የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የአሳብ ውጊያ/2

ውስጣዊ መነጽር

ሰውን ሰው የሚያሰኘው አጭር ቁመቱ ፣ ጠባብ ደረቱ ሳይሆን ጊዜና ቦታ የማይወስነው አሳቡ ነው ። አሳቡ ከፍ ብሎ እስከ ጽርሐ አርያም ፣ ዝቅ ብሎ እስከ እመቀ እመቃት የሚወርድ ፣ ከአድማስ አድማሳት በክንፍ የሚበርር ነው ። አሳብ ሰውን ውስን ሳለ ምሉዕ በኵለሄ ፣ ጠባብ ሳለ ስፉሕ ፣ ድኩም ሳለ ኃያል ያደርገዋል ። ከወንበር ሳይነሣ ዓለምን ያዞረዋል ። የትላንቱን በትዝታ ፣ የነገን በተስፋ እንዲያስብ ያደርገዋልና ሰው በአሳቡ ከጊዜ ውጭ ይሆናል ። ከዛሬ ሺህ ዓመት በፊት ከነበረው ሰው ጋር እንዲያወጋ ፣ ወደፊት ሺህ ዓመት ተራምዶ እንዲያስብ ያደርገዋል ። በመንግሥተ ሰማያት ርስት ፣ በዘላለም ውስጥም ይዋኛል ። በአሳቡ ብዙ እየሰፈረ ለወዳጁ ይሰጣል ፣ የጠላውንም ሰው ችሎት ሰይሞ ይቀጣል ። ነገሥታት ጉልበቱን ቢገዙ የሰውን ልቡን መግዛት ግን ይከብዳቸዋል ። ልቡ የእግዚአብሔር ከተማ ፣ የራሱም እልፍኝ ነው ። የልብ ቁልፍ ያለውም በእግዚአብሔርና በባለቤቱ እጅ ነው ። ሰው አቅፎት ለሚተኛው ሌላ ሰውም ስውር ነው ። ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ ራሱ ራሱን ሳያውቀው ሊሞት ይችላል ። እንደውም ስለ ራሱ ካለው እውቀት ስለ ሰው ያለው እውቀት ይበልጣል ።

እግዚአብሔር ሰውን “ልብህን ስጠኝ” ማለቱ አንተ ብቻ የምታዝዝበትን ማንነትህን አስረክበኝ ማለቱ ነው ። በልብ ከተማ የሚነግሥ እግዚአብሔር ብቻ ነው ።

አሳብ ይህን ያህል ኃያል ሲሆን ፣ አሳብ ግዙፉን ሥጋ ሲጫነው ደግሞ እጅግ የሚከብድ የብረት ሸክም ነው ። አሳብ እንደ ጦርነት ይሆናል ። አንዱ ሰው ለሁለት ተቧድኖ ይፋጃል ። በመሠረቱ ውጫዊ ጦርነት መነሻው ውስጣዊ ጦርነት ነው ። ሰላም ያለው ሰላም ይሰጣል ። ልብና ልብ ፣ አሳብና አሳብ ሲጣሉ ተዉ ማለት ያስቸግራል ። ሁሉም የራስ ነውና ሁሉም በጀ አይሉም ። አሳብ እንደ ሕፃን ልጅ ነው ። ሁሉ ቤት ካልገባሁ ይላል ። የእግዚአብሔር መንፈስ ደግሞ ትኩረትህን ራስህ ላይ አድርግ ብሎ ይገሥጸዋል ። ምድራዊ ሞግዚት አሳብን መጠበቅ አይችልም ። መንፈስ ቅዱስ ብቻ አሳብን በቀና መንገድ መምራት ይችላል ። አሳብ እልከኛ ነውና እሹሩሩ ባሉት ቍጥር ልቅሶን ይጨምራል ። አንድን ነገር ላለማሰብ በሞከርን ቍጥር የበለጠ እያሰብነው እንመጣለን ። አሳብ የሚሻረው በሌላ አሳብ ነው ።

አሳብ በአሳብ ሳጥን ውስጥ ከትቶ ያፍነናል ። ሕፃን ልጅ እንደሚገድል አያውቅምና አፍንጫችንን ግጥም አድርጎ ይዞ ስንጨነቅ ይስቃል ። አሳብም አስጨንቆ ይዞን ልቀቀኝ ብንለው ይሳለቅብናል ። አሳባችን የብዙ ነገሮች ምርኮኛ ሁኖ ይውላል ። የምኞታችን ፣ የቂማችን ፣ የሰማነው ክፉ ነገር ፣ የፍላጎታችን ፣ የመንፈሳዊነታችን ፣ የዓለማዊነታችን ፣ የሰይጣን ምርኮኛ ሁኖ ሊውል ይችላል ። እነዚህ ሁሉ የአሳብ ገዥዎች ሲሆኑ መልካሙ ገዥ ግን እግዚአብሔር ብቻ ነው ።

“ባሮክ ሆይ ፥ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይልሃል ። አንተ፡- እግዚአብሔር በሕመሜ ላይ ኀዘንን ጨምሮብኛልና ወዮልኝ ! በልቅሶዬ ጩኸት ደክሜአለሁ ፥ ዕረፍትንም አላገኘሁም ብለሃል ።… ለራስህ ታላቅን ነገር ትፈልጋለህን ? በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ ፥ እነሆ ፥ ክፉ ነገርን አመጣለሁና አትፈልገው ፥ ይላል እግዚአብሔር ነገር ግን በሄድህበት ስፍራ ሁሉ ነፍስህን እንደ ምርኮ አድርጌ እሰጥሃለሁ ።” ኤር. 45 ፡ 2-5 ። የእግዚአብሔር ሰዎች ሁሉ የአሳብ ሰልፍ ውስጥ አልፈዋል ። ብዙ የምንመኛቸው ነገሮች ቢሆኑ የአሳብ ውጊያውን ያበዙት ይሆናል እንጂ አያበርዱትም ። የዚህ ዓለም መልስ ፣ ተመልሶ ጥያቄ ይሆናል ። የማጣትን ያህል ማግኘት ፣ የመሐንነትን ያህል መውለድ ጥያቄ የሆነበት ብዙ ሰው አለ ። በዚህ ሁሉ ውስጥ ግርታና መደናበር እንዳይፈጠር እግዚአብሔር ነፍስን ምርኮ አድርጎ ይሰጣል ። ነፍስን ምርኮ አድርጎ የሚሰጠውም እንደ ቃሉ ለሚሄዱና አገልጋዮችን እንዳይደክሙ ለሚያበረቱ ነው ። ባሮክ እንዲህ ያለ ሰው ነበርና ። ምርኮ ከኋላው ጦርነትና ድል አለ ። እግዚአብሔር ጦርነቱንም ድሉንም ፈጽሞ ምርኮ ይሰጣል ።

የሕይወትና የኑሮ ዘይቤ መነሻው አሳብ ነው ። አሳብ በፍልስፍና ሲቃኝ ግዴለሽ ፣ በሥጋዊነት ሲቃኝ ስግብግብ ፣ በዘረኝነት ሲቃኝ ገዳይ ፣ በፍቅረ ንዋይ ሲቃኝ ምሕረት የለሽ ይሆናል ። አሳብ መልካም ዜማ የሚኖረው በእግዚአብሔር ፍርሃት ሲቃኝ ብቻ ነው ። የንስሐ ጸሎታችንም “ላለፈው ስርየት ፣ ለሚመጣው ንጹሕ ልብን”ን የሚለምን ነው ። አሳብ ንጹሕ ካልሆነ ግባችን አስፈሪ ነው ። ነቢዩ የጸለየው ትልቅ ጸሎት፡- “አቤቱ ፥ ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ ፥ የቀናውንም መንፈስ በውስጤ አድስ” የሚል ነው ። መዝ. 50 ፡ 10 ። የቀና መንፈስ በልጅነታችን የነበረን ፣ ወደ እግዚአብሔር ቤት በመጣን ሰሞን የተጎናጸፍነው ነበር ። የቀና መንፈስ ከሌለን በራሳችን ግምትና ትርጉም እየተሰቃየን እንመጣለን ። ሰው ራሱን አስሮ የሚያሰቃይበት እስር ቤት ጠማማ አስተሳሰብ ነው ።

ፀሐፊው ጆርጅ በርናርድ ሻው፡- “ልብህን ብሩህ አድርገው ዓለምን የምትመለከትበት መስኮት ነውና” ብሏል ።

ይቀጥላል

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ