የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የነቢያት ጉባዔ ክፍል 6

ነቢዩ ሙሴ ወደ አሮንና ወደ ኢያሱ እያየ መናገሩን ቀጠለ፡-

“እኔ በጉልበቴ እስራኤልን ነጻ ላወጣ ተነሣሁ ። ነገር ግን ራሴን ለስደት ዳረግሁ ። “ጨው ውኃ ልትቀዳ ወደ ወንዝ ወረደች ፣ እንኳን ልትቀዳ እርስዋ ራስዋ ውኃ ሁና ቀረች” የተባለው ደረሰብኝ። በመጨረሻ ግን የራሴን መቃብር ቆፍሬ ተቀበርሁ ። ከአንድ ሚሊየን የሚልቅ ሕዝብን መርቼ አንድ ቀባሪ አልነበረኝም ። የእግዚአብሔር ሰው ቀብሩ ሳይሆን ኑሮው ፣ ሞቱ ሳይሆን ምርጫው ፣ መልኩ ሳይሆን እግሩ የሚያምር ነው /ሮሜ. 10፡15/ ። እናንተ አገልጋዮች ዓለም በዝና መቃብር ሳትቀብራችሁ ፣ የወርቅ ጉድጓድ ውስጥ ሳትጥላችሁ ፣ የአልማዝ ሸለቆ ውስጥ ሳታስራችሁ መቃብራችሁን ቆፍሩ ። ለዓለም ያልሞተ ለእግዚአብሔር መኖር አይችልም ። ለሚታየው ዓለም ያልሞተ ለማይታየው ዓለም መኖር አይችልም ። ሊቁ ልጃችን ቅዱስ አትናቴዎስ፡- “ዓለም ሁሉ ጠላህ” ቢሉት “እኔ አስቀድሜ ዓለሙን ጠልቼዋለሁ” አለ ይባላል ። ዓለምን ቀድሞ ያልናቀ ዓለም ስትንቀው ይደነቃል ። እንዳይሰድቡት ብሎ ይዋሻል ፣ እንጀራ እንዳይነሡት ብሎ ኅብስተ ሕይወት ክርስቶስን ይክዳል ። ዓለም ድንጋዩን ወርቅ አድርጋ ታሳያለች ። “ወድቀህ ካልሰገድህ አልሰጥህም” ትላለች ። ወድቀው ሲሰግዱ በድንጋዩ መትታ ትገድላለች ። በሽታ ከገደለው ምኞቱ የገደለው ይበዛል ።”

“እናንተ የልዑል ነቢያት አገልጋዮች ! ለእኔነታችሁ መሞት አለባችሁ ። እስራኤል ቀይ ባሕር ውስጥ ባይቀበሩ መና አይበሉም ነበር ። ከክርስቶስ ጋር ያልሞተም ለእግዚአብሔር ክብር መነሣት አይችልም ። ዓለም ተስፋ እስክትቆርጥባችሁ ፣ እናንተም በዓለም ተስፋ እስክትቆርጡ በሞት ሕግ መለያየት አለባችሁ ። ቤተ መንግሥቱ ያወራውን እናንተ መስማታችሁን የሚያረጋግጥ ፣ እናንተም የተናገራችሁት ነገሥታቱን ያላስከፋ መሆኑን ማዳመጥ ከማን የወረሳችሁት ባሕል ነው ?? ከምድራውያን ጋር ያላችሁን ርኵስ ጋብቻ ፣ የሰዎችን ፊት እያያችሁ ያላመናችሁበትን መናገር ፣ ሁለገብ ለመባል ጽድቁንም ኃጢአቱንም መባረክ ፣ አዋቂ እንዲሏችሁ መጽሐፋችሁንና ፍልስፍናን ማዛመድ ፤ ከደረጃችሁ መውረድ ፣ ራሳችሁን በራሳችሁ ማጥፋት ነው ። ለምእመን እየራራችሁ ለወደቀ አገልጋይ ግን የምትጨክኑ ፣ የምትሰብኩትን ምሕረት ለግላችሁ ብቻ እየተጠቀማችሁ ፣ ራሳችሁን በጸጋው ሌላውን በሕግ የምትዳኙ ፣ ከሥራ ይልቅ ሴራን የመረጣችሁ ፣ ለአንድ እንጀራ በእግዚአብሔር ስም መዋሸትን የደፈራችሁ ፣ በእናንተ ስብከት ሌላው እያመነ እናንተ የካዳችሁ እንዳትሆኑ እባካችሁ ተጠንቀቁ !! እኛ እዚህ በሰማይ ያለነው የእግዚአብሔርን ደግነት ፣ በመንግሥቱ ያለውን ሰማያዊ ግብዣ ባየን ጊዜ ወደ ምድር ሄደን ለማገልገል ተመኝተናል ፤ ግን አይቻልም ። ማገልገል ዕድል ነውና ተጠቀሙበት ።”

ሙሴ ይህን ሲናገር “ምነው አገልጋዩ ሁሉ ይህን በሰማ” አልኩኝ ። አንደኛው ልቤም፡- “እግዚአብሔር የሚናገረው ለመጣው እንጂ ላልመጡት አይደለምና ወደ ራስህ ተመልከት” አለኝ ።

ይቀጥላል

የነቢያት ጉባዔ/6

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ሚያዝያ 12 ቀን 2015 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ