የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የአሳብ ውጊያ/9

6- ያለ መፈለግ ስሜት

የአሳብ ውጊያ ከሚያመጡ ነገሮች አንዱ ያለ መፈለግ ስሜት ነው ። ያለ መፈለግ ስሜት በተለያየ መንገድ ሊመጣ ይችላል ። አንዳንድ ሰዎች ከመሬት ተነሥተው “ሁሉ ሰው አይወደኝም ፣ ማንም አይፈልገኝም” የሚል ስሜት ውስጥ ይገባሉ ። እነዚህ ሰዎች የመሰላቸውን ነገር ከእውነቱ ለመለየት ጊዜ ያጣሉ ። ለራስ በማዘን ራሳቸውን የተንከባከቡ ይመስላቸዋል ፤ ለራስ ማዘን ደስ የሚል ስሜት ያለው ሲሆን ቆይቶ ግን ባዶነት እንዲወረን ያደርጋል ። አንዳንድ ሰዎችም የሌሎችን ኀዘኔታ በመናፈቅ ወላጅ እያላቸው የለኝም ፣ ወገን እያላቸው ምንም ዘመድ የለኝም በማለት ይናገራሉ ። ብዙ ጊዜ ስለሚናገሩት ይህን ነገር እያመኑት ይመጣሉ ። ይልቁንም በቤተሰቤ አድልኦ ተደርጎብኛል ብለው የሚያስቡ ሰዎች በዚህ ንግግር ይጠመዳሉ ።

ያለ መፈለግ ስሜት በሚያምኗቸው ሰዎች በመከዳት የሚመጣ ነው ። በሕይወት ውስጥ ዛሬ አብረውን ያሉ ሰዎች ነገ ባሻገር ቆመው ሊተኩሱ ይችላሉና ያንን መጠበቅ መልካም ነው ። የዓለም መልኳ ፍቅር ብቻ ሳይሆን ጥላቻም ነው ። የሰው ልጅ በኃጢአት ወደቀ ስንል ከፍቅር ወደቀ ማለታችን ነውና ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የወረት ባሪያ ሁኗል ። ወረት ያልበደሉንን ሰዎች መሸሽ ነው ። ወረተኞች ሌላውን የሚጎዱ ብቻ ሳይሆን ራሳቸውም ይጎዳሉ ። የሚፈልገንን የምንሸሽበት ዓለም ቢሆንም የፈለግነውም የሚሸሸን ዓለም ውስጥ ነን ። እዚያ የምናጭደው እዚህ የዘራነውን ነው ። አንዳንድ ሰው በመጀመሪያ ትዳሩ የዘራውን በሁለተኛው ትዳሩ ያጭደዋል ። ሰው ቅድሚያ መውደድ የነበረበት የሚወደውን ሰው ነው ። የጨበጠውን ጥሎ የሄደውን ነፋስ ለመጨበጥ ይሮጣል ።

ያለ መፈለግ ስሜት የትዳር ጓደኛ ሌላ ኑሮ ሲጀምር የሚጫጫን ስሜት ነው ። ቃል ኪዳኑን ውኃ ሲበላው ፣ በድህነት የቆየው ፍቅር በበረከት ሲፈርስ ብዙዎች ግራ ይጋባሉ ። አንዳንድ ዘማ የሆኑ ሰዎች ቤቱን ጥለው ይሄዳሉ ። ሌሎቹ ግን በቤት ውስጥ ያለውን የትዳር ጓድ እንደሌለ ቆጥረው በድፍረት ዘማነታቸውን ይቀጥላሉ ። ቤት የያዘውን ምሥጢር እግዚአብሔርና የሃይማኖት አባቶች ከድነውት እንጂ ብዙ ዘግናኝ ታሪክ አለ ። ያለ መፈለግ ስሜት የትዳር ጓዶችን ካለመረዳት ይመጣል ። በትዳር ውስጥ የሚታየው የጠባይ ለውጥ ሁልጊዜ ወረት አይደለም ፣ የአእምሮ ጭንቀትም ይሆናል ። የትዳር አንድነት ግላዊ ማንነትን የሚያስቀር አይደለም ። ያ ሰው ትዳሩ ጥሩ ቢሆንም ሕይወት ግን ለእርሱ ጦርነት ሁናበት ይሆናል ። ትዳር ፣ የትዳር ጥያቄ መልስ እንጂ የሁሉም ነገሮች መልስ አይደለም ። ራሱን ማራቅ ፣ መነጫነጭ ፣ መቆጣት የጀመረ የትዳር አካል ካለ እኔ ስላልተፈለግሁ ነው ከማለት ያልተፈታ ጠብ ወይም የሚያልፍበት የሕይወት ውጣ ውረድ እንዳለ ማሰብ ተገቢ ነው ። ምንጩ ካልተገኘ ፈውሱ ይዘገያል ።

የጎረቤት ሰው ሰላም ሳይለን ቢያልፍ “ልብ አላለኝም” እንላለን ፣ ሲቆጣን “የተናደደበት ነገር ቢኖር ነው” እንላለን ። ጠባዩ ሲለወጥ ኑሮው አልተመቸው ይሆናል ፣ ይለፍለት” ብለን ጊዜ እንሰጠዋለን
። ይህንን ቅንነት ግን ለትዳር ጓዳችን አለማሳየታችን የሚገርም ነው ። ብዙ ኑሮ እየተናጋ ያለው ከምናይበት መነጽር እንጂ የእኛ የትዳር ጓዶች ክፉ ሁነው አይደለም ። እንደውም የተሻሉ ናቸው ።

ያለ መፈለግ ስሜት ልጆች የራሳቸውን ኑሮ መኖር ሲጀምሩ የሚከሰትም ነው ። ልጆች ከቤት ወጥተው ወደ ትምህርት ተቋማት እንደገቡ በገጠማቸው ዓለም ግር በመሰኘት አሊያም አዲሱን ዓለም ባለመጥገብ ወላጆቻቸውን ፍጹም ይረሳሉ ። ወላጆቻቸው ትዝ የሚሏቸው ገንዘባቸው ማለቅ ሲጀምር ነው ። በዚህ ጊዜ ወላጆች “ልጄ እንኳ ተወኝ ፣ አሳድጌ ስልክ ለማንሣት እንኳ ተፈተነ” በሚል ያለ መፈለግ ስሜት ውስጥ ይገባሉ ። “ትምህርትህን ይግለጽልህ” ብለን የመረቅነው ኮሌጅ ሲገባ ፣ “አግባ ፣ አግባ” ያልነው ሲያገባ ታግሦ ማለፍ እንጂ መልሶ መራገም ጥቅም የለውም ። ልጆች የወላጆችን ፍቅር መገንዘብ የሚጀምሩት ወላጆች ለቀቅ ሲያደርጓቸው ነው ። ልጅ ጥላ ነው፣ ሲከተሉት ይሸሻል ፣ ሲሸሹት ይከተላል ። ብዙ ጊዜ የግዴለሽ ልጆች ወላጆቻቸውን በጣም ይወዳሉ ።

ያለ መፈለግ ስሜት ለመጠናናት ብለው የጀመሩት ጓደኝነት ሲፈርስ ሊመጣ ይችላል ። የመጠናናት ወቅት ጊዜን እንጂ ሌላ ነገርን የሚካፈሉበት አይደለም ። በቅጡ ካሳለፉ ሲለያዩም ያን ያህል አይከብድም ። መላመድ ፍቅር እየመሰለ ያደናግራል ። በእጮኝነት ጊዜ የሄደው ሰው ጊዜን አትርፏል ። በትዳር ሰዓት ቢሄድስ ? ብሎ ማሰብ ያጽናናል ። ያለ መፈለግ ስሜት ዕድሜ ሲገፋ ፣ የሞቀው ቤት ጭር ሲል ፣ ጉልበት ሲከዳ ፣ በሽታ ሲያጠቃ የሚመጣም ነው ። ይህ ስሜት ከፍተኛ የሆነ የአሳብ ውጊያ ያመጣል ። ሰዎች ፈልገውን ቢመጡ ቀበሌ አቋርጠው ነው ። ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከድንግል ተወልዶ የፈለገን ወዳጅ አለን ። ሰዎች የከበቡን በመሰለን ሰዓትም የነበረው ፣ ዛሬም ጭር ሲል ያለው አማኑኤል ብቻ ነው ። የስሙ ትርጓሜ እግዚአብሔር ምስሌነ – እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው የሚል ነው ።

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ