የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የአሳብ ውጊያ /8

5 – የልጆች ማመፅ
የአሳብ ውጊያ ከሚያመጡ ነገሮች አንዱ የልጆች ማመጽ ነው ። ልጆች በአጉል መንገድ ላይ ሲጓዙ ወላጆች መታወክ ይጀምራሉ ። ለልጃቸው በሥጋው ብቻ ሳይሆን በነፍሱም ኃላፊነት እንዳለባቸው የሚሰማቸው ወላጆች ልጃቸውን ከእነርሱ ይልቅ ጨዋና ቅዱስ ሊያደርጉት ይመኛሉ ። ልጆች ምንም ልጅ ቢሆኑም በተፈጥሮ ነጻ ፈቃድ አላቸውና እስኪያምኑበት ድረስ እንቢ ሊሉ ይችላሉ ። ወላጆች በኃይልና በቍጣ አሳባቸውን ልጆቻቸው ላይ ቢጭኑ ልጆች በርግገው ለጊዜው ሊታዘዙ ይችላሉ ። ወላጆቻቸው በሌሉበት ስፍራ ግን የተከለከሉትን ነገር በእልህ ያደርጋሉ ። ከወላጆቻቸው ቤት ሲወጡና የራሳቸውን ኑሮ ሲጀምሩ ወላጆቻቸውን የጎዱ ይመስል ብዙ ማጥ ውስጥ ይዘፈቃሉ ። ልጆችን ስናንጽ እያስተማርንና እያሳመንን ሊሆን ይገባዋል ። ለልጆች መንገዱን እናሳያለን እንጂ አንራመድላቸውም ። በምንፈልገው ጎዳና ላይ በግድ ልናስገባቸው አንችልም ።

ልጆች የወላጆቻቸውን ምክር የማይከተሉበት ብዙ ምክንያቶች አሉ ። ወላጆቻቸው የወደቀ ሥነ ምግባር ይዘው ሲመክሩአቸው መቀበል ይቸግራቸዋል ። ምክንያቱም ልጆች የቃል ሳይሆን የተግባር ተማሪዎች ናቸውና ። የምንነግራቸውን ሳይሆን የምናደርገውን ይከተላሉ ። የልጆችን መልካምነት የምንፈልገው ለራሳችን ጥሩ ስም ተጨንቀን ፣ የእገሌ ልጆች እኮ … እንዲባልልን ከሆነ ልጆች ማፈንገጥ ይጀምራሉ ። ክፉና ደጉን ማሳየት እንጂ በተጽእኖ ልናተርፋቸው አንችልም ። ከምክር ከተማሩ እሰየው ፣ ካልተማሩ ደግሞ እኛ በተማርንበት ስብራት ይማራሉ ። “የእገሌ ልጅ እንዲህ ሆነ ይሉሃል” ፣ “እንዳታሰድበኝ” እያሉ ልጅን ማሳደግ ውጤታማ አያደርግም ። የብዙ አገልጋይ ልጆች መረን የሚሆኑት አባቶቻቸው ለስማቸው ብለው ጨዋ ሊያደርጉአቸው ስለሚሞክሩ ፣ ልጆቹ የራሳቸውን ኑሮ መኖር የተከለከሉ ስለሚመስላቸው ነው ።

አዳም የወደቀ ማንነት ውስጥ ሁኖ አቤልን ፣ ጻድቁን ሰማዕት ወልዷል ። ብዙ ባለጌ ሰዎች ጨዋ ልጅ ወልደዋል ። ነቢዩ ዳዊት ቡሩክ ሳለ ልጆቹ ግን መልካሞች አልነበሩም ። ልጅን በማየት ወላጆችን መመዘን ከንቱ ነው ። ስላልተቀጣ ነው እያልን እንፈርድ ይሆናል ። እግዚአብሔር ቀጥቶ ይስጥ እንጂ አድካሚ ነው ። ክፉ ወላጅ ሳይቀር ልጁ መልካም እንዲሆንለት ይፈልጋል ። ልጅ ግን በራሱ መንገድ ሊሄድ ይችላል ። የደርግ መንግሥት ትልቅ ባለሥልጣን የነበሩ አንድ ሰው ወኅኒ ቤት ተገናኝተን ስናወራ፡- “ልጅ እንደራሱ ነው ፣ መጽሐፍ ግን እንዳንተ ነው ። አሥራ ሁለት ልጆች ወልጃለሁ ፣ አንዱም የእኔን አሳብ አያንጸባርቅም ፤ ሁለት መጽሐፍ ጽፌአለሁ ፣ የእኔን አሳብ ያንጸባርቃል ። እባክህ መጽሐፍ መጻፍን አታቋርጥ” ብለው መክረውኛል ።

ልጆችን በሚመለከት የአሳብ ውጊያ የሚመጣው በግምት ነው ። በተለያዩ ዜና ማሰራጫዎች የምንሰማውን ክፉ ነገር ወደ ልጆቻችን አምጥተን ካሰብነው መጨነቅና ልጆቹንም ነጻነት ማሳጣት እንጀምራለን ። ከእኛ ስም ይልቅ የልጆቹ ሕይወት ሊያሳስበን ይገባል ። ሁሉም ልጅ ወላጅ አለውና የእኛ መንሰፍሰፍ አለማመን እንጂ ርኅራኄን አያመለክትም ። ልጆቻችን በየዕድሜአቸው ላይ የሚለዋወጥ ጠባይ አላቸው ። ያንን መረዳትና በትዕግሥት ማሳለፍ ልጆችን ገንዘብ ለማድረግ ይረዳል ። በጣም መጫናችን ለእኛ ብለን ቅዱስ የምናደርጋቸው ይመስላቸዋልና ተወት ማድረጋችን እንዲያስቡ ያደርጋቸዋል ። “በዚህ ውስጥ የምፈራው ነገር ቢሆንስ” የሚል ጭንቀት ይከበን ይሆናል ። የሚሆነው ሁሉ ሲሆን የነበረ ነው ። ብቻ የተጸለየለት ልጅ አይወድቅም ። ቅድስት ሞኒካ ስለባካናው ልጅዋ ስለ አውግስጢኖስ በጣም ታለቅስ ነበር ። ቅዱስ አምብሮስም ፡- “አንቺ ሴት ይህን ያህል እንባ ያፈሰስሽለት ፣ በጸሎት የተማፀንሽለት ልጅ ጠፍቶ የሚቀር ይመስልሻልን ? በፍጹም ዓመፀኛው ልጅሽ አንድ ቀን በእግዚአብሔር ፍቅር ልቡ ተሸንፎ እውነት ፣ ሕይወትና መንገድ ወደሆነው ወደ ጌታችንና መድኋኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይመጣል” ብሏት ነበር ። በርግጥም ታላቅ ቅዱስ ፣ ሰባኪና ፈላስፋ የሆነው ቅዱስ አውግስጢኖስ የእናቱ ጸሎት ፍሬ ነበር ።

የአሳብ ውጊያ ውስጥ ከምንገባበት ነገር አንዱ ልጆች ለእነርሱ ብለን ያደረግነውን መልካም ነገር ክፉ ትርጉም ሲሰጡት ፣ አቅማችን ሲደክም ለወቀሳና ከሰሳ ሲመጡ ፣ ትክክል አይደላችሁም ብለው ሲያጣጥሉን ትልቅ ስብራት ሊገጥመን ይችላል ። ብዙ ወላጆች የመጨረሻው ተስፋ መቍረጥ የሚያገኛቸው ልጆቻቸው ሲነቅፏቸው ነው ። “ልጄ እንዲህ ካለኝ ከሌላ ምን እጠብቃለሁ ?” የሚል አስተሳሰብና የአሳብ ውጊያ ውስጥ ይገባሉ ። የሚበዙት ወላጆች በመንፈስ ጭንቀት ውስጥ እንደሚያልፉ ልጆች አይረዱም ። የልጆችን ወቀሳ በቀላል መንገድ ለመቀበል ራስን ማዘጋጀት አለብን ። በአንድ ወቅት አምስተኛውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስን አንድ ጥያቄ አቀረብሁላቸው ። ጥያቄው “ብዙ ሰዎች ስለ እርስዎ የሚናገሩት ክፉ የሚመስል ንግግር አለ ፣ በዚህ ይከፉ ይሆን ወይ ?” አልኳቸው ። “ይኸውልህ ልጄ እስከ ዛሬ ድረስ የኖረው እውነት አባት ትክክል ፣ ልጅ የተሳሳተ ነው ተብሎ ነው ። አሁን ግን አባትም ሊሳሳት ይችላል የሚል አስተሳሰብ ላይ መድረስ አለብን ። ስለዚህ ማንም ቢነቅፈኝ ተሳስቼ ሊሆን ይችላልና ራሴን ስላሳየኝ ያን ሰው እወደዋለሁ ፣ እቀበለዋለሁ” ብለውኛል።

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ