የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የኢየሱስ እናት ማርያም

ማርያም የሚል ስም መሰየም የጀመረው የእስራኤል ልጆች በግብጽ መከራ ሳሉ ነው ። መከራው ስፍር ቍጥር የሌለው ፣ ለማምለጥም በባርነት የደከሙ ሕዝቦች የማይችሉት ነበር ። ያ ዘመን አራስ ወንድ ልጅ ሁሉ እየታነቀ የሚገደልበት ፣ ወንድ ጠል ዘመን ነበረ ። በዚያ ዘመን የተወለደችውን የሙሴን ታላቅ እኅት ስምዋን ማርያም ብለው ሰየሙት ። በዚህ ስም ብዙዎች ተጠሩ፡- የዕዝራ የልጅ ልጅም ማርያም ተብላ ተጠርታለች ። የማርታና የአልዓዛር እኅት ፣ ሰባት አጋንንት የወጡላት መግደላዊት ማርያም በዚህ ስም ተጠርተዋል ። የቀለዮጳ ሚስት የማርቆስ እናት በዚህ ስም ማርያም ተብለው ተጠርተዋል ። ከእነዚህ ማርያሞች ልዩ የሆንሽው አንቺ ግን የኢየሱስ እናት ተብለሽ ተጠርተሻል ። ከመጀመሪያዋ የስም ባለቤት ከእኅተ ሙሴ ከማርያም ጋር ብዙ መነጻጸር አለሽ ። እኅተ ሙሴ ማርያም ወንድ በሚገደልበት በፈርዖን ዘመን ወንድምዋን አዳነች ፣ አንቺም ሄሮድስ ሕፃናትን በሚገድልበት ዘመን ልጅሽን ይዘሽ ተሰደድሽ ። ያቺ ማርያም እኅተ ሙሴ ተብላለች ፣ አንቺም ወንድም ተብሎ በለበሰው ሥጋ ለተጠራው ልጅሽ በቤተ ክርስቲያን አካልነትሽ እኅተ ኢየሱስ ትባያለሽ ። ማርያም እኅተ ሙሴ እስራኤል ቀይ ባሕርን በተሻገሩ ጊዜ ከሁሉ ቀድማ ከበሮ ነጥቃ ፣ ደናግልን ይዛ “ንሴብሖ” ብላ ዘመረች (ዘጸ. 15፡20)። አንቺም ባሕረ ሞት ሲከፈል ፣ ልጅሽ አማናዊ ሙሴ ሁኖ ዓለምን ሲያሻግር ባየሽ ጊዜ ከሁሉ ቀድመሽ “ታዐብዮ ነፍስየ ለእግዚአብሔር” ብለሽ ዘመርሽ (ሉቃ. 1 ፡ 46) ። ሙሴ የልጅሽ ምሳሌ ነው ፣ ማርያምም ያንቺ ምሳሌ ናት ። ሙሴ የብሉይ ኪዳን መካከለኛ ነው ፣ ልጅሽ የአዲስ ኪዳን ሊቀ ካህን ነው ። ሙሴ መቃብሩ አልተገኘም ፣ ልጅሽም መቃብሩን ባዶ አድርጎ ሽቅብ በደብረ ዘይት ዐርጓል ። ሙሴ የልጅሽን ሰው መሆን ፣ መልኩን ማየት ይናፍቅ ነበርና ከመቃብር አሥነስቶ በደብረ ታቦር ፊቱን አሳየው ። ልጅሽ የሚወዱትን ያከብራል (ማቴ. 17 ፡ 3)።

የኢየሱስ እናት ማርያም ሆይ የመውለጃሽ ሰዓት በተቃረበ ጊዜ የፀጥታ ስጋት የነበረበት አውግስጦስ ቄሣር የዓለም ሕዝብ ይቆጠር ብሎ ትእዛዝ አወጣ ። ሁሉም ወደ ተወለደበት አገር ይግባ ብሎ አዘዘ ። ነገሥታት ያዝዛሉ እንጂ ያዘዙት እንዴት እንደሚፈጸም ማሰብ አይፈልጉም ። ሁሉም ወደ አገሩ ከገባ እርሱም ወደ ሮም መግባት ፣ በሮም መወሰን ነበረበት ። ነገር ግን ልጅሽ የእኛን ሥጋ ለብሶ ፍጹም ሰው ሁኗልና ፣ ከዓለም ሕዝብ እንደ አንዱ ሁኖ ለመቆጠር ፣ በዓለም መዝገብም ለመስፈር ፈቃዱ ሆነ ። ከናዝሬት ረጅሙን ጎዳና ይዘሽ ስትመጪ እስራኤል በሮማውያን እጅ መውደቋን ታስቢ ነበር ። ከባቢሎን ምርኮ በኋላ የፋርስና የሜዶን ጥምር መንግሥት በዓለም ላይ ገነነ ። እርሱ ሲወድቅ የግሪክ መንግሥት ተንሠራፋ ። የግሪክ መንግሥትም ደክሞት ለአዲሱ የሮማ አገዛዝ ስፍራ ለቀቀ ። የሮማው አገዛዝ የመጨረሻ ነው ። ምክንያቱም ልጅሽ በዚህ ዘመን ተወልዶ መንግሥቱን በዓለም ላይ መሥርቷልና ። የመልአኩ ብሥራትም የመጨረሻው መንግሥትና ለመንግሥቱ መጨረሻ የሌለው ልጅሽ መሆኑን አሳውቆሻል ። ይህን ለዳንኤል በትንቢት አስቀድሞ የገለጠው ቅዱስ ገብርኤል ነው ፣ ፍጻሜውንም ከ600 ዓመታት በኋላ ላንቺ ሊነግር መጣ ። መንግሥታት ያስጨነቁአቸው ሕዝቦች የመጨረሻው መንግሥትና ለመንግሥቱ መጨረሻ የሌለው ልጅሽ ነውና ዛሬ ደስ ይበላቸው ።

እመ ኢየሱስ ማርያም ሆይ ! በሳምራውያን መንገድ ሳይሆን በዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ ስትመጪ እስራኤል የተሻገሩትን ያንን ወንዝ ባየሽ ጊዜ ምን አስበሽ ይሆን ? በጩኸት የፈረሰችውን ኢያሪኮን ባየሽ ጊዜ የጸሎትን ኃይል ታስቢ ነበር ። ማዶውን ሙት ባሕርን ስታይ የኃጢአት ዋጋ ምን መሆኑን አሰብሽ ። ከሙት ባሕር አጠገብ የተሰባሰቡት ፣ የሃይማኖት ፖለቲካ የሰለቻቸውን የኵምራን ገዳማውያንን እያሰብሽ ነበር ። ሃይማኖትና ፖለቲካን አጋብተው የሚኖሩትን ፈሪሳውያን ትተው ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብና በመገልበጥ ሥራ የተጠመዱት የኵምራን ማኅበረሰብ በልብሽ ምን ዓይነት ስፍራ አግኝተው ይሆን ? ብርዱ በጸናበት ፣ በረዶ በሚጋገርበት በዚያ ወራት ቤተ ልሔም ስትደርሺ ጊዜው መሽቶ ፣ ድካሙም በዝቶ ፣ ብርዱም እንደ ጅራፍ የሚገርፍ ነበር ። ላንቺና ለልጅሽ የሚሆን ስፍራ በእንግዶች ማደሪያ አልተገኘም ነበር ። ዓለም ለእውነትና ለእውነተኞች ስፍራ የላትም ። አስቀድመው ስስት ፣ ትዕቢትና ፍቅረ ንዋይ ስፍራ ይዘዋልና የሚቆረስ ፍቅር መቀበል አይችሉም ። ሰው ገፍቶሽ እንስሳት ተቀበሉሽ ፣ በእስትንፋሳቸውም ልጅሽን አሞቁት ። በዚህም የነቢዩ ትንቢት ተፈጸመ ። “በሬ የገዢውን አህያም የጌታውን ጋጣ አወቀ እስራኤል ግን አላወቀም፥ ሕዝቤም አላስተዋለም።” (ኢሳ. 1 ፡ 3)። ቆይቶም በአህያ ጀርባ ተቀምጦ ኢየሩሳሌም ይገባል ። በተናቀው ስፍራ የተናቅነውን ሊያከብር መጣ ። በረት በውኃ ይጸዳል ፣ በረት ማንነታችን ግን በደሙ ይነጻል ። ከሰማይ ወረደ ፣ ከቤተ መንግሥታቸው ወርደው ድሀ ማየት የማይፈልጉትን በተግባር ገሠጸ ። በእንስሳት መኖ መካከል ተኛ ፣ ተፈጥሮን እንደሚያከብር አስታወቀ ። ከአብ ያለ ድካም ፣ ካንቺም ያለ ሕማም ተወለደ ። የሔዋን ምጥም ባንቺ ተሻረ ። እርሱ ቡሩክ ነውና ከመርገማችን ጋር አልተወለደም ፣ ስለዚህ ምጥ የለብሽም ። የእኛ ኃጢአት የሌለበት የእኛ ሰው ነው ። ኃጢአታችንን ተሸከመ እንጂ ኃጢአተኛ አልሆነም ። የኢየሱስ እናት ማርያም ሆይ የቤተ ልሔሙን ሕፃን ከኢሳይያስ ጋር “የዘላለም አባት” ብለን እንጠራዋለን (ኢሳ. 9 ፡ 6)። የዕለት ሕፃን ፣ እርሱ የዘላለም አባት ነውና ።

የዳዊት ልጅ በዳዊት ከተማ ማደሪያ አጣሽ ! ኢየሩሳሌምን የሠራው አባትሽ ሳለ አንቺ ግን ቍራሽ መሬት ተነፈግሽ ! መውለጃ ቦታ አጥተው በሜዳ ፣ በዋሻ የሚወልዱ ፣ ልጆቻቸውን ለማልበስ ቅዳጅ ጨርቅ አጥተው በጎዳናው ብርድ የሚንጠረጠሩ አንቺን ሲያስቡ ይጽናናሉ ።

የኢየሱስ እናት ሆይ ዛሬም የሰው ልብ ለታካችነት ተከፍቶ ለትጋት ስፍራ አጥቷልና ልጅሽን ለምኚ !

ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥር 4 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ