የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የነጠፈው ጅረት /1/

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ኅዳር 25 ቀን 2011 ዓ.ም
ከሥቃይ ፣ ከሐፍረት ፣ ከኪሣራ ያዳነኝን ፤ ዕረፍት ፣ እምነትና በረከት የሰጠኝን ያን የእግዚአብሔር ልጅ ለመዘከር እፈልጋለሁ ። በገዛሁት እርሻ ላይ ትልቅ ሐውልት ለመሥራት አስቤ የግሪክና የሮማ እጀ ጠበብቶችን በአሥር ሺህ ዲናር አነጋግሬአለሁ ። ዓመታትና ዘመናት ለእኔ ያደረገውን እንዲተርኩ ፣ ትውልድም በተፈራረቀና በዚያች መንገድ ባለፈ ጊዜ ሁሉ በብዙ ለተዋረዱሁት የሰጠውን ብዙ ክብር እንዲናገሩ ፈለግሁ ። ድንጋይን ምን ያናግረዋል ቢሉ ውኃ ይባላል ። ሐውልት ድንጋይ ነው ፣ ሐውልቱን የሚያናግረው የእኔ የእንባ ውኃ ነው ። በድምፅ በተሞላው ዓለም ድንጋይም ተናጋሪ ነው ። የሺህ ዓመት ወረቀት ፣ የጻፈውን የማያጠፋም የድንጋይ ሰሌዳ ነው ። ሰው ድንጋይ ብሎ ይሳደባል ። እግዚአብሔር አሠርቱ ቃላትን በድንጋይ ጽፎ እንደ ሰጠ ይረሳል ። ስድብ ሁሉ ስድብ የሚሆነው ለአላዋቂ ነው ። አላዋቂ ሲሳደብ የተሳደበ ፣ አላዋቂም ሲሰማ የተሰደበ ይመስለዋል ። አህያ ብሎ የሚሳደብም አያሌ ነው ። አህያ ጌታን ተሸክማ ወደ ኢየሩሳሌም እንደ ገባች የማያውቅ የተሳደበና የተሰደበ ይመስለዋል ። ሰው ውሻ ብሎ ይሳደባል ፣ የውሻ ያህል ታማኝነት ግን እንደሌለው ራሱን ባለመፈተሹ አያውቅም ።

በውለታው ፊት ስጦታዬ ፣ በማዳኑ ፊት መታሰቢያዬ ትንሽ ነው ። ግን የልቤን እንፋሎት ካስተነፈሰው ፣ ቃጠሎውን ካበረደው ብዬ ይህን ሐውልት ልተክልለት አሰብሁ ። የጸና መታሰቢያ ለጸናው በረከቱ ይገባል ። አገሬ እስራኤል ብዙዎች ይመኙአታል ። ይመላለሱባታል ። ወና ሁናም ፍርሃት ፣ ፈርሳም ድንጋጤ ሁናባቸዋለች ። ከግብጽ ባርነት ጀምሮ ምድያማውያን ፣ ፌርዛውያን ፣ አማሌቃውያን ፣ ኢያቡሳውያን ፣ አሦራውያን ፣ ባቢሎናውያን ፣ ሔለናውያን ፣ ሮማውያን … ሊነክሷት ይመጣሉ ። ጥርሳቸው በአፋቸው ውስጥ ውኃ ሁኖባቸው ይመለሳሉ ። ለዚህ ነው ነቢዩ ዳዊት “ለጥርሳቸው ንክሻ ያላደረገን የእስራኤል አምላክ ይባረክ” ያለው ። ዛሬም አገሬ ተንቃ ያልተረሳች ፣ ተፈርታ ያልታፈረች ናት ። በሯን ዘግታ መኖሯ ፣ የራሴ ሃይማኖትና ባህል በቂ ነው በማለቷ ፣ ስልታቸውን በሚቀይሩ ጠላቶች እንድትወጋ አድርጓታል ። ይልቁንም ዙሪያዋ በአረማውያን መከበቧ የሃይማኖት ደሴት አድርጓታል ። እርስ በርሳቸው የማይዋደዱ አረማውያንም በአገሬ ጥላቻ አንድ ሁነዋል ። መጠላት ፣ የጠላት ብዛት እንደማያጠፋ አገሬ ምስክር ናት ። አገሬን ሁለት ነገሮች አንድ አድርገው ይዘዋታል ። በአንዱ አምላክ ላይ የተመሠረተው ሃይማኖትና የጠላት መብዛት አንድ አድርገው ያስተሳስሯታል ። ጠላት ሲጠፋ ግን እርስ በርስ መባላት እንጀምራለን ። በየነገዱ ስንከፋፈል ደግሞ ጨርሶ እንዳንለያይ ሃይማኖቱ ይይዘናል ።
ታዲያ የአገሩና የውጭው ሕዝብ ይህን የምስጋና ሐውልቴን እንዲያየው በማሰብ ነበር የሮማና የግሪክ ጠበብቶችን ማነጋገር የጀመርኩት ። በድንገት ሔርማ የተባለው ወጣት ወደ እኔ መጣ ። ሔርማ የብሉይና የአዲስ እውቀት የነበረው ከልቡ የብሉይ አማኝ ስለነበረ ወደ አዲስ ኪዳንም የደረሰ ወጣት ነው። ሰው ለሚያምነው ነገር ታማኝ ሲሆን መንገዱን ቢስት እንኳ እግዚአብሔር ወደ መንገዱ እንደሚመራው ሔርማና ጳውሎስ ምስክር ናቸው ። ሔርማ ከፊቱ ደስታ ይነበባል ። አንቺም ዕረፊ የሚል ድምፅ የሚያወጣ ይመስላል ። ከደስታ ዜና ጋር እንደ መጣ አውቄ መንገድ አጋምሼ ተቀበልሁት ። እርሱም ሰላም ሳይለኝ ሐውልትሽ የሚበልጥ ሐውልት አግኝቷል አለኝ ። እኔም ነገሩን እንዲያብራራልኝ በታላቅ ጉጉት ስጠብቀው ወንጌላዊው ማርቆስ ታሪክሽ በወንጌሉ በምዕራፍ አምስት ከቊጥር 25-34 ላይ ዘግቦታል አለኝ ። እንዴ ! ብዬ በመገረም ዝም አልሁ ። ሐውልት እኮ ዘመን ቢረዝም ይወድቃል ፣ መጽሐፍ አይወድቅም ፤ ሐውልት መጥተው ካላዩት አይሄድም ፣ መጽሐፍ ግን የሚንቀሳቀስ ሐውልት ነው ። በትንሹ ሳስብ በብዙ ደረሰልኝ ። ምስጋናዬንም እርሱ ሠራልኝ ብዬ በደስታ እንደገና ማልቀስ ጀመርሁ ። እስካሁን የገባኝ ልመናን እንደሚሰጥ ነበር አሁን ደግሞ ምስጋናም ይሰጣል ብዬ ማመስገን ጀምርሁ ። ትንሽ የልብ መነሣሣት ስናደርግ በብዙ እግዚአብሔር ይሠራል ። እርሱ አሳብን እንደ ውለታ ይቆጥራል።
በልቤ አንድ ነገር ትዝ አለኝ ። ያኔ እኔ ስፈወስ ማርቆስ ልጅ ነበረ ። እንዴት አወቀ ? ብዬ ጠየቅሁ ።  መንፈሳዊ መገለጥ ከእውቀትና ከዕድሜ በላይ ነው የሚል ድምፅ በውስጤ ስሰማ እንደገና ዝም አልሁ ። ማርቆስ የጴጥሮስ ደቀ መዝሙር ነበርና ወንጌሉን እርሱ እየነገረው እንደ ጻፈው የሰማሁት ትዝ አለኝ ። ማርቆስ በዚህ ክቡር መዝገብ ላይ ያሰፈረኝ ምን ሠርቼ ነው ? አልኩና መልሼ የተሠራልኝ ከሁሉ የበለጠ መሆኑን ፣ ውዴ በነፍስ በሥጋ እንደ ተንከባከበኝ አስተዋልኩኝ ።
ይቀጥላል
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ