የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የአዳም ተስፋ

የበደለ አዳም ቀና ብሎ ይሄድ ዘንድ ዳግማዊ አዳም ሁኖ መጣ ፣ የስህተት በር የሆነችዋን ሔዋንን ያጽናና ዘንድ ክርስቶስ ከሴት ዘር ተወለደ ። ገነትን ላጣው አዳም ራሱ ክርስቶስ ገነት ሆኖለት መጣ ። ስጦታውን ቢያጣ ሰጪው ዘመዱ ሆነ ። ስጦታው የተፈጠረ ነው ፣ ሰጪው ግን ያልተፈጠረ ነው ። አዳም ሰማይና ምድር የእርሱ ቢሆኑ ያለ ጌታ ኀዘን እንጂ ደስታ አይሆኑትም ነበር ። የሰማይና የምድር ጌታ ለመሆን አስቦ ከሰይጣን ጋር መከረ ፣ እንኳን ሰማይን ሊያተርፍ ግዛቱ የሆነችውን ምድር አጣ ። ክርስቶስ ግን በመወለዱ የሚታየውን ብቻ ሳይሆን የማይታየውን ዓለመ መንፈስ ፣ ሰይጣንንና ደዌያትን ይገዛ ዘንድ ባለሥልጣን ሆነ ። ተጠቃን የሚሉ ወንድ ልጅ ሲወልዱ ስሙን ደምመላሽ ይሉታል ። ክርስቶስም ርስትን ይመልስልን ዘንድ ፣ ጠላትንም ይበቀል ዘንድ ወንድ ልጅ ሆኖ ተወለደ ። ክርስቶስ በወንድ አምሳል ስለ መጣ ወንድ ልጅ ክቡር ነው ። ክርስቶስ ከሴት ዘር በመወለዱ ከድንግል ማርያም የተነሣ ሴት ሁሉ ክብርት ናት ። የሄደችውን ገነት አዳም በእንባ ፣ አበው በምግባር ፣ ካህናት በመሥዋዕት ፣ ነቢያት በናፍቆት ሊያስመልሷት አልቻሉም ። ክርስቶስ ግን በመወለዱ የሰማይ በር ተከፈተ ። አዳም በወደቀ ቀን አጋንንት ዘፍነዋል ፣ ክርስቶስ በተወለደ ቀን መላእክት ዘመሩ ። ዛሬም በክርስቶስ ልደት የሚዘፍኑ ፣ የሚሰክሩ በአዳም የውድቀት ቀን ከተደሰቱ አጋንንት ጋር ይተባበራሉ ። አዳም ሳይወልድ በመበደሉ አንድ ራሴን ነኝ ብሎ ተመክቶ ነበር ። ነገር ግን የአባት ዕዳ ለልጅ ይተርፋልና ልጆቹ በደለኛ ሆኑ ። በአንዱ አዳም የተኰነኑ ፣ በአንዱ ክርስቶስ ጻድቃን እንዲሆኑ ፣ ሚዛንም እንዲተካከል ይህ ሆነ ።

አዳም በገደል ላይ በመጫወቱ ከጥልቁ ወደቀ ። ነገሥታትና ጠቢባን ከገደል ሊያወጡት አልተቻላቸውም ። ምድራዊ ሥልጣን ማዕሠረ ኃጢአትን ሊበጥስ ፣ ምድራዊ ጥበብም መቃብርን ሊበዘብዝ አልቻለም ። ክርስቶስ ግን ጠቢብ ድሀ ሆኖ መጣ ። ጌትነትን ተመኝቶ የሞተው አዳምን ፣ ክርስቶስ ክብርን ንቆ ሊታደገው መጣ ። የከፍታው ምሥጢር ዝቅታ መሆኑን ሊያስተምረው ክርስቶስ በበረት ተወለደ ። ሔዋን ደመኛው ሆና ብትታየው ፣ በእርስዋ ላይ ቢነሣሣባት የመዳኛውን ዘር ያጣው ነበረ ። አዳም ይቅርታ በማድረጉ ክርስቶስን አገኘ ። ከክርስቶስ የለዩን አንድ ዘመን ላይ ወደ ክርስቶስ ያቀርቡናል ። እግዚአብሔር ታሪክን ሲለውጥ ከበደሉን በላይ ይክሱናል ። ከቆሸሸው በላይ የሚያጸዳ ባለሙያ አለ ። ትልቁ ባለሙያ እግዚአብሔር ምድራዊት ገነትን ላጣው አዳም ሰማያዊ ርስትን ሰጠ ። በልጅነት ላይ ክህነትን ደረበለት ። መበቀል የፍጡር ጠባይ ነው ። እግዚአብሔር ግን ኃይሉን በይቅርታ ገለጠ ። ይቅር የሚሉ የሁልጊዜ ብርቱዎች ናቸው ። መግደል ብዙዎች ችለዋል ፣ ይቅር ማለት ግን አልቻሉም ። ይቅርታ የልዕልና መገለጫ ነው ። አባቶችን ከተቀየምን መጀመሪያ የምንቀየመው አዳምን ነው ። አዳም የወደቀባትን ቦታ ሳይሆን የተነሣባትን ጎልጎታ እናስታውሳለን ።

አዳም ገነትን በራሱ አጣ ፣ በክርስቶስ እንደሚያገኛት ተስፋ አደረገ ። ሰው ተስፋ ሰጥቶ ይጸጸታል ። እግዚአብሐር ግን ተስፋን እንደ ክብሩ እንጂ እንደ ዕዳ አያየውም ። አዳም መውደቅ በቻለበት አቅም መነሣት አልቻለም ። ያለ መካሪ የበደሉ ሰዎች በመካሪ ኃይል ሊነሡ ይቸገራሉ ። ሰውን ከኃጢአት የሚያላቅቀው ነጻ ፈቃዱ ከኃይለ መንፈስ ቅዱስ ጋር ሲዛመድ ነው ። አዳም በሰማይና በምድር ብቸኛ ሆነ ። ጥቂት ዘመን በደስታ ኖሮ 5500 ዘመን በስቃይ አሳለፈ ። አዳም አባት እናት አልነበረውም ፣ አባትና እናቱ እግዚአብሔር ነበረ ። አዳም ሙሉ ስሙ ሲጠራ “አዳም ወልደ እግዚአብሔር በጸጋ” ይባል ነበረ ። አባትና እናትህን አክብር የሚለውን ትእዛዝ አዳም ሻረ ። አዳም በገነት ውስጥ አነጋጋሪው ፣ የብቸኝነቱ መድኃኒት እግዚአብሔር ነበረ ። አሁን ግን ወዳጁን አጣ ። እግዚአብሔርም በወዳጁ ቤት ቆሰለ ። ክርስቶስ ሰው የሆነው ለአዳም ያለውን ፍቅር ለመግለጥ ፣ የወጣ እንደ ወጣ ይቅር የማይል አምላክ መሆኑን ለማስታወቅ ነው ።

አዳም የሠላሳ ዓመት ጎልማሳ ሁኖ ተፈጠረ ። ክርስቶስ ግን ሊያድነው የዕለት ሕፃን ሆኖ በበረት ተጣለ ። አዳም በገነት ብቻውን ነበረ እንጂ ብቸኛ አልነበረም ። ምክንያቱም እግዚአብሔር ያለው ብቸኛ አይባልምና ። አሁን ሔዋን አጠገቡ ሳለች ብቸኝነት ተሰማው ። ብቸኝነት ያለ ሰው ሳይሆን ያለ እግዚአብሔር መሆን ነው ። አዳም ተስፋው የክርስቶስ መወለድ ነበረ ። ይኸው ተወለደ ። እርሱ አሻግሮ መወለዱን አየ ፣ እኛ መለስ ብለን መወለዱን አስተዋልን ። ዕለት ዕለት ክርስቶስ መወለዱን የሚያምኑ ጥሙቃን /ተጠማቂዎች በቤተ ክርስቲያን ይገኛሉ ። የእኛ አምላክ አብ የሚወልድ ፣ የእኛ ጌታ ክርስቶስ የሚወለድ ነው ። ሰው በመሆኑ አምላክነቱን አልከሰረም ። ጌታቸው ባለበት መላእክቱ ተገኝተው ምስጋናውን አቀረቡለት ። የዘላለም አባት ፣ በሕፃን መልክ ሲገኝ በመደመም ዝም አሉ ። ቅዱስ ገብርኤል ምን ቢያበስር ይህን የልደት ምሥጢር መልመድ አልቻለም ። እኔ ድሀው ከመላእክት አእምሮ በላይ ለሆነው ልደትህ ክርስቶስ ሆይ ሰላም እላለሁ !

ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ታኅሣሥ 24 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ