የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የእግዚአብሔር ባሪያ

ወቅቱ ያልወለደች ማኅፀን ፣ ያላጠባች ጡት የተባረከች ናት የሚባልበት ፣ ወላድ በመውለዷ የተጸጸተችበት ዘመን ነበር ። ልጅን እንደ ወለዱት በክፉ ቀንም መልሰው ቢውጡት ጥሩ ነበር ። አንቺን አልፈልግም ብሎ ልጇን ለሞት የሚፈልግ ፣ እኔ ልለወጥ ብትል የእናትን ቤዛ መሆን የማይቀበል ቀን ከባድ ነው ። ቀን ሲከፋ ያሳደጉትም ውሻ ይነክሳል ። ያበሉት ጠላት ፣ ያኖሩት ገዳይ ይሆናል ። ማኅፀን የዘጠኝ ወር ቤት እንጂ  የሰባና የሰማንያ ዓመት መኖሪያ አይደለም ። እናት ምነው ባልወለድሁ የምትልበት ፣ ልጅም ምነው ባልተወለድሁ ብሎ የተወለደበትን ቀን የሚረግምበት ዘመን አለ ። ሲወለድ ያዩት የትላንቱ ሕፃን ሲሞት ማየት ከባድ ነው ። ኋላ የመጣው ማሙሽ ቀድሞ ሲሄድ ልብን የሚሰብር ነው ። ሰው የጨከነበት ፣ ወልዶ የበላበት ፣ አሳድጎ የቀጠፈበት ዘመን ነበር ። ከሽፍታ መንግሥት ያስጥላል ፣ መንግሥት ሽፍታ ሲሆን ግን ማን ያስጥላል  የምድር ነገሥታት በቅዱስ መጽሐፍ ላይ በአውሬ ተመስለዋል ። ለሥልጣን ልጃቸውን የሠዉ ፣ ሕዝብ የጨረሱ ፣ እናታቸውን የገደሉ ናቸውና ። ንጉሥ ተብሎ በግ የተባለ ክርስቶስ ብቻ ነው ። የገደለን ሳይሆን የሞተልን ነውና ። ወዳጅ ሲጠቁም ገዳይ የሚታዘብበት ፣ ጎረቤት ሲተኩስ ጥይት ራርቶ የሚስትበት ዘመን ነበር ፤ ያ ዘመን ።

በችሎት የቆመው አንድ ደግ አባወራ ዳኛው፡- “ወዳጅህን ይዘህ ና” ቢለው ውሻውን ይዞ መጣ ። “ጠላትህን ይዘህ ና” ሲለው ሚስቱን ይዞ መጣ ። ሚስቱ በሰላም ቀን ያወሩትን በክፉ ቀን አደባባይ ዘርታዋለችና ። ያ ዘመን እንኳን ባልንጀራ ልብ የማይታመንበት ዘመን ነበር ። እንደ ገለባ የሚያቀልል ዘመን አለ ።

ወዳጅና ጠላት ፣ ዘመድና ባላጋራ ፣ ሟችና ገዳይ የሚቀላቀሉበት ዘመን አለ ። ጦርነቶች ሁሉ ለሰልፍ የደረሰውን ጎበዝ ለመቍረጥ ይቀሰቀሳሉ ። ይህኛው ጦርነት ግን የሚወለዱትን ሕፃናት የሚቀጭ ነበር ። ሕፃናት ዘጠኝ ወር ካምስት ቀን ተረግዘው አንድ ሰዓት በዚህች ዓለም ላይ እንዲኖሩ አይፈቀድላቸውም ነበር ። ቀጣይ ጉዞ ያለው መንገደኛ በአየር ማረፊያው አንድ ቀን ያድራል ፣ ወይም አንድ ሰዓት ቆይቶ ይበርራል ። ከማኅፀን ዓለም በቀጥታ ወደ ሰማያዊ ዓለም መሄዳቸው እነዚያ ሕፃናት ያሳዝናሉ  ። ማርና ወተትን ሳይለዩ ፣ የተዘጋጀውን የጡቱን እፍታ ሳይቀምሱ ፣ የሚፈውሰውን እንገር ሳይጠጡ ይታነቁ ነበር ። ለሚሞት ሰው መድኃኒት ምኑ ነው  እናትም ምጡን እንጂ ልጁን ማየት አልታደለችም ነበር  ። ልጁን እያሰቡ ማማጥ ደስታ ነበረ ። ሞትን እያሰቡ ማማጥ ከሌሊት በኋላ የመጣ ሌሊት ያሰኛል ። ከእግዜር የመጣ ቍጣ ሳይሆን ሰው ለሰው የደገሰው ክፉ መርዝ ነበር ። ያ ዘመን ወንድ ልጅን የጠላ ዘመን ነበር ። የወንድን ቍጥር ለመቀነስ የተነሣ ዘመን ነበር ። በሰልፍ ሳይሆን በልደት ብዙ ወንዶች ይሞቱ ነበር ።

የወንድ ልጅ እናት ታጠቂ በገመድ ፣
ልጅሽን አሞራ እንጂ አይቀብረውም ዘመድ ፤

ቢባል ወግ ነበረ ። እነዚያ ሕፃናት አንድ ቀን ሳይኖሩ እስከ ወዲያኛው ይሞታሉ ። ኖሩ ሳይባል ሞቱ መባል ከባድ ነው ። አንድ ቀን ንጹሕ አየር ሳይተነፍሱ በተውሶ ተንፍሰው መሞታቸው ያሳዝናል ። አዋላጆች ገዳዮች የሆኑበት ጊዜ ፣ ነገሥታት ከእርጥብ ጨቅላዎች ጋር የተጣሉበት ዘመን ነበር ። ነገሥታት ጠብ ካልናቁ ከጽንስም ይጣላሉ ። ወዳጅነታቸው ወረት ያለበት ነውና ጥንቃቄ ይፈልጋል ። ፍቅራቸው ያሳብዳል ፣ ጠባቸው ይቀብራል ። ተጣላኝ ብቻ ሳይሆን የተወለደው የዛሬ ሃያ ዓመት አድጎ ሊጣላኝ ይችላል ብለው ያንቃሉ ። ለአዋላጅነት የተማሩት የገዳይነት ሥልጠና ሳይወስዱ ገዳይ ሆኑ ። ከትምህርት ባሻገር መቆም ፣ የባከነ እውቀት ነው ። ማዳን እንጂ መግደል ሙያ አይጠይቅም ። ሕፃናት በማኅፀን በራፍ ላይ ሞት እንደሚጠብቃቸው ቢያውቁ ኑሮ አልወለድም ብለው ይጮኹ ነበር ።

እንኳን ሕፃናቱ አራዊትና ከብቱ ፣ ሣሩና ቅጠሉ የእነርሱ ሳለ መኳንንትና ነገሥታት ሕፃናትን ለማነቅ ተነሡ ። ሳይኖሩ መሞት ፣ የአንድ ቀንን ፀሐይ ሳይሞቁ ማለፍ በእውነት ልብ ይነካል ። ልጁ ለራሱ ለማዘን ፣ ገዳይን ለመማጸን እውቀትም አቅምም የለውም ። ማርና ወተትን ፣ ሞትና ሕይወትን ሳይለይ ይሞታል ። የወለደች እናት ፣ ያማጠች ሴት ግን ታዝናለች ።

ልጇን ቀለመ ወርቅን ቅኔ ቢማር ብላ ዋሸራ የሰደደች የጎጃም እናት በትምህርት ቤቱ እሳት ተነሥቶ ልጇ እንደ ሞተና አመድ እንደሆነ ሰማች ። ኀዘን የቅኔ መገኛ ነውና እንዲህ ብላ በአለቀሰች፡-

ይማርልኝ ብዬ ዋሸራ ሰድጄ ፣
ቀለም ገባው አሉ እሳት ሆነ ልጄ ።

በአገራችን ዐፄ እንደ ማለት የግብጽ ነገሥታት የሚጠሩበት የክብር ስም ፣ ስመ መንግሥት “ፈርዖን” የሚል ነበረ ። ፈርዖኖች በጭካኔ የታወቁ ናቸው ። ታላቁ ቤተ መንግሥታቸውን በዓባይ ዳር የመሠረቱ ፣ የዝናብ ጥገኛ ስላልሆኑ ዓለም ሲራብ የሚተርፉ ናቸው ። ዓባይና ሊቃውንት ሲያልፉ ዝም ብላ የምታይ ፣ ካለፉ በኋላ የምትዘፍን ኢትዮጵያን ጥሎላቸው በሰላም ይኖራሉ ። ቋንቋቸው ቅብጥ የሚባል የቀበጦች ቋንቋ ነው ። እስልምና መካከለኛውን ምሥራቅ አልፎ ወደ ግብጽ ሲመጣ ቋንቋዋን ከቅብጥ ወደ ዐረብኛ ለወጠባት ። የነገሥታቱም ስም ከፈርዖን ወደ ከሊፋ ተለወጠ ። በታላቁ እስክንድር ስም የተሰየመችው እስክንድሪያም ዋና ከተማነቷ አብቅቶ በአሥረኛው ክፍለ ዘመን ካይሮ ዋና ከተማ ሆነች ። ግብጽ አፈርና ውኃን ከኢትዮጵያ ምድር የምታገኝ ብትሆንም ፣ በአፈሩ ዘርታ ፣ በውኃው አብቅላ አንድ ቀን እንኳ ኢትዮጵያን እሸት ቅመሺ ብላ አታውቅም ። በኢትዮጵያ የረሀብ ዘመን እንኳ ከማላገጥ በቀር አንድ ኩንታል እህል አልረዳችም ። እንደ ስምዋ ቅብጥ ፣ ቀበጥ ናትና አድርጉልኝ ብቻ የምትል ፣ ተቀብላ የማታመሰግን ፣ እኔን ብቻ ይድላኝ የምትል ናት ። የኮፕት ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳትም ኢትዮጵያውያን ከገዛ መምህራኖቻቸው ጳጳሳት መሾም አይችሉም ብለው ለ1600 ዓመታት ያህል በመንፈሳዊ ባርነት ሥር አውለውናል ። ጳጳሳቱም በአብዛኛው የዓባይ የበላይ ጠባቂ እንጂ የሕዝቡ መንፈሳዊ እረኛ አልነበሩም ። በግብጽ ያሉ ክርስቲያኖች በከሊፋዎች እንዳይጠቁ በኢትዮጵያ ያሉ እስላሞችን የሚንከባከቡ ነበሩ ። ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንንም እያወገዙ ፣ መሃይሙንና ወረኛውን ምሥጢር መጋቢ እያሉ የሚጠሩ ነበሩ ። ይህም መንፈሳዊ ባርነት የተሰበረው አቡነ ባስልዮስ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ በሆኑ በ1951 ዓ. ም. ነው ።

ከአባ ፍሬምናጦስ ጀምሮ 111 የግብጽ ጳጳሳት የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያንን አስተዳድረዋል ። ጳጳሳቱም ይመጡ የነበረው በወርቅ እጅ መንሻ ነበረ ። አፈሩና ውኃው ሳያንስ ወርቁ ይጋዝ ነበር ። ወርቁም ካይሮ ሲደርስ እኩል ለቀዳሽ ፣ እኩል ለነጋሽ ብለው የኮፕት ቤተ ክርስቲያን መሪዎች ከከሊፋዎች ጋር ይካፈሉት ነበር ። ኢትዮጵያ ለተወለደባት ኮሶ ፣ ለባዕድ እንጀራ የምታቀርብ ፤ የባዕድ እናት ፣ የልጆችዋ እንጀራ እናት ናትና የራሷን ሊቅ እያወገዘች መሃይም የሆኑትን የደጅ ሰዎች ስታከብር የምትኖር ናት ። ይህ እዩኝና ውደዱኝ ማለት ዛሬም ስላልለቀቃት ፣  ኢትዮጵያ የአፈ ቀላጤዎችና የባዕዳን እንጀራ ናት ።

ይቀጥላል

የእግዚአብሔር ባሪያ/1

ሰኔ 1 ቀን 2012 ዓ.ም.

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ