የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የአሳብ ውጊያ /4

1- የክስ ስሜት

ይህ ዓለም በጥፋታቸው ይቅርታ የማይጠይቁ ደንዳና ሰዎች ያሉበትን ያህል ያለ ጥፋታቸው ደግሞ በሰይጣን ክስ የሚሰቃዩ ደንባራ ሰዎች የሞሉበትም ነው ። ዓለምን ፍትሐዊነት የሚያሳጣት ይህ ይመስላል ። የክስ መነሻው ብዙ ነው ። ማንኛውም ውስጣዊ ክስ ግን ከሰይጣን ነው ። መንፈስ ቅዱስ ይወቅሳል ፤ ሰይጣን ደግሞ ይከስሳል ። ወቀሳ መነሻው ፍቅር ፣ መድረሻው የኃጢአተኛው መዳን ነው ። የክስ መነሻው ጥላቻ ፣ መድረሻው በደለኛውን ተስፋ ማስቆረጥ ነው ። የሕሊና ክስ ፣ የሰዎች ክስ ፣ ሰይጣን ክስ ያለበት ዓለም ነው ። እነዚህ ሦስት ከሳሾች በተጨበጠና ባልተጨበጠ ክስ ሊያሳድዱን ይችላሉ ። ሕሊናም ፣ ሰዎችም ሆኑ ሰይጣን ሊከስሱ ቢችሉም ይቅርታ መስጠት ግን አይችሉም ። የእግዚአብሔር ይቅርታ ከሕሊና ፣ ከሰዎችና ከሰይጣን ክስ በላይ ነውና እርሱ ይቅር ያለውን ማንም ሊከስሰው አይችልም /ሮሜ. 8 ፡ 33/። ያለፈው ስህተታችን ፣ የዛሬው ውድቀታችን ፣ የሚመጣው ስጋታችን ክርስትናችንን ልበ ሙሉ ሁነን እንዳንኖረው ያደርገናል ። ሰውን ሰው የሚያሰኘው እግዚአብሔርን በንስሐ ፣ የበደላቸውን ሰዎች ደግሞ በይቅርታ ክሶ የቀደመ ፋይሉን መዝጋት የቻለ ነው ። ያለ መበደልን ያህል በበደል መጸጸት ትልቅ ዋጋ አለው ። የንስሐ መንፈስ እምነትም ምግባርም ነው ። ንስሐ አያስፈልገኝም የሚል ደግሞ እምነትም ምግባርም የሌለው ከሀዲና ዓመፀኛ ነው ።

የጥፋተኝነት ስሜት ከባድ የሆነ ስቃይ ያለው ነው ። ጠላቶች ደጋግመው በሚሰጡን ክፉ ስም እውነት ያጠፋን የሚመስለን ጊዜ አለ ። ሰይጣን አንድን ነገር ደጋግሞ በማስወራት ያ ስሜት እንዲሰማን የማድረግ የውጊያ ስልት አለው ። ሌላ ጊዜም በምናደርገው መልካም ነገር ፍቅርን ለመግዛት ስንፈልግ የትዳር ጓደኛችንን ፣ ልጆቻችንን ያስቀየምን እየመሰለን የጥፋተኝነት ስሜት ውስጥ እንገባለን ። ኃይለኛና ሞገደኛ የሆኑ ሰዎች ጋር ስንኖርም የሁልጊዜ ቍጣቸው ራሳችንን እንደ በደለኛ እየቈጠርን እንድንኖር ያደርገናል ። አንዳንድ ጊዜ የትዳር ጓደኛችንና ልጆቻችን ይህን ደካማ ስሜታችንን ካወቁ ለማንበርከክና የፈለጉትን ለመቀበል ድራማ ይሠሩብናል ። ያኮርፉናል ፣ በር ዘግተው ይቀመጡብናል ፣ ስልክ አያነሡልንም ። በዚህ ጊዜ ያልበደልነውን መናዘዝ እንጀምራለን ። እየተለማመጥን በመኖር ከሰውነት ልክ ወርደን በውሻ ደረጃ እንገኛለን ። የሚገርመው ይህን ያህል መገዛት ለእግዚአብሔር አድርገን አናውቅም ። የሚያኖረን እግዚአብሔር መሆኑን ረስተን መኖራችን በሰው ላይ የተመሠረተ ከመሰለን ይህ እምነትን መጣል ነው ።

የሰው ታዛዥና ሎሌ የሆነው በክርስትና ትምህርት ተገርተን ከሆነ መልካም ነው ። ነገር ግን ሰዎችን ፈርተን ከሆነ ራሳችን ላይ ወጥመድ ይዘን እንዞራለን ። እነዚያን ሰዎች ካጣን ሕይወታችን የሚያከትም መስሎ እየተሰማን የሰው ጣዖት አቁመን እንሰግዳለን ። ይህ ፍርሃትና አለመረጋጋት ያመጣብናል ። እምነታችንን ወስዶ ዕራቈታችንን ያስቀረናል ። መኖር ግን በእግዚአብሔር ነው ። ሊሄድ የወደደውን በደስታ መሸኘት እንጂ እየሰገዱ መኖር ያንንም ሰው ማባለግ ነው ።

በክስ ስሜት ወይም በጥፋተኝነት ሕመም የሚሰቃዩ ሰዎች የአሳብ ውጊያ አለባቸው ። በትክክል አጥፍተው ከሆነ እግዚአብሔርን በንስሐ ፣ ሰዎችን በይቅርታ መቅረብ አለባቸው ። ሰው ሁኖ የማይበድል ፣ እንጨት ሁኖ የማይጤስ የለምና ። ቤተ ክርስቲያንም የተነሣሕያን ማኅበር እንጂ የፍጹማን ኅብረት አይደለችም ። በቤተ ክርስቲያን ያለው አገልግሎት በሙሉ ከስርየት ጋር የተያያዘ ነው ። ጸሎት ፣ ጥምቀት ፣ ቍርባን … የንስሐ አገልግሎት ነው ። ቤተ ክርስቲያን በደለኞች ባይኖሩባት ኖሮ የንስሐ ጸሎት በየሰዓቱ አታደርስም ነበር ። እነዚህ በጥፋተኝነት ስሜት የሚሰቃዩ ሰዎች አላጠፉ እንደሆነ ይቅርታ መጠየቅ አይገባቸውም ። ያለ ጥፋት ይቅርታ መጠየቅ ጥፋተኛ ሰውን ማባለግ ነው ። ለእውነት ዋጋ እየከፈልን እንጂ እውነትን እየሠዋን የምንመሠርተው ፍቅር ዕድሜ የለውም ።
በጥፋተኝነት ስሜት የሚመጣው የአሳብ ውጊያ ዋነኛ መሪው ሰይጣን ነው ። ሰይጣን ተከሳሹ ከሳሽ ነውና ልንፈራው አይገባንም ። በደላችን የእኛና የእግዚአብሔር ጉዳይ እንጂ የማንም አይደለም ። የእግዚአብሔር ፖሊስ ነን ብለው የሚያስቡ ሰዎችንም መፍራት አይገባንም ። መፍራት አንድ አምላክን ብቻ ነው ። በጥፋተኝነት ስሜት የሚመጣብን የአሳብ ውጊያ አለ ። መፍራት ፣ ሁሉም ሰው ጻድቅ ሁኖ እኛ ብቻ የረከስን መስሎ እንዲሰማን ያደርገናል ። ቤተ ክርስቲያን ብንሄድ ሰይጣን እንዳለበት ሰው የምንጮህ ፣ የእግዚአብሔር ሰዎችን ስንቀርብ ቀሚሳቸው የሚያቃጥለን መስሎ ይሰማናል ። መፍትሔው ስህተቱ ካለ ንስሐ ገብቶ መርሳት ነው ። ምክንያቱም እግዚአብሔር የረሳውን ማስታወስ ነውር ነውና ። ስህተቱ በሌለበት ያለ የአሳብ ውጊያ ግን ከሰይጣን ነውና በስመ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ከእኔ ራቅ ማለት ይገባናል ። ትላንትን ቢያስብ ሐዋርያው ጴጥሮስ ከሀዲ ነበር ። ሐዋርያው ጳውሎስ እስጢፋኖስን ያስገደለ ነው ። የትላንቱን ካልረሳን ወደፊት መዘርጋት አይቻልም ፊልጵ. 3 ፡ 13 ።

አቤቱ ልቡናችንን ግዛው!

ይቀጥላል

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ