በዛሬው ዘመን ብዙ ንቃቶች ይታያሉ ፡፡ የሰብአዊና የማኅበራዊ መብት ተሟጋቾች እየበዙ ነው ፡፡ እነዚሁ ተቋማት በራሳቸው መብትን የሚጥሱ መሆናቸው ሳይዘነጋ ፡፡ ስለ ሰው ዘር እኩልነት በሚሰበክበት በዛሬው ዘመን የዘር መድልኦ ፣ የሥልጣን መባለግ ፣ ብዙ አሰቃቂ ወንጀሎች ፣ ብዙ የስደተኞች መጥፎ አያያዝ ፣ ብዙ የሴቶችና የሕጻናት ጉዳት ይሰማል ፡፡ ዓለም ሕግን በጣም ትወዳለች ፣ ሕግን እንደ ማብዛቷ ለማክበር ግን አልታደለችም ፡፡
† ፈሪሃ እግዚአብሔር የሰውን ልብ ካልተቆጣጠረ የሚያስፈራሩ ሕጎች ከመደፈር አይድኑም ፡፡
ብዙ ሰው ነቅቷል ፡፡ ብዙ ሰው የምናገረው አለኝ ይላል ፡፡ ያልተጣሩና መታረም የማይፈልጉ አሳቦች አደባባይ ውለዋል ፡፡ የዘር ፣ የሃይማኖት ፣ የፖለቲካ ፣ የቢዝነስ ንቃቶች ይታያሉ ፡፡ በበራድነት እየተጓዘ ያለው እውነተኛው እምነትና ፍቅር ብቻ ነው ፡፡ ሌሎች ነገሮች በታላቅ ትኩሳት ውስጥ ናቸው ፡፡ ሰዎች ለመገናኘት ማዕከላዊ አሳብን አልመረጡም ፡፡ ጥግና ጥግ ይዞ መታኮስ ግን ባሕል እየሆነ መጥቷል ፡፡ የተጨፈለቀ ሰው እንጂ የተባበረ ሰው መፍጠር እያቃተን ይመስላል ፡፡ መጠራጠር ፣ ትንታኔ መስጠት ፣ እንዲህ የሆነው በዚህ ምክንያት ነው ማለት ፣ ርእስ ይዞ ዝርዝር ማውራት ፣ እገሌ የዓላማችን እንቅፋት ነው መውደም አለበት የሚሉ ንቅናቄዎች አያሌ ናቸው ፡፡ እርሱ ፣ እርሷ እንጂ እኔ የሚል ድምፅ እየጠፋ ኃላፊነትን የሚወስድም እየራበን ይመስላል ፡፡ ስለ አስተሳሰብ አካል ይቀጣል፡፡ እኛን አልመሰለም ተብሎ ሰው በአቋሙ ብቻ ዓይንህ ላፈር ይባላል ፡፡ የራሴን ኑሮ መኖር እፈልጋለሁ ብሎ ከቡድን ርቆ የተቀመጠ ሰው ስሙ ፣ ክብሩ እንዲጠፋ ይደረጋል ፡፡ ብዙ ንቃቶች አሉ ፡፡ አገራዊ ሳይሆን ቡድናዊ ፣ ሰዋዊ ሳይሆን ጎሣዊ ፣ መንፈሳዊ ሳይሆን አክራሪነት ያለበት እንቅስቃሴ እየጦፈ ነው ፡፡
ሐዋርያው ጳውሎስ፡- “በጽድቅ ንቁ” አለ 1ቆሮ. 15፡34 ፡፡
እኛ የነቃነው በምንድነው ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን ፡፡ ልጆች የነቁት በምንድነው ? የሰው አገር ቋንቋ በመናገር ነው ? ወይስ ፊልም በማየት ነው ? ወጣቶች የነቁት በምንድነው ? ራሳቸውን በዝሙት እሳት በመለብለብ ነው ? ጎልማሶች የነቁት በምንድነው ? ገንዘብ በመሰብሰብ ነው ? አረጋውያን የነቁት በምንድነው ? ሽምግናቸውን በሚያጠፋ ቀለም ነው ? አሮጊቶች የነቁት በምንድነው ? ስለ ፈረንጅ አገር በማውራት ነው ?
† በጽድቅ ካልነቃን ፍጻሜው መልካም አይደለም፡፡
አገርን የጎሣ ማሰሮ ውስጥ ለመክተት ትግል ላይ ነን ፡፡ ውጤቱ ማሰሮው ይሰበራል ፡፡ ቤተ ክርስቲያንን የማኅበር ማኅደር ውስጥ ለመክተት ነቅተናል፡፡ ፍጻሜው መበተን ነው ፡፡ የዘር ዕድር ከመጠጣት የሰው ዓለም አባል መሆን የተሻለ ነው ፡፡ ከዚያ ሁሉ በላይ የእግዚአብሔር መሆን የሚያስደስት ነው ፡፡ ብዙ ንቃቶች የሰውዬውን ምልክቱን ፣ ቋንቋውን ለመለየትና እገሌ እንዲህ ነው ለማለት ነው ፡፡ ሰው ከሆነ ይበቃን ነበረ ፡፡ ምንጩን ትተን ወራጅ ላይ መታገል ፣ አዳምን ጥለን ቅርንጫፍ ላይ መንጠልጠል ከንቱ ንቃት ነው ፡፡ ብዙ ሰው ሃይማኖትን በሚመለከት ትኩስ ልብ ያለው ይመስላል ፡፡ ሃይማኖት ግን በምንም መንገድ ፍቅርና ጨዋነትን አይጥልም ፡፡ በሃይማኖት ስም መሰዳደብ ሰይጣንን ብቻ የሚያከብር ነው ፡፡ የስድብ ንቃት ፣ የቡድን ንቃት በጣም በዝቷል ፡፡ ሐዋርያው እነዚያን ዘመናዊ ነን የሚሉትን የቆሮንቶስ አማንያን በጽድቅ ንቁ ይላቸዋል ፡፡
ትልልቅ ሆቴሎችን ፣ የምግብ አበላሎችን ፣ የፋሽን መስመሮችን አለማወቅ ከሕይወት አያጎድልም ፡፡ ጽድቅን መጣል ግን ከሕይወት ያጎድላል ፡፡ ብዙ ባለ ትዳሮች ትዳራቸውን ለማቆም የሚፈልጉት በፊልም ላይ በተማሩት ስልት እንጂ በመንፈሳዊነት አይደለም ፡፡ ርቀት በማይጓዝ ነገር መንቃት ከንቱ ንቃት ነው ፡፡ የሸመገለ በቦታው ፣ ወጣትም በቦታው በጽድቅ ቢነቁ የተሻለ ዓለም መፍጠር ይቻል ነበር ፡፡ ገንዘብን በሚመለከት ብዙ ሰው ነቅቷል ፡፡ እንዴት ልቀበል እንጂ እንዴት ልስጥ አይልም ፡፡ ሕይወት መስጠትና መቀበል መሆኗን ከዘነጋን የምንጎድለው ከደስታ ነው ፡፡ ንቃት ማለት ማኅበራዊ መገናኛ መጠቀም አይደለም ፡፡ በመንግሥታት የምንሰለልበት ፣ ራቁታችንን የቆምንበት ሜዳ ቢኖር ማኅበራዊ መገናኛ ነው ፡፡ ማኅበራዊ መገናኛ የተደበቀውን ነውራችንን ያወጣ ነው ፡፡ በእነዚህ ጫካዎች ውስጥ ተደብቆ ጀግና መሆን ንቃት አይደለም ፡፡ ኃላፊነት የማይሰማውና የምናገረው ምን ችግር ያመጣል የማይል የነቃ አይደለም ፡፡ ሰይጣናዊ ንቃቶች ብዙ ኑሮዎችን እያፈረሱ ነው ፡፡ እኛስ የነቃነው በምን ይሆን ? በጽድቅ እንንቃ ፡፡
የደስታ ቋጠሮ/12
ተጻፈ አዲስ አበባ
ሐምሌ 6/2010 ዓ.ም
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን