እግዚአብሔር የለም በሚባልበት ዘመን አንድ አገልጋይ የሆኑ ሰው ዘመን ወዳመጣው ክህደት ተሳቡ ። በአደባባይም “እስካሁን በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ስንል ኖረናል ፤ ከዚህ በኋላ ግን በስመ ሌኒን ወማርክስ ወኢንግልስ አሐዱ ሶሻሊስት እንላለን” አሉ ። እኒህ ሰው ዘመኑን ለመምሰል ብለው የጀመሩት ከመጨረሻው ኃጢአት ነው ። ሰይጣን እንኳ ሀልወተ እግዚአብሔርን አይክድም ። ሰው ግን ደፋር ነው ። የማይሞተውን አምላክ በሚሞቱ አብዮተኞች መተካት ያሳዝናል ። እግዚአብሔር የለም ብለው ዓለምን ያስካዱ አገሮች ካሉ የመጀመሪያዋ ሩስያ ናት ። ትርፏም እልቂትና ውድቀት ነበር ። ዛሬ በሩስያ ሁሉም አማኝ ነው ። የሀገሪቱ መሪም አስቀዳሽ ናቸው ። “ዓርብ ረቡዕን ገደፍን በሥጋ ባዋዜ ፣ እንዲህ ለሚያልፈው ለማይቆየው ጊዜ” ተብሏል ። ግጥሙ ዓርብ ረቡዕ ሥጋ መብላት የተራማጅነት ምልክት ተደርጎ የተወሰደበትን ዘመን ያስታውሰናል ። አንዳንድ ዘመን ከባድ ነው ። ካህንን ከሀዲ ፣ ሰባኪን ፖለቲከኛ ያደርጋል ። እኒህ ከላይ የጠቀስናቸው ሰው የአብዮቱ አጋር ፣ የእግዚአብሔር የለሽ ሥርዓት መልእክተኛ ለመሆን ብለው ይህን አደረጉ ። ዘመን ከሚያልፍብኝ ዘላለም ይክዳኝ አሉ ። ለሚያልፍ መንግሥት የማያልፈውን መንግሥተ ሥላሴ ለማጣት ወሰኑ ። ሒሳብ እንኳ አያውቁም ነበር ። የሚገርምው የእኒህ ሰው ደመወዝ ከቤተ ክርስቲያን ነበር ። ከእግዚአብሔር ቤት እየጎረሱ ወደ ዓለም የሚውጡ ጥንትም ዛሬም አሉ ። እርሳቸው ደመወዝ የሚበሉት እግዚአብሔር አለ ብለው የሚያምኑ ምእመናን በሰጡት አሥራት በኵራት ነው ። የእግዚአብሔር መኖር ለእርሳቸው እንጀራ እንኳ አስፈላጊ ነው ። በእምነት በተሰበሰበ አሥራት ከሀዲዎችን ማገልገል ግን ይገርማል ። መድኃኔ ዓለም እየጠሉትም እንጀራ ነው ።
ብዙ የነገረ መለኮት ተቋማት ሰዎች በእምነት ገብተው በእውቀት የሚወጡበት ፣ አንዳንዶችም እምነታቸውንና ሞራላቸውን የሚከስሩበት ነው ። መንፈሳዊ ትምህርት በመንፈሳዊነት ካልተሰጠ ፣ ነገረ መለኮት ከአምልኮተ እግዚአብሔር ጋር ካልቀረበ አደጋው ትልቅ ነው ። ቢሆንም የነገረ መለኮት ተቋማት አማንያን በሚያወጡት አሥራት በኵራት የተቋቋሙ ናቸው ፣ ስለዚህ ከሀድያን እንዳይወጡባቸው ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ።
የዘመን ሐዋርያ የሆኑ ሰዎች ራሳቸውን የለውጥ ሐዋርያ ብለው ይሰይማሉ ። በእግዚአብሔር ቤትም የፖለቲካ ወኪል ይሆናሉ ። ከእግዚአብሔር ካህንነት የመንግሥት ካድሬነት ፣ ከመላእክት ጥበቃ የደኅንነቶች ስልክ ቍጥር ፣ ከሰማይ ቤት የቁጠባ ቤትን ይመርጣሉ ። ዋጋቸውን አሳንሰው ፣ በሰማይ ጀምረው በምድር የሚጨርሱ ናቸው ። ይቅርታን የሰበከ ቂምን ሲዘራ ፣ አንድነትን የተረከ መለያየትን ሲያውጅ ፣ አማኒው ስሜታዊ ሲሆን የዘመን ሐዋርያ ሁኗል ማለት ነው ። ቢሆንም ለሚያልፍ ቀን የማያልፍ ንግግር መናገር ተገቢ አይደለም ። ቅዱስ ጳውሎስ ግን የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ነበር ።
ሐዋርያነት ከማዕረግ ይልቅ ሥራን የሚያሳይ ነው ። ራሳቸውን ሐዋርያት ቢሉ ኖሮ ቢጽ ሐሳውያን/ሐሰተኛ ወንድሞች እንላቸው ነበር ። ክርስቶስ ግን ሐዋርያት ስላላቸው ሐዋርያ ተብለው ይኖራሉ ። ሐዋርያ ማለት ጥሬ ትርጉሙ ሒያጅ ፣ ገስጋጅ ማለት ነው ። የክርስቶስን ስምና መልእክት ተሸክሞ የሚፈጥን ማለት ነው ። መልእክቱን የሚያደርሰው ደግሞ ለሰው ነው ፤ ሰው ደግሞ ሞት የሚባል አባራሪ ያለበት ነው ። ከሞት ይልቅ ካልፈጠነ ሰውን ማትረፍ አይችልም ። ስለዚህ ይገሰግሳል ። ገስጋሽ ነውና ኑ ብሎ የሚጠራ ፣ ካልመጡ ብሎ የሚቀር አይደለም ። ዓለምን ድንበር ፣ ጽንፍን ዳርቻው አድርጎ ይገሰግሳል ። ሐዋርያነት ወንበር ላይ የሚገላበጡበት ሹመት አይደለም ። የበላይ ሁነው ሁሉን ታች የሚያዩበት አለቃነትም አይደለም ። በገጠር በከተማው ፣ በቆላ በደጋው ሰውን ለማትረፍ መገስገስ ነው ። ሐዋርያ ሲያልፍ ፣ ሲገሰግስ ይታያል እንጂ ቆሞ ሲሳደብ ፣ የሰው ስም ሲያነሣ ፣ ድንጋይ ሲወረውር አይታይም ። ጊዜ የለውም ። ሰውን ከዘላለም ሞት ለማዳን ይሮጣል ። ሕፃን ልጅ ከመደቡ ወርዶ በእሳቱ ቅላት ተማርኮ ወደ ፍሙ ሊገባ ሲል ወላጅ በታላቅ ፍጥነት እንደሚገሰግስ ፤ በዓለም አታላይነት ተይዘው የጠፉትን ፣ ይግባኝ ወደማይጠየቅበት ፍርድ እየወረዱ ያሉትን መታደግ ሐዋርያነት ነው ። እነዚህ ሰዎች ጥንትም ነበሩ ፣ ዛሬም አሉ ። እስከ ዓለም ፍጻም እንደ ቃሉ ይኖራሉ ። ሐዋርያት መካን አይደሉምና ። ማቴ. 28፡20 ።
ሐዋርያት ቋሚ አድራሻ አልነበራቸውም ። እንደ ሰው አነጋገር ብንናገር ኑሮአቸውም ሞታቸውም ያማረ አይደለም ። “አሟሟቴን አሳምርልኝ” እንደሚባለው ፣ ያማረ አሟሟት በዘመድ ተከቦ መሞት ሳይሆን ለእውነት ዘመድ አጥቶ መሞት ነው ። ሐዋርያት ግን አኗኗራቸውን በቆራጥነት አሳመሩት ፣ አሟሟታቸውን ደግሞ ገዳዮቻቸው አሳመሩት ። እነርሱ ባይገድሏቸው ሰማዕት አይባሉምና ። ጠላቶቻችን ማዕረግ ይጨምሩልናል ። ሐዋርያት ለክርስቶስ ስለ ኖሩ ሞትን እንደ ሙሽርነት ቀን ናፈቁት ። በትክክል የኖረ ሞቱ አያስፈራውም ። ሲኖሩ ከዕቁብ መገለልን ፣ ሲሞቱ ዕድር ማጣትን አላሰቡም ። ስለ ክርስቶስ እንደ ጨው ዘር ተበተኑ ። መልእክታቸውም ቃል ሳይሆን ሕይወታቸው ሆነ ። እግዚአብሔር ይወዳችኋል ከማለት በክርስቶስ ፍቅር ሰዎችን ወደዱ ። የጨው ዘር ናቸውና ከቤተ መንግሥት እስከ ደሀዋ ቤት ተገኙ ። በዚህም የብዙዎችን ሕይወት አጣፈጡ ። አዎ ቅዱስ ጳውሎስ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ነበረ ። እኛስ የማን ሐዋርያ ነን ?
ኤፌሶን ትርጓሜ/2
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥር 19 ቀን 2014 ዓ.ም.