የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የነቢያት ጉባዔ/8

ታላቁ ነቢይ ሙሴ በጉባዔው ላይ ንግግሩን ቀጠለ፡-

“እናንተ በምድር ያላችሁ አገልጋዮች ፣ ካህናተ ሥላሴ ! በጥቅም ፣ በውዳሴ ከንቱ አትስከሩ ። የሰከረ ሰው ምን እንደሚያደርግ አያውቅም ። በውዳሴ ከንቱ ፈረስ ላይ የተቆናጠጠ ያልተገራ ፈረስ ላይ ተሳፍሮአልና መውደቁ አይቀርም ። ሰካር ጠዋት ይምላል ፣ ማታ ይመለሳል ። በውዳሴ ከንቱ የሰከረም ፣ ምስጋናው አልጠቅም ይለዋል ። በሸንጋዮችም ሲዘረፍ ይኖራል ። “እርሱ እኮ” እያሉ ብልጦች ያራቁቱታል ፣ ገንዘቡን ያለ ውለታ ይጨርሳል ። በእውነት የሚገሥጸውን ሰው እንደ ጠላቱ ይቆጥረዋል ። ራሱን የሚሾም የእግዚአብሔር ሹመት ሲመጣ ያልፈዋልና ራሳችሁን ባሕታዊ ፣ ነቢይ ፣ ሐዋርያ አትበሉ ። ስትሞቱ የሚነገርላችሁን ቆማችሁ ለራሳችሁ ካስነገራችሁ መሞታችሁን እወቁ ። በቁሙ ሐውልት የሚሠራ ፣ የሞተ ቀን ማንም እንደማይሠራለት ያረጋገጠ ነው ። ጥፋታችሁ በፊት ለፊት ፣ ደግነታችሁ ግን በኋላ ቢወራ የተሻለ ነው ። ለሹመት ስትጠሩ እንኳ አልበቃም ብላችሁ ሽሹ እንጂ ለመሾም ብላችሁ አድማ አታደራጁ ፣ ጉቦ አትነስንሱ ። ዋጋ የምሰጥ እኔ ነኝና ሰው ስም ሰጠኝ ብላችሁ አትጨነቁ ። በፍርድ ቀን የከሰሱአችሁም ያወደሱአችሁም ስለ እናንተ አይናገሩም ። ሥራችሁ ይከተላችኋልና ሰው ከሚያመሰግናችሁ ሥራችሁ ያመስግናችሁ ።

ደም በደም እንደማይጠራ ፣ በሹመት ፍቅር ላይ አድማና ጉቦ የበለጠ መርከስ ነው ። እንደ አሮን የሰውን ጠብ ፈርታችሁ ጣዖት አትጥረቡ ። በእግዚአብሔር ስም ከብራችሁ ፣ በሕዝብ ስም የምትኖሩ አይምሰላችሁ ። አሮን አፈ ማር ነበር ። እግዚአብሔር ግን አፈ ቆላፋውን እኔን ሙሴን መረጠ ። የምላስ አርበኞች የትኛውም ውጊያ ላይ ውለው አያውቁም ። እምነታችሁ ጥረትን እንዳይንቅ ተጠንቀቁ ። እግዚአብሔር ተነሣሽነታችሁን አይቶ ጸጋን ይጨምራል እንጂ እንደ ማሽን አይጠቀምባችሁም ። ጥረታችሁም እምነትንና ጸጋን ከንቱ እንዳያደርግ ፣ “ያለ እኔ ምንም ማድረግ አትችሉም” ያለውን ቃለ ወንጌል አስቡ ።

የእምነት ቃልን አውጁ ። ይህ አዋጅ መኪና የእኔ ነው ፣ ቤቱ የእኔ ነው የሚል ፍቅረ ንዋይ ሳይሆን እግዚአብሔር አንድ ነው ፣ ክርስቶስ ጌታ ነው የሚል ነው ። እናንተ የእግዚአብሔር አገልጋዮች ዘመኑ ደርሶአልና ለማትኖሩበት ዓለም ደክማችሁ ወደምትኖሩበት ዓለም ባዶ እጃችሁን እንዳትሄዱ ተጠንቀቁ ።”

ሙሴ ይህን ቃል ከተናገረ በኋላ ሰይጣን የአንጀት ሎሌዎች አግኝቶ እግዚአብሔር ግን እያበላ እንኳ በእውነት የሚያገለግሉትን በማጣቱ ኀዘን የገባው መሰለ ። ነቢዩ አልሳዕም በድንገት ብድግ ብሎ መልእክት ጀመረ፡-

“የዘመናት ርዝማኔ አንድ የሚያደርጋቸው የችግሮች ተመሳሳይነት ነው ። እግዚአብሔር ግን ማለዳ አዲስ ነው ። እርሱ ፈውስን ብቻ ሳይሆን ደዌንም ጸጋ አድርጎ ይሰጣል ። ኢዮብ እምነቱ እንዲታወቅ ፣ ጳውሎስ በጸጋው ብዛት እንዳይታበይ የጸጋ ደዌ ተቀብለዋል ። ትዕቢት የነፍስ በሽታ ፣ ከእግዚአብሔር የሚለይ ነው ። ደዌ ሥጋ ግን ከእግዚአብሔር አይለይም ። እንደውም ለንስሐ ሊያበቃ ይችላል ። ቅዱሳን ሁሉ በደዌ ውስጥ አልፈዋል ። ደዌውን መጠበቂያ አድርጎላቸዋል ። መከራ የሌለው ክርስትና አጥር የሌለው ቤት ነው ። ሰዎች ከእምነት መከራ ቢርቁም መከራን ግን ማለፍ አልቻሉም ። የዚህ ዓለም ባለጠጎች አልጋን እንጂ እንቅልፍን መግዛት አልቻሉም ። ባለገንዘቦች ምግብን እንጂ አምሮቱን መሸመት አልተቻላቸውም ። ንብረት ያላቸው ብዙ ሰው መኮልኮል ችለዋል ፤ ወዳጅን ማትረፍ ግን አልቻሉም ። እንደውም ባገኙ ቍጥር ጠላታቸው ይበዛል ። ባለጠጎችና ባለሥልጣናት በውሸት የሚወዳቸው ፣ በእውነት የሚጠላቸው ብዙ ነው ።

በውብ ከተሞች መራራና ገዳይ ውኃ አለ ። ሕንፃዎች ባደጉ ቍጥር የሰው ሞራል እየወደቀ ይመጣል ። ኢያሪኮ ደማቅ ከተማ ነበረች ፤ ዛሬ ግን አመድ ወርሶአታል ። የተዋቡ ከተሞች የእሳት ቀጠሮ ተይዞላቸዋል ። ወጥመድነታቸውም ወደ ማሳዘን ይለወጣል ። ግንባታቸውም ፍርስራሽ ይሆናል ። የጸና ሰው ብቻ ሳይሆን የጸና ከተማም የለም ። ከመሬት በላይ የነበሩ ከተሞችና ቤተ መንግሥቶች ዛሬ ከመሬት በታች በቁፋሮ ይፈለጋሉ ። ጸንቶ የሚኖረው በእግዚአብሔር ማመን ብቻ ነው ።

ይህን በተናገረ ጊዜ ማኅበረ ነቢያት በሙሉ ብድግ ብለው “ምስጉን ነው የተመሰገነ” እያሉ ዝማሬ ጀመሩ ። የዳዊት በገናም ሲገረፍ ጽንፍ እስከ ጽንፍ ማስተጋባት ጀመረ ። ዕዝራም በማሲንቆ ተከተለ ። ራሴንና ጉዳዬን እስክረሳና እስክረግጣቸው ድረስ በደስታ ተዋጥኩኝ ።

ይቀጥላል

የነቢያት ጉባዔ/8

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ግንቦት 13 ቀን 2015 ዓ.ም.

ያጋሩ

ያግኙን

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ስልክ ፡ +251930006086                             +251911699907

ኢሜል፡ ashumekon@gmail.com

የገጹ ዓላማ

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።

አሸናፊ መኮንን
Ashenafi Mekonnen
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
Commercial Bank of Ethiopia
1000165078482

አቢሲኒያ ባንክ
Bank of Abyssinia
23202573

ሕብረት ባንክ
Hibret Bank
1030416569497017

ወጋገን ባንክ
Wegagen Bank
0870286030101

አዋሽ ባንክ
Awash Bank
01320034656200

በማህበራዊ ሚዲያ ይወዳጁን።

copyright @ 2021 ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን 
በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።