የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የነጠፈው ጅረት /4/

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ረቡዕ ታህሣሥ 10 ቀን 2011 ዓ.ም.
ጌታ፡- “ልብሴን የዳሰሰኝ ማን ነው ?”
ሲል ልቤ ሁለት ዓይነት ስሜት ተሰማው ። የመጀመሪያው ፍርሃት ነው ። ሰውን ሸሽቼ የኖርሁ በመሆኔ ሰው መሐል ስገኝ እጨነቃለሁ ። ልዩ ፍርሃትም ይንጠኛል ። አሁንም ደግሞ በብዙ ሕዝብ መካከል እኔና ክርስቶስ ብቻ ንግግር ልንጀምር መሆኑ አስፈራኝ ። በተቃራኒው የደስታ ስሜት ውስጤን ሞላው ። ጌታ ጨርቄን የጎተተ አላለም ። የዳሰሰኝ ማነው ? ስላለ በጎ ምኞቴን በጎ አድርጎ የተረዳልኝ በመሆኑ ደስ አለኝ ። በኖርሁበት ዘመኔ ከሰው ፈልጌ ያጣሁት ፣ ክፉ አድርጌ በበጎ እንዲተረጎምልኝ ፣ አሊያም በጎ አድርጌ በጎ እንዲመለስልኝ አይደለም ። የተናገርሁትንና ያደረግሁትን በጎ ፣ በጎ ነው ብሎ እንዲቀበሉልኝ ፈልጌአለሁ ። ነገር ግን ለበጎነቴ ቀና ትርጉም ባለማግኘት ሳዝን ኑሬአለሁ ። እኔን የነካ በሕጉ መሠረት ይረክሳል ። የነካሁትም ይረክሳል ። ክርስቶስ ግን ቢነኩትም ፣ ቢነካም ይቀድሳል ። በእኔ የሚረክስ አምላክ የለኝም ። እኔን የሚቀድስ አምላክ ግን አለኝ ። አንድ የሃይማኖት መምህርም ከዚህ ሕግ ውጭ አይደለም ፣ እርሱም እኔን በመንካቱ ይረክሳል ። ክርስቶስ ግን ቅድስናው በምንም አይጎድፍም ።

ጌታ ኃይል ከእርሱ እንደ ወጣ በራሱ አወቀ ። የደም ምንጭን ለማድረቅ ኃይል ያስፈልጋል ። በዓለም ላይ በመሳሪያ ኃይል ደም ይፈስሳል ። የበረታ መሳሪያ ያለውም ደምን ለማስቆም ይጥራል ። እርሱም ደምን የሚያቆመው ደምን በማፍሰስ ነው ። ሰማያዊው ኃይል ግን ደምን በልብሱ ቅዳጅ ያቆማል ። ቀይ ባሕር ለሁለት ተከፍሏል ፣ ዮርዳኖስም ግራና ቀኝ ጥግ ይዟል ። እነዚህ ወንዞች ግን በረከት ናቸው ። የሚፈሰው ደም ግን ርግማን ነው ። የእኔ የደም ምንጭ ሲቆም የዓለምስ የደም ምንጭ መቼ ይቆማል ? ብዬ ማሰብ ጀመርሁ ። ደም የፈሰሰበት መሬት ለማብቀል ቢያንስ አሥር ዓመት ይፈጃል ። ደም መሬትን ያሳርራል ። ደም በእግዚአብሔር ፊት ቁሞ ይፋረዳል ። የንጹሐን ደም ትውልድን ዋጋ ያስከፍላል ። ደም ድምፅ አለውና ያውካል ። ደም ያፈሰሱትን ሰዎች ብቻ ሳይሆን ዝም ያሉትንም ይጠይቃል ። የአቤል ደም እስከ ጥፋት ውኃ ይጮህ ነበር ። የቃየን ዘሮች በጥፋት ውኃ ሲያልቁ ያን ጊዜ ዝም አለ ። ዓመታትና ዘመናትን የደምን ድምፅ ዝም ማሰኘት አይችሉም ። ደም የፀጥታው ጩኸት ነው ። የሮማ ገዥዎች የሕዝብን ደም ሲያፈስሱ እንዴት እንደ ቀላል ቆጠሩት ብዬ አስባለሁ ። ደም መፍሰስ ካለ መረጋጋት የለም ። እኔን ሰው ሁሉ ይሸሸኝ እንደነበር እንዲሁም የውጭ ሰዎች ሁሉ ይሸሹናል ። ደም የሚፈስበት አገር ማንም አይቀርበውም ። በላዬ ላይ በተነደለው የደም ጎርፍ ምክንያት ንብረቴን አጥቻለሁ ። ደም የሚፈስበት ምድር ድህነት ይውጠዋል ። ብዙ ጠቢባን መፍሰስ የጀመረውን ደም ማቆም አልቻሉም ። እንዲሁም በምድር ላይ የሚፈሰውን ደም የትኛውም ጠቢብ ሊያቆመው አይችልም ። ደም በደም አይጠራም ። ነገር ግን ሰው ደም ያፈስሳል ። ደም በምድር ላይ እንዳይፈስ አንድ ሰውም እንዳይጎዳ መጠንቀቅ ይገባል ። ያለፈውን ዘመን የደም ዋጋ ሳንከፍል ሌላ መጨመር የለብንም ።
በምድር ላይ የሚፈሰው ደም ምክንያቱ የክርስቶስ ሰላም መታጣቱ ነው ። ደስታዬንና ምቾቴን የነካኝ ያ ሰው ነው ሲል ይህኛው ወገን ደም ያፈስሳል ።ንጹሐን ስለማይጠነቀቁ በከንቱ ደማቸው ይፈስሳል ። ክፉዎች ግን ተጠንቀቅው ስለሚሄዱ በእነርሱ ምክንያቱ ብዙ ቤት ይፈርሳል ፣ ብዙ ሕንፃ ሥላሴ ይፈርሳል ። የሚፈሰውን ደም ቸል የሚል ወገን ራሱን የሚያስር ፣ ለነገ ዕዳ የሚያስቀምጥ ነው ። የሮማውያንን ወዳጅነት ፣ የገዥዎችን ፍቅር ተገን አድርጎ በሌላው መሞት መሳቅ የራስን ሞት በማይቀር ቀጠሮ መጠበቅ ነው ። ዳር ሲነካ መሐሉ ዳር ይሆናልና ።
እኔም ከተንጋለልሁበት ክርስቶስ ሲናገር ብድግ ብዬ እግሩ ሥር ወደቅሁ ። አሁንም ፊቱን ለማየት አልደፈርሁም ። እኔ የተደረገልኝን እርሱም ያደረገልኝን ያውቃል ። በምልአት ይሠራል ። እርሱ ጀርባ የለውምና በጀርባው ያለሁትንም ይባርካል ። የፊተኞቹን ያስተምራል ። የኋለኛዋን ይምራል ። ደቀ መዛሙርቱ ግን ከሕዝቡ ብዛት የተነሣ ልብሴን የዳሰሰኝ ማነው በማለቱ ተገረሙ ። ሕዝቡ ሲያጋፉህ እያየህ ፡- ማን ዳሰሰኝ ትላለህን አሉት ። ጌታ ግን የቆመው ለሚያጋፉት ሳይሆን ለሚዳስሱት ነው ። የሚያጋፉት የሚዳስሱት ላይ በር የሚዘጉ ናቸው ። ዓላማቸው ሆታ እንጂ ፈውስ አይደለም ። በግርግር ውስጥ ራሳቸውን የሚደብቁ በትልልቅ ጉባዔያት ዝግጅት የሚጠመዱ ናቸው ። ጊዜ ሰጥተዋል ፣ ራሳቸውን መስጠት ግን አይችሉም ። የሚያጋፉት ዜና ያገኛሉ ፣ የሚዳስሱት ግን ፈውስ ያገኛሉ ። እርሱ የሚያጋፉትን ከሚዳስሱት ለይቶ ያውቃል ።
ጌታ ወደ ኢያኢሮስ ቤት እየሄደ እኔን ለመፈወስ ቆመ ። ወደ ሹም ቤት እየሄደ ለድሀ የሚቆም ፣ ወደ ምኩራብ አለቃ እየሄደ ለኀጥእ የሚገኝ ፣ ወደ ሙት እየሄደ የቁም መከረኛን የሚያስታውስ እርሱ ብቻ ነው ። አሥራ ሁለት ዓመታት ከመቃብር በላይ ሳለሁ ከመቃብር በታች ካሉት በላይ ተረስቻለሁ ።ሙታንስ ይታሰባሉ ፣ እኔ ግን ተረስቻለሁ ። ከሞት የማይሻል ኑሮ እገፋለሁ ። ኑሮ ነው ካሉት መቃብር ይሞቃል ይባላል ። አንድ ሰው የሚጠይቀው ያጣ በሽተኛ አለ ። መቶ ሰዎች የሚቀብሩት ሙት ግን አለ ። ጌታ እግረ መንገዱንም የዘመናትን የደም ዥረት ገደበ ። እርሱ ለአጋጣሚ ቦታ ሳይተው ይሠራል ። ዓመታትና ዘመናት የተጫኑትን ታሪክ እንደገና ሕያው ያደርጋል ። ከመቃብር ሕይወት አውጥቶ ከሰው ቊጥር ይደምራል ። ከጫካ ጠርቶ ከነገሥታት ሰፈር ያውላል ።
ጌታ ዙሪያውን እየቃኘ እኔን መፈለግ ጀመረ ። የተፈወስኩት ሳያንሰኝ በአዋጅ ከተለየሁት ሕዝብ ሊቀላቅለኝ ካህኔ ተጋልኝ ። የተፈወስኩት ሳያንሰኝ ሊያመሰግነኝ የት አለች ? ማለት ጀመረ ። የተደረገልኝን አውቄአለሁና እየፈራሁና እየተንቀጠቀጥሁ ከእግሩ ሥር ወድቄ መናዘዝ ጀመርሁ ። እርሱ ግን በደል ማለት ከእኔ መራቅ እንጂ ወደ እኔ መጠጋት አይደለም በሚል ስሜት አበረታታኝ ። እርሱ ሥጋን ብቻ ሳይሆን ሕሊናንና መንፈስን ይፈውሳል ። ወደ ጌታ ስቀርብ እንዲህ ይሆናል ብለው ያልገመቱት ደቀ መዛሙርት በትንግርት ሊያዩኝ ጀመሩ ።
ጌታም ተናገረ ፡- “ልጄ ሆይ እምነትሽ አድኖሻል በሰላም ሂጂ ከሥቃይሽም ተፈወሺ” አለ ። እኔን እንደ ሰማ እናንተንም ይስማ ። የአገራችንን የደም ዝረት በቃ ይበል ። ለዘላለሙ አሜን ።
ተፈጸመ
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ