውነትም ሌት ተቀን ሳይደክሙና ሳይታክቱ፣ የቤቱ ቅናት እያቃጠላቸው ለቅዱስ ወንጌል በፍቅር የሚደክሙ፣ በእንባና በጸሎት የሚጋደሉትን የወንጌል አርበኞች የሆኑ እውነተኛ አባቶቻችንን ረጅም እድሜ ሰጥቶ በሰላም ይጠብቅልን ዘንድ እጃችንን ከልባችን ጋር ወደ አርያም የምናነሳበት ዘመን ላይ ነን። ቤተክርስቲያንም ለሀገራችን ሰላም፣ እድገትና ብልጽግና እንዲሁም ለትውልድ ተስፋና ፈውስ የሚቃትቱ የእውነተኛ የወንጌል ገበሬዎች፣ የፍቅርና የይቅርታ መዝገብ፣ የጸሎትና የተጋድሎ ሕይወት ምስክር የሆኑ የእውነት ጠበቆች ቤት ልትሆን እንጂ የወንበዴዎች ዋሻ ትሆን ዘንድ አልተነገረላትም፣ አልተፃፈላትምም፡፡
ቤተክርስቲያን ለዘመናት እንቆቅልሽ የሆኑብን ጥያቄዎቻችን ይመለሱልን ዘንድ፣ ለትውልዳችን ጩኽት ነፍስን የሚያሳርፍ መልስ የሚሹ የብዙዎች ልብ፣ ዓይንና እጆች ወደ እሷ ተነስተዋል፡፡ እነዚህ በቅዱስ ማደሪያው የምህረት አደባባይ ለይቅርታ፣ ለሰላም፣ ለምህረት፣ ለፍቅርና ለአዲስ ብሩህ ተስፋ ጎህ መቅደድ የተነሱ ልቦችና የተዘረጉ እጆች ከቤተክርስቲያን ዘንድ በቂ፣ እውነተኛ እና ልብን የሚሳርፍ ምላሽን ይጠብቃሉ፣ ይሻሉም፡፡ በእውነትም የአባቶቻችን አምላክ ልዑል እግዚአብሔር ስለ ቅዱስ ስሙ ሲል የምድራችንን፣ የትውልዳችንን እና የቤተክርስቲያንን የመጎብኘት ወራትን ያቅርብልን፡፡ አሜን!
ወይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ አበዊነ!!!

ያጋሩ