ክፍል አንድ
ሊቀ ነቢያት ፣ ታላቁ መስፍን ፣ ሊቀ ካህናት አሮንን የቀባው ታላቁ ካህን ፣ እግዚአብሔር ባሪያዬ ያለው ፣ የእግዚአብሔርን መልክ ያያል የተባለለት ፣ የሰው ሳይሆን የእግዚአብሔር ሎሌ የሆነው ፣ እጅግ ከፍ ያለው ፣ ነገር ግን በምድር ካሉት ይልቅ ትሑት የሆነው ሙሴ ወደ መድረኩ መጣ ። በዙሪያው የእስራኤልን ነገድ የወከሉ ሰባ ሽማግሌዎች እንደ አጃቢ በዙሪያው ተሰበሰቡ ። ዐቃቤ ሕግ ሙሴ ፣ ብሉይ ኪዳን ሲሰጥ መካከለኛ የነበረው ፣ ከልዑልነት እረኝነትን ፣ ከቤተ መንግሥት ሐቅለ ሲናን የመረጠው ፣ የአርባ ዓመቱ ልዑል ፣ የአርባ ዓመቱ ስደተኛ ፣ የአርባ ዓመቱ መሪ ፣ የገዛ መቃብሩን የቆፈረው ፣ ድንቅ ሰባኪ ሊናገር ሲል ነቢያት ሁሉ ፀጥ አሉ ። የሰማዩ አደባባይ በዝማሬ ውስጥ ፀጥታ ፣ በፀጥታ ውስጥ ዝማሬ አለው ። ሰማይ ሰላም ነው ። ለእግዚአብሔር እንጂ ለራሱ የሚኖር ማንም የለምና ፣ የእኔና የእኛ የሚል ሙግት በአርያም ዓለም የለም ። ሁሉም የእግዚአብሔር ነውና ሽብር የለም ። ሰው የራሱ ሲሆን ሞትን ይፈራል ። ሰው የሰው ሲሆን ሞቶ ይኖራል ።
ሙሴ ወደማይዘጋውና ሥራ ወደማይፈታው ታላቁ የሰማይ አደባባይ ሲመጣ ከአቤል እስከ ሚልክያስ ያሉ ነቢያት ሁሉም በታላቅ አክብሮትና እልልታ ተቀበሉት ። የድል ነሺዎች ማኅበርም ከአቤል ጀምሮ ያሉ ሁነቱን በአትኩሮት ይከታተሉት ነበር ። ምድርን ሁሉ የእኔ ይላታል ፣ ቀና ብሎ ወደ ሰማይ በማየት ግን ሰማይን የእኔ ማለት አይቻልም ። ሰማይ የሁሉ ነው ። ሰማይ ቢፈካ ፣ ቢጨግግ ማንም መለወጥ አይችልም ። ሰማይ ጥያቄ የሌለበት ነው ። እኔም በዚህ የሰማይ ማኅበር ላይ ራሴን ሳገኘው የእኔ የሚል ነገር እስካጣ ሁሉም የእግዚአብሔር ፣ ሁሉም የእኔ ሁኖ ይሰማኝ ነበር ። እጅግ ድህነት እጅግ ባለጠግነት እንዲህ ተሰምቶኝ አያውቅም ነበር ። አቤል የመጀመሪያው ሰማዕት ነው ፣ የመጨረሻው ግን አልነበረም ። የመጨረሻ ከሆንን የመጀመሪያዎች አሉ ። የመጀመሪያ ከሆንም የሚቀጥሉት ይመጣሉ ። ኤልያስ ብቸኛ ነኝ አለ ። በምድርም በሰማይም ግን ብዙ አጋሮች ነበሩት ። ወገን የሌለው ብቸኛ ሃይማኖት የለም ። በሰማይም በምድርም ብዙ ወዳጆች አሉን። ኢዮብ ልጆቹ ቢሞቱም በሰማይ አሥር ልጆች ፣ በምድር አሥር ልጆች ሁነውለት የሃያዎች አባት ሆነ ። እግዚአብሔር አውቆት የሚባክን በሰማይ የተቀመጠ እንጂ የጠፋ አይደለም ። ባለመጥፋትና ባለመታጣት የሚመለክ እግዚአብሔር ነው ። እነዚህ ሁሉ አባቶች እንደ ደመና በዙሪያዬ አሉ ። ደመና ቢቆለልም አያስጨንቅም ። ደመና ባናት ላይ ቢሆንም ቀጥሎ ዝናብ የሚያፈስስ ነው ። የቅዱሳን ገድልም የእውነት ጠል ነው ።
ይቀጥላል
የነቢያት ጉባዔ/1
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መጋቢት 24 ቀን 2015 ዓ.ም.