የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የአባትነት ስሜት

በዮርዳኖስ ልጅነትን የምታሰጥ ጥምቀት ተመሠረተች ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወልደ አብ መሆኑ ተመሰከረ ። አብ ስለ ልጁ ይናገራል ። ልጁም ስለ አባቱና ስለ ባሕርይ ሕይወቱ ስለመንፈስ ቅዱስ ይናገራል ። መንፈስ ቅዱስም ስለ ወልድ ይናገራል ። በሥላሴ መንግሥት አንዱ አካል ስለ ሌላው አካል ይናገራል ። የሥላሴ መንግሥት የፍቅር መንግሥት ነው ። አንዳችን ስለ አንዳችን በጎ ስንናገር ፍቅር ይገለጻል ። ፍቅርም ይጸናል ። ወዳጅ ለወዳጁ አምባሳደር ነው ። አምባሳደር ስለ ራሱ ሳይሆን ስለ ላከው አገርና መንግሥት በፍጹም ጽናት ይመሰክራል ። እኛም ስለ ራሳችን ብንናገር ክብር አይሆንልንም ፣ ስለ ሌሎች መመስከር አለብን ። ደግነትም ዋጋው የሚከብረው በተቀባዮቹ ሲነገር ፣ ዋጋውን የሚያጣው በሰጪው ሲወራ ነው ።

ልብ ቃልን ቢልከው አልበለጠውም ፣ ያለ ቃል ልብን ማወቅ አይቻልም ። ቃልም ልብን መሠረት አድርጎ ፣ ከልብ ሳይለይ ይገለጻል ። ቃልን የሰማ ልብህን አሳየኝ አይለም ። ልብ በቃል ይታወቃል ። ቃል ከልብ ይወለዳል እንጂ ልብ ከቃል አይወለድም ። አብ ልብ ነው ፣ ወልድም ቃል ነው ። አብ መላኩ ልብ ቃልን ስለሚልክ ነው ። በሥላሴ መንግሥት መላክና መላክ ድርሻንና ፍቅርን እንጂ የክብር ብልጫን አያሳይም ። አብን ያወቅነው በወልድ ነው ። በዮርዳኖስ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ሲወርዱ አብ ግን በደመና ሆኖ ተናገረ ። ልብ ከስፍራው ሳይናወጥ ቃሉን እንደሚልክ አብም በስፍራው ሁኖ ወልድን ይልካል ። አብ አባት መሆኑ ቃል ከልብ ስለሚወለድ ነው ። ቃል ከልብ ለቅጽበት ሳይለይ ይወጣል ። የወልድ ልደትም ተከፍሎ ወይም መለየት የሌለበት ነው ። በዚህም ከምድራውያን ልደት ልዩ ነው !

እግዚአብሔር የሰው ልጅን በልጅነት ማዕረግ ፈጠረው ! ሊያድነው በመጣ ጊዜም የልጅነት ጸጋውን መለሰለት ። አባወራ የቤቱን አባላት በሙሉ እንደ ልጅ ማየት አለበት ። ካህን ምእመናንን እንደ ልጅ ማየት አለበት ። ንጉሥም ሕዝብን እንደ ልጅ ማየት አለበት ። የአባትነት ልብ ከሌለ መሪነት ጨካኝነት ይሆናል ። ሁሉም የቤተሰብ አባላት በአባታቸው ሥራ ባይረኩ አባትነቱን አይጠራጠሩም። አባትነትና ልጅነት አይለወጥም ። መሪዎችም ሕዝባቸውን እንደ አብራክ ክፋይ ማየት አለባቸው ። ባዕድ ንጉሥ አይሆንም ፣ ንጉሥ ሁሉ ከሕዝቡ የወጣ ነው ። ስለዚህ መሪና ተመሪ በሥጋና በደም የተሳሰሩ ቤተሰብ ናቸው ። እግዚአብሔር ልጅነት ሰጠን ፣ ልጁንም ወደ ዓለም ላከ ። መሪዎች አባታዊ ስሜት ፣ ተመሪዎች የልጅነት መንፈስ ካልያዙ የዚህ ዓለም ስቃይ አይወገድም ።

ዘመናዊነት “መሪ አገልጋይ ነው” የሚል አስተሳሰብ አምጥቷል ። የሕዝቦች ነጻነትም መሪያቸውን በመስደብ የሚገለጽ ሆኗል ። መሪ አገልጋይ ከሆነ የኮንትራት ሠራተኛ ነው ማለት ነው ። የኮንትራት ሠራተኛ ለታሪኩም ለክብሩም አይጨነቅም ። ስለዚህ የዚህ ዘመን መሪዎች ፆታን የሚያዛቡ ፣ አደንዛዥ ዕፅን የሚፈቅዱ ፣ ለትውልድ ነውርን ሕግ አድርገው የሚፈቅዱ ናቸው ። በዚህ ዘመን ያሉ የዐረብ አገር ነገሥታት ቢያንስ ሕዝቡን እንደ ንብረታቸው ይጠብቁታል ። የመጀመሪያው ንጉሥ አዳም ግን አባት ነበረ ። የኮንትራት ሠራተኛ ፣ ሕዝቡንም እንደ ንብረቱ የሚጠብቅ አምላክ አከል ንጉሥ አልነበረም ። እግዚአብሔር የፈቀደው መሪነት አባትነት ያለበት ነው ። መሪ በመጨረሻ ሕዝቡን መርቆ ይሄዳል ። ሕዝቦች መሪዎችን እንደ አባት፣ መሪዎችም ሕዝብን እንደ ልጃቸው እንዲያዩት ይህ ዘመን ይናፍቃል ። አንተ አባወራ ፣ አንተ ካህን ፣ አንተ ንጉሥ የአአላፍት አባት አድርጎሃልና ደስ ይበልህ ! ልጅ ጠፋ ስትሉ አባት ሆነናል ወይ ? ብላችሁም ራሳችሁን ሞግቱ !

ይቀጥላል
የካቲት 8 ቀን 2016 ዓ.ም.
ዲ/ አሸናፊ መኰንን

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ