የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የአዞ እንባ


በተለምዶ “የአዞ እንባ” ሲባል እንሰማለን ። አዞ ጥቅጥቅ ባለው ቆዳው አማካይነት ላብ ስለማይወጣው በዓይኑ አማካይነት ላቡ እንባ መስሎ ይፈስሳል ። ከ62 እስከ 66 በሚጠጉት ጥርሶቹ ሥጋ የሚቆርጠው አዞ ተንቀሳቃሽ ምላስ የሌለው መዋጥ እንጂ ማኘክና ማላመጥ የማያውቅ ነው ይላሉ ስለ እርሱ ያጠኑ አዋቂዎች ። በዚህ ሰዓት ላይ ብዙ ሥጋ ቆርጦ ከዋጠ ጉሮሮው ስለሚጨናነቅ ላብ ያልበዋል ፣ ላቡም በዓይኑ በኩል ይፈስሳል ። የአዞ እንባ ላቡ ነው ። በብዛትም የሚታየው ሲበላ ነው ። አዞ እየበላ የሚያለቅሰው ላቡን ለማውጣት እንጂ አድኖ በመብላቱ ተጸጽቶ አይደለም ። እየበላ ያለቅሳል ፣ እያለቀሰ ይበላል ። አዞ ያስለቅሳል እንጂ አያለቅስም ። የዋሃን እንባውን አይተው ያለቅሳሉ ፣ እርሱ ግን ላቡን ያወጣል ። የአዞ እንባ ፈሳሽ እንጂ ስሜት የለበትም ። እንባው ደስታንም ኀዘንንም የሚገልጥ ሳይሆን ዓይኑ የላብ ቦይ በመሆኑ የመጣ ነው ። አስመሳይ ሰዎች ፣ እንባ ናልኝ እያሉ ሲጠሩት የሚመጣላቸው ፣ ቆየኝ ሲሉት የሚቆምላቸው ፣ በአጭር ቃል እንባ ሎሌ የሆነላቸው ፣ የውሸት አልቅሰው የእውነት የሚያስለቅሱ ሰዎች የአዞ እንባ የሚል ስያሜ ተሰጥቷቸዋል ።

ጠንካራ ማንነት ያላቸው ፣ ጥቅጥቅ ልብ የያዙ ፣ ለፍቅር ክፍተት የሌላቸው ፣ አድፍጠው መኖር ፣ የማያዩአቸውን እያዩ መሳቅ የሚፈልጉ ሥጋ በል የሆኑ ፣ ሰውን ካልጠለፉ ደስታ ፣ ካላጠፉ እንቅልፍ የሌላቸው ሰዎች በምድር ላይ አሉ ። አዞ መሰሏን ለመውለድ ብዙ ጥንቃቄ ታደርጋለች ። ፈሪሳውያን እንደ እነርሱ የከፉ ሰዎችን ለማምረት ቆላ ደጋ ይማስኑ ነበር ። ልፋት ሁሉ ልፋት አይደለም ። ዲያብሎስም ከወደቀ ጊዜ አንሥቶ ያለ ደመወዝ ይለፋል ። ውጤቱ ግን ለገሀነመ እሳት የሚያበቃ ነው ። ጌታችን፡- “እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን ፥ አንድ ሰው ልታሳምኑ በባሕርና በደረቅ ስለምትዞሩ ፥ በሆነም ጊዜ ከእናንተ ይልቅ ሁለት እጥፍ የባሰ የገሃነም ልጅ ስለምታደርጉት ፥ ወዮላችሁ” በማለት ገሥጾአል ። ማቴ. 23 ፡ 15 ። አዞ የተፈለፈሉ ልጆችዋን ባሕር ውስጥ ከመክተትዋ በፊት ትንንሽ ነፍሳትን እንዲበሉ ሣር ላይ ትተዋቸዋለች ። መሰላቸውን ከልጅነት ጀምሮ ክፋትን የሚያለማምዱ ፣ የክፋትን የዕድገት ሕግ የሚያከብሩ ፣ ለመኖር ሌላውን መግደል አለብህ በማለት ትውልድን የሚያሰለጥኑ ፣ እነርሱ ትልልቅ ገዳይ ሳሉ ልጆቻቸውን ትንንሽ ገዳይ አድርገው ፣ በልጆቻቸው ልክ የገሃነም ቀሚስን የሚሰፉ አያሌ ናቸው ። ስግብግብነት ሁሉም የእኔ ይሁን ባይነት እንደ ሰዎች ተፈጥረን እንደ አራዊት የምንኖርበት ጠባይ ነው ። እግዚአብሔር የመረጠልን ሰውነት ከጠዋቱ ሕጻንነትና መልአክነት የነበረው ነው ። ከእግዚአብሔር የተቀበልነው ገራም ተፈጥሮ ነው ። ያዳበርነውና የመረጥነው ግን አራዊታዊ ጠባይ ነው ።

አዞ በባሕር ፣ በየብስና በዛፍ ላይ መቆየት ይችላል ። ሁሉም ቦታ ላይ ግን የእኔ ነው ብሎ ሊተናኮል ይችላል ። ልካቸውን የማያውቁ ፣ ድምበርተኛ አልፈልግም ብለው ሁሉንም መጠቅለል የሚሹ ፣ የራሳቸውን የግላቸው ፣ የሌሎችን የእኔ ብለው የሚያስቡ ሰዎች በምድር ላይ መኖራቸው እርግጥ ነው ። አዞ ረሀቡን በቅጠል የማስታገሥ የማይችል ፣ ካልገደለ የማይበላ ነው ። ባልተገራ ፍላጎትም ለአንድ ሆዳቸው ሺህ ገዳይ የሆኑ ጨካኞች በምድር ላይ ከተከሰቱ ብዙ ዘመን ሁኗቸዋል ። ቃየንም መሪያቸው ሁኖ ይኖራል ።

ሕይወትን ለማጣጣም ፣ በልኩ እየኖሩ የቀኑን ሲሳይ ተቀብለው ለማመስገን የማይፈልጉ በመዋጥ ብዙ ተጨንቀው የሚያስጨንቁ በዚህች ዓለም ላይ ተከስተዋል ። የእኔ አሳብ ብቻ ይደመጥ የሚሉ ፣ የሌሎችን እምነትና ባህል ደፍጥጠው በማለፍ የሚረኩ አያሌ አሉ ። መደመጥ የሚፈልግ ሰው ማድመጥ አለበት ። ማድመጥ መቻል የሰውን የልብ ሰላም ማሳያ ነው ። ሰው ሲታወክ ማውራት ብቻ ይፈልጋል ። ራሱ ጣኦት ሲሆንበትም እኔ ካልኩት ውጭ አዲስ አሳብ የሚያመጣ ጠላቴ ነው ይላል ። ብዙ ሰብስበው ለመዋጥ ጉሮሮአቸው የተጨናነቀባቸው በዚህ ምክንያት የሚሰቃዩ አሌ የማይባሉ ናቸው ። መሰብሰብ ይቻላል ። መብላት ግን እግዚአብሔር ሲፈቅድ ነው ። አውሬ እንኳ ከጠገበ አይተናኮልም ፣ የሚያድነው በቂም ሳይሆን በረሀቡ ምክንያት ነው ። ሰው ግን ጠገብኩ የማይል ሁልጊዜ የሚስገበገብ መሆኑ አሳዛኝ ነው ። ይህ ዘመን የሚያስተምረን ነገር ቢኖር ንብረት ከንቱ መሆኑን ነው ። እግዚአብሔር የገንዘብን ትምክሕት ሊሰብር ቆርጦ ወጥቷል ። “በኪሱ ሳንቲም የሌለው ከሽፍቶች መንደር ሲደርስ ያቅራራል” ይባላል ። በዚህ ዘመንም ተረጋግቶ እየኖረ ያለው ምንም የሌለው ድሀው ነው ። ሲሰበስብ የታወከው ባለጠጋ ሊበላ ሲልም ሁከት ይገጥመዋል ። ብቻ ትምክሕት እንደዚህ ዘመን ቶሎ ቶሎ ሲፈርስ አልታየም ።

እንባ አንድ ትርጉም ብቻ ያለው ከመሰለን ሞኝነት ነው ። እንባ እንደ አዞ ጠባይ ከሆነ ላብ ማስወጣት ነው ። እንባ ፊልም የሚሠሩበት ፣ በሚያስለቅስ ቅባት የሚያለቅሱበትም ነው ። እንባ ደስታን መግለጫ ፣ ኀዘንንም ማውጫ ነው ። እንባ የሰዎችን ስሜት ወክሎ የሚታይ መልእክተኛ ነው ። እኔ ቀብር መውጣት አልቻልኩም አንተ ሂድልኝና ታይልኝ ብሎ ስሜት የሚልከው እንባን ነው ። ራሳቸው በድለው ራሳቸው የሚያለቅሱ ፣ በሁልጊዜ ትክክለኛነት ስሜት የሚኖሩ ፣ ዓለሙ ሁሉ በድሎ እኔ ብቻ ቀረሁ የሚሉ ፣ ጌታዬ ብለው የሚጠሩትን ባልም ይሁን አለቃ በእንባ ላሳምን የሚሉ ደካማ ሰዎች አሉ ። ሙሉ አካል እያላቸው ሠርተው መብላት ሲችሉ ነገር ምሰው ፣ ሰው አፋጅተው ይኖራሉ ። ሰው ያወቀባቸው ሲመስላቸው ዕድሌ ነው ብለው ያለቅሳሉ ። መኝታቸው ላይ ሆነው ለፍጅት የሚያነሣሡ ለራሳቸው ግን አካላቸውንና ጥቅማቸውን ጠብቀው የሚኖሩ፣ የአስመሳይነት እንባቸውን ግን ጊዜ ባመጣው መሣሪያ ቀርጸው የሚልኩ ዘመናዊ ነጋዴዎችን እናያለን ። አገራቸውን በዘፈን ብቻ የሚወዱ ፣ ወገናቸውን በከንፈር ፉጨት ብቻ እናዝንልሃለን የሚሉ የአዞ ዘመዶች አሉ ። አልቃሽ ራስዋ አታለቅስም ። ኩሏን ተቀብታ ልቅሶ ትወጣለች ኩሉ ሳይበላሽ ትመለሳለች ። ዓይንዋ ድንጋይ ከሆነ ሰንብቷል ። ደረቷን አትመታም ። የሰው ደረት ሲፈርስ ግን ደስ ይላታል ። አዞ እንባ ቢወጣውም እያለቀሰ አይደለም ። ቢያስለቅሰም አያለቅስም ። እየበላ በማንባቱ የሚያዝን የሚመስል ፣ እያለቀሰ በመብላቱ የምበላህ ላንተ ብዬ ነው የሚል አስመሳይ ነው ።

አስመሳይነት ፣ ዋሽቶ አዳሪነት የአዞ እንባን ይወልዳል ። እውነትን ዋስ መጥራት የማይችሉ እንባን “ቶሎ ናልኝ ፣ ልጠቃ ነው ፤ ድረስልኝ” በማለት የየዋሃንን ልብ የሚጠመዝዙ ፣ ደጉን ሰው ከሚወዳቸው ጋር እንዲጣላ ፣ ከልጅ ከሚስቱ እንዲለያይ የሚያደርጉ ሰብቀኞች የአዞ እንባ ተብለው ይገለጣሉ ። ቲያትራቸውን ሲጨርሱ የደስታ ሻማ የሚያበሩ ፣ እናትና ልጅ በማጣላት ግን የተጉ ብዙ ናቸው ። እውነተኛነትና “መኖር በእግዚአብሔር ነው” ብሎ ማመን ከአዞ እንባ ያድናል ። ጥገኝነት የአዞ እንባን ይወልዳል ፣ ጨካኝነትም የአዞን እንባ ያመጣል ፣ በልክ አለመብላትም የአዞን እንባ ይከስታል ።

አንድ አባባል አለ፡- “የውሸት ብንኖርም የምንሞተው ግን የእውነት ነው ።” የእውነት እንሞታለንና የውሸት አንኑር።

እግዚአብሔር በሰላሙ ይባርካችሁ ። አሜን ።

የብርሃን ጠብታ 22

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ኅዳር 15 ቀን 2014 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ