መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » የአሳብ ውጊያ » የአሳብ ውጊያ /3

የትምህርቱ ርዕስ | የአሳብ ውጊያ /3

የአሳብ መደፍረስ

ንጹሕ ጅረት በመንገድ ሳለ ጎርፍ ተቀላቅሎት ፣ ቆሻሻ ገጥሞት ድንገት እንደሚቆሽሽ አሳብም ድንገት የሚበከልበት ጊዜ አለ ። አሁን ስለ ይቅርታ እያሰበ ወዲያው በቀልን ማሰላሰል ይጀምራል ። በፍቅር ልብ ደስ ብሎት መልሶ በጥላቻ ይታመሳል ። እግዚአብሔር የረዳው ሰው በአሳቡ ላይ የበላይ ይሆናል ። እውቀት ፣ አመክንዮ ፣ እምነት ፣ ፍቅር እንዲሁም ጸሎት አሳብን የሚዋጉልን ትልቅ መሣሪዎች ናቸው ። አሳብ ጦርነት ውስጥ የሚገባበት ጊዜ ብዙ ነው ። ወፍጮ ቤት ገብቶ ዱቄት አይንካኝ እንደማይባል በዚህ ዓለም ተገኝቶም የአሳብ መደፍረስ የማይገጥመው ሰው የለም ። በድንገት ስለ ራሳችን ፣ ስለ ሰዎች ፣ ስለ ዓለም ፣ ስለ ሕይወት ፣ ስለ እግዚአብሔር ያለን አሳብ ሊለወጥ ይችላል ። የማይቀጥል እንጂ የማይታወክ ማንም የለም ። ዛሬ ቀኑ ደስ ሲል ብለን ሳንጨርስ ብዙ የሚያስጨንቁ አሳቦች ይመጣሉ ። አንዳንዶቹ ምክንያት አላቸው ፣ ሌሎቹ ግን ያለ ምክንያት የሚበጠብጡን ሊሆኑ ይችላሉ ። ብዙ ሰው ከውስጣዊ ሕመሙ በላይ ምክንያቱን አለማወቁ ያሳዝነዋል ።

በኢዮብ መጽሐፍ፡- “በምድር ላይ የሰው ሕይወት ብርቱ ሰልፍ አይደለምን ? ወራቱም እንደ ምንደኛ ወራት አይደለምን ?” ይላል ። ኢዮብ. 7 ፡ 1 ። ሕይወት ጦርነት ከሆነች እንደ ወታደር ታጥቀን ልንጠብቃት ይገባል ። ሕይወት ብርቱ ጦርነት የሆነችው በዚህ ምድር ነውና ሁሉ በማለፉ ልንደሰት ይገባል ። ምንደኛ ደመወዙ በቀን የሚለካ ነው ። ለአንድ ሠራተኛ ቀኑ ሳያውቀው ይመሽለታል ። ሳናስበው አርባና ሃምሳ ዓመት ይሞላናል ። የጦርነት መጨረሻ ጦርነት ሁኖ አያውቅም ። አንድ ቀን ዕረፍትና ሰላም አለ ። በአሳብ ፍልሚያ ውስጥ የሚያልፉ ሰዎች ብዙ ዓይነት ስሜት ይፈጠርባቸዋል ። ከራሳቸው ጋር ክርክር ውስጥ ይገባሉ ። በሠሩት ክፉ ሥራ ብቻ ሳይሆን ባደረጉት መልካም ነገርም ይጸጸታሉ ። አንዳንድ ጊዜ ክልብስ የሚል ረባሽ ስሜት ፣ ሆድን ባሕር ባሕር የሚያሰኝ ሁከት ፣ በቀትር የሚያንቀጠቅጥ ፍርሃት ይመጣባቸዋል ። ለማልቀስም አቅም የሚያጡበት ፣ ለሰው ለመናገር እብድ እባላለሁ ብለው የሚሰጉበት ጊዜ ጥቂት አይደለም ። ይህ ስሜት እየተሰማችሁ ይሆን ? በዚህ ዓይነት ስሜት ውስጥ ካላለፋችሁ አልኖራችሁም ማለት ነው ።

ይህን የአሳብ ውጊያ ታግሠው የሚኖሩ ፣ የእግዚአብሔርን የሰላም ቀን የሚጠባበቁ ብፁዓን ናቸው ። የአሳብ ውጊያውን መቋቋም ያልቻሉ ሰዎች አንደበታቸውን የመርዝ መርጫ ፣ እጃቸውን መግደያ ያደርጉታል ። ሕዝብን ከሕዝብ ሲያፋጁ የሚውሉ ፣ የጠብ ርእስ ከሌለ መኖር የማይችሉ የሚመስላቸው የአሳብ ውጊያቸውን በተገቢው መንገድ ማሸነፍ ያቃታቸው ሰዎች ናቸው ። እነዚሀ ሰዎች ሁሉም ነገር ጸጥ ካለ ከራሳቸው ጋር ስለሚገናኙ የሽብር ዜና መራዘሙን እንደ ፈውስ ያዩታል ። ሲለፈልፉ ራሳቸውን ለጊዜው ስለሚረሱ መጠነኛ እፎይታ ያገኛሉ ፤ አንዳንዶች ደግሞ በሱስ ውስጥ ይደበቃሉ ። ሱስ የሕልምና የቅዠት ዓለምን ይፈጥራልና ለጊዜው አየር ላይ ይንጎማለላሉ ። አዎ የአሳብ ውጊያ በተለያየ መንገድ ይመጣል ። ቀጥሎ ይህን ማየት እንጀምራለን ።

ይቀጥላል

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ

አዳዲስ መጻሕፍት

ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ

ለምድራችንና ለአገልግሎታችን በረከት የሆነ መጽሐፍ
የመጀመሪያ እትም ጥቅምት 2016 ዓ.ም

1ኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ – ክፍል አንድ

የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 2013 ዓ.ም

ምክር አዘል መጽሐፍ

የመጀመሪያ እትም