የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የኃጢአተኞች ወዳጅ

“ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው ፤ ከኃጢአተኞችም ዋና እኔ ነኝ፤” 1ጢሞ. 1፡15
ትዕቢት ከእግዚአብሔር መራቅ ነውና ሙት ነገር ነው ። ሙት ነገር የነኩት ሁሉ አብረው ይሞታሉ ። በብሉይ ኪዳን ከታዘዙት ሥርዓቶች አንዱ በድን መንካት ያረክሳል የሚል ነው ። በአዲስ ኪዳን ግን በጥምቀት ጸጋን ያገኘ ፣ በሜሮን የከበረ ፣ ማኅደረ መንፈስ ቅዱስ ፣ ታቦተ ሥላሴ ነውና የሰውን ሥጋ ወይም በድን ስመን እንሸኘዋለን ። ትንሣኤ ዘጉባዔን በማመን በተስፋ የክርስቲያንን በድን እንቀብረዋለን ። ትዕቢት የሞተ ነገር ነው ። የሚነካውን ሁሉ ያረክሳል ። ሰዎች ትዕቢት ሲጀምራቸው ውድቀት እያደባባቸው ነው ። የመዋረድ ዋዜማው ትዕቢት ነው ። ትዕቢት ከሆኑት በላይ ራስን አተልቆ ማየት ነው ። በዚህ ምክንያት ኃጢአት በዓለመ መላእክትና በዓለመ ሰብእ መካከል መግቢያ አገኘ ። ሳጥናኤልን ሰይጣን ያሰኘ ፣ አዲሱ ሰው የተባለውን አዳምን አሮጌ ሰው ያሰኘ ትዕቢት ነው ። በዚህ ምክንያት ትዕቢት ከአርእስተ ኃጣውዕ አንዱ ነው ። ትዕቢት በጣም ጥንቃቄ ካላደረግን በቶሎ የሚይዘን ነው ። ሰው እኔ እኮ አመንዝራ አይደለሁም ፣ እንደ እገሌም ሌባ አይደለሁም ካለ እውነት ቢሆን እንኳ ትዕቢት ነው ። ሰይጣን በሌሎች ነገሮች ካሸነፍነው በትዕቢት ደግሞ ይመጣብናል ። እኔ እኮ ትሑት ነኝ ብሎ መኩራትም እርሱ ትዕቢት ነው ።

ትሕትና በመካከል ያለ ነው ። ከመጠን በላይም ራስን ከፍ አለማድረግና ከመጠን በታች ራስን ዝቅ አለማድረግ እርሱ ትሕትና ነው ። ትሕትና የዝቅተኝነት ስሜት ሳይሆን በእግዚአብሔር የመታመን ጥበብ ነው ። የእግዚአብሔር ሰዎች ተለይተው የሚታወቁት በትሕትናቸው ነው ። ራስን በትክክል ማወቅ እርሱ ቅዱስነት ነው ። ጻድቁ አብርሃም፡- እኔ አፈርና አመድ ስሆን ከጌታዬ ጋር እናገር ዘንድ እነሆ አንድ ጊዜ ጀመርሁ” ብሏል ። /ዘፍ. 18፡27 ።/ አበ ብዙኃን የተባለው ፣ ሥላሴን በቤቱ በእንግድነት የተቀበለው ፣ ስለ ሰዶም ጥፋት የማለደው ፣ በዓለም ላይ ያሉ አይሁዶች ፣ ክርስቲያኖችና ሙስሊሞች አባታችን የሚሉት እርሱ እኔ አፈርና አመድ ነኝ አለ ። ትሕትና ራስን በእግዚአብሔር በማየት ሲገኝ ፣ ትዕቢት ደግሞ በጎረቤት ኑሮ ራስን በማየት ይመጣል ። አብርሃም በእግዚአብሔር ፊት እንደ ቆመ አውቋልና ፍጹም ትሑት ሆነ ። በእግዚአብሔር ፊት ስንቆም ራሳችን ያንስብናል ። ይህ ማነስም ክብርና ደስታ በውስጡ ያለው ነው ። ንጉሡ ዳዊትም፡- እኔ ግን ትል ነኝ ሰውም አይደለሁም የሰው ማላገጫ በሕዝብም ዘንድ የተናቅሁ ነኝአለ ። /መዝ. 21፡6 ።/ ዳዊት እስከ ዛሬ የተከበረ ንጉሥ ነው ። ጌታችንም ወልደ ዳዊት ተብሏልና ክብሩ ለዘላለም ነው ። ላለፉት ሦስት ሺህ ዓመታት ቤተ አይሁድ ፣ ላለፉት ሁለት ሺህ ዓመታት ቤተ ክርስቲያን የዳዊትን ዝማሬ በየቀኑ ይዘምራሉ ። ዳዊት ዝናው ያልፈዘዘው ፣ በየቀኑ የሚያበራው ትሑት ስለነበረ ነው ። ትዕቢተኞች ራሳቸውን ከፍ ስለሚያደርጉ የወደቁ ቀን የሚያነሣቸው የለም ። ትሑታን ግን ያለ ዘመናቸውም ይከብራሉ ። በቅዱሳን ስም የተሰየሙ አብያተ ክርስቲያናት የትሑታን ስምና ዝክራቸው እንደማይጠፋ ምስክር ናቸው ። ትዕቢተኞች የሠሩአቸው የራሳቸው ሐውልቶች ግን ፈርሰዋል ።
ሐዋርያው ጳውሎስም እኔ የኃጢአተኞች ዋና ፣ አውራ ፣ ፊት መሪ ፣ የበደለኞች በደለኛ ነኝ አለ ። ይህ ሐዋርያ የሰረቀ ፣ ያመነዘረ አልነበረም ። አዳኙን ክርስቶስን የገፋ ነበረ ። ሐዋርያው የኃጢአተኞች ዋና የነበረውን ሰይጣንን የእርሱን ወንበር ነጥቆ ፣ የኃጢአተኞች አውራ የነበረውን የአዳምን ስም ወስዶ ራሱን እጅግ ኃጢአተኛ አድርጎ ያቀርባል ። ሐዋርያው ራሱን ኃጢአተኛ ነኝ የሚለው ጻድቅ እንዲሉት አይደለም ። እኛ “እኔ ኃጢአተኛ ነኝ” የምንለው ጻድቅ እንዲሉን ፣ “እናንተማ እንዲህ ካላችሁ እኛ ምን እንበል ?” እንዲሉን ነው ። እውነተኛ ትሕትና ራስን ኃጢአተኛ ማለት ሳይሆን ኃጢአተኛ ሲሉን መታገሥ ነው ይባላል ።
የሃይማኖታችን ራስና ሊቀ ካህናት የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም “እኔ የዋህና በልቤም ትሑት ነኝ” ብሎናል ። /ማቴ. 11፡28-30 ።/ የጌታችን ትሕትና ኃጢአተኞች ላይ በቃል ፍርድ ፣ በልብም ትዝብት የሌለው ስለሆነ ነው ። በሌሎች ድካም ላይ በቃል መፍረድ ፣ በልብ መታዘብ እርሱ ትዕቢት ይባላል ። ጌታችን ግን በልብ ትሑት ነበረ ። በአንገት ሰበር ፣ በጉልበት ሸብረክ በማለት ብዙዎች ትሑታን ናቸው ። በፊት ለፊት ቅዱስ አባታችን እያሉ በስተኋላ ሳይበቁ ቅዱስ የሚሉ አያሌ ናቸው ። ትሕትና የልብ ሲሆን እውነተኛ ነው ።
ታዲያ ዛሬ ያለው ክርስትና አብነት ያደረገው ማንን ይሆን ? ትዕቢት ፣ በሌሎች መፍረድ ፣ ጭካኔ ፣ ጉረኝነት ፣ ወንድነት ፣ ፉከራ ፣ እኔ እኔ ማለት ከማን የወረሰው ይሆን ? የራሳችንን ምስጋና ቁጭ ብለን በፈገግታ የምንሰማው ፣ ሌሎችን እያሳነስን ስለ ራሳችን ካብ የምንክበው ከማን አግኝተነው ነው ? ክርስትና ከፈገግታ ይልቅ ልባዊ ፍቅር ፣ ከጥርስ ይልቅ ውስጣዊ ንጹሕነት ፣ ከልብስ ይልቅ ጸጋ እግዚአብሔር ፣ ከብዙ ንግግር ይልቅ ጥቂት ተግባር ይፈልጋል ። ሐዋርያው ጴጥሮስ፡- ብርና ወርቅ የለኝም፤ ይህን ያለኝን ግን እሰጥሃለሁ ፤ በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሣና ተመላለስ” በማለት ሽባውን ተረተረው ። /የሐዋ. 3፡6 ።/ ዛሬ ብዙ ርስት ፣ ብዙ ብርና ወርቅ አለን ። ጴጥሮስ ግን ብርና ወርቅ የለውም ፤ ፈውስ ግን አለው ። እኛ ብርና ወርቅ አለን ፣ ፈውስ ግን የለንም ። ልዩነታችን እዚህ ላይ ነው ።
የእግዚአብሔር ቸርነትና ምሕረት በትክክል ቢነገር ብዙ ሰዎች ንስሐ ይገቡ ነበር ። ንስሐ የሚገቡ ሰዎች የጠፉት የእግዚአብሔር ቸርነት ፣ የጌታችን ማዳን ስላልተነገረ ነው ። ብዙ ኃጢአተኞች በዐውደ ምሕረት ስንሰዳደብ ፣ በዘመናዊ መገናኛዎች ስም ስንጠፋፋ ፣ የእገሌ መረጃ አለኝ ስንል እየሰሙንና እያዩን ፍጹም ከክርስትና ርቀዋል ። ዛሬ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተደበቁ ጨካኞች በዓለም ቢፈለጉ አይገኙም ። ሰይጣን ሥራው ከቤተ ክርስቲያን ማስወጣት ብቻ አይደለም ። ወደ ቤተ ክርስቲያንም የሚያስገባቸው ሰዎች አሉ ። መንጋውን እንዲበጠብጡ ፣ ሰዎች ተስፋ ቆርጠው እንዲጠፉ የሚያደርጉ የሰይጣን የውስጥ ካድሬዎች አሉ ።
ቤተ ክርስቲያን ኃጢአተኞች በክርስቶስ ደም ታጥበው የሚነጹባት ቤተ ሕሙማን እንጂ ቤተ ፍጹማን አይደለችም ። ዓለሙ ጻድቅ ቢሆን ኑሮ የእግዚአብሔር ልጅ የሰው ልጅ መሆን ባላስፈለገው ነበር ። የሰዎችን ስህተት እንድንሸፍን እንጂ እያስፈራራን ገንዘብ እንድንቀበል አልተጠራንም ። ይህን ክፋት በዓለም ያሉም ገና አልደረሱበትም ። ክርስቶስ ግን የመጣው ለኃጢአተኞች ነው ። ኃጢአተኞችን ስንገፋ የወልደ እግዚአብሔርን ደም ከንቱ እናደርገዋለን ። እርሱ ኃጢአትን ይጠላል ፣ ኃጢአተኞችን ይወዳል ።እኛ ደግሞ በተቃራኒው ኃጢአተኞችን እንጠላለን ፣ ኃጢአትን እንወዳለን ።
ሐዋርያው ጳውሎስ እየተናገረ ያለው የኃጢአተኞች ዋና በምሆን በእኔ ላይ ምሕረቱን ያበዛው ጳውሎስን ይቅር ያለ እኛንማ ይቅር ይለናል ብለው ኃጢአተኞች ተስፋ እንዲያደርጉ ነው ይላል ። ትልቁን ከማረ ትንሹን መማሩ እርግጥ ነው እያለ ነው ።
ጌታችን የመጣው ኃጢአተኞችን አድራሻ አድርጎ ነውና ውስጣዊ ክስ የሚሰማችሁ ፣ በራሳችሁ ፊት መቆም ያቃታችሁ ፣ ራሳችሁን በጸጸት የምትቀጡ ወደ መድኃኒታችሁ በንስሐ ቅረቡ ። በፊቱ ስትወድቁ ያለፈው ዘመን ታሪካችሁ አብሮ ይወድቅና አዲሱን ሸክም ፍቅርን ይዛችሁ ትነሣላችሁ ። ሸክም አስጥሎ ሸክም የሚሰጥ ፣ የሚከብደውን ጭነት አውርዶ ፣ ቀሊል ቀንበር የሚያሸክም ፣ የሚበልጠውን ሸክም ወስዶ የሚያስደስተውን ኃላፊነት የሚሰጥ ጌታ እየጠበቃችሁ ነው ። መዳን ኃላፊነት መሆኑን ጨምሮ ሊነግራችሁ ነው ።
ጌታችን ኃጢአተኞችን ሊያድን መምጣቱ የታመነና ሁሉ ሊቀበሉት የሚገባ መሆኑን ይናገራል ። እኔ ይቅር አልባልም የሚል ስጋት ያለባቸው ሰዎች አሉ  ። የራሳቸውን ስርየት ተቀብለው ሌሎች ይቅር እንደሚባሉ የማይቀበሉም አሉና ይህን አለ ።
የኃጢአተኞችና የቀራጮች ወዳጅ ተብለህ በእኛ ምክንያት ሐሜት የተቀበልህ ጌታችን ምስጋና ለስምህ ይሁን ።
1ጢሞቴዎስ /17/
ኅዳር 25 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲ.አ.መ.
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ