ዓለም ሳትጠላው ቀድሞ የጠላት ሰው ልቡን ከኀዘን ይጠብቃል። ዓለምን እየወደደ እርስዋ የጠላችው ስብራቱ ብርቱ ነው። ዓለም እስከ መጨረሻው የምትወደው ማንም የለም። ዓለም ወረተኛ ናት። በየሰው ቤት መዞር ትወዳለች። ካረፈደችበት ቤት አትውልም፣ ከዋለችበት ቤት አታድርም። ዓለም ስትመጣ የምታልፍ አትመስልም፣ ስትሄድም የምትመጣ አይመስልም። የነጋላቸው የሚመሽ አይመስላቸውም፣ የመሸባቸውም መንጋቱን ይጠራጠራሉ። ቋሚ ነገር የለም፣ ሁሉም ነገር ለመለወጥ ይቸኩላል ። በእግዚአብሔር ሥርዓት ሌሊት ይቀድማል፣ ቀን ይከተላል። ዓለም ግን ጣፋጩን አስቀድማ ቀጥሎ እሬቱን ታልሳለች፣ ጣፋጩ ሐሰተኛ ፣ ምሬቱ እውነተኛ ነው።
ዓለም ኪራይ ናት። አንድ ቀን ውልቅ ብለው ይወጡባታል። በዓለም ላይ ሁሉም ተከራይ ነው፡፡ ተከራይ ጊዜያዊ ነው ፣ ሕይወትም በምድር ላይ ቆይታዋ አጭር ነው። ተከራይ ጓዝ ማብዛት የለበትም፣ ሰውም ትጥቁን አጠር ማድረግ አለበት። ተከራይ ምንም ቢከርም መውጣቱ አይቀርም፣ ሰውም ምንም ቢሰነብት መሄዱ አይቀርም። ተከራይ የራሱን መኖሪያ ይናፍቃል፣ ሰው ከመቆያ ዓለም ወጥቶ የሰማይ መኖሪያውን ሊናፍቅ ይገባዋል። ዓለም መቆያ ናት ፣ መኖሪያችን በሰማይ ነው። የለፋንበትን ማንም ይበላዋልና በቁመና መስጠት ይገባል። ለሚፈርሰው ቤታችን ለፍተን ለማይፈርሰው ቤታችን ምንም አለመሥራት አለመታደል ነው። ጠዋት ላይ የዕድር ጡሩንባ ሲነፋ አንድ ተከራይ ለቀቀ ማለት ነው። ተከራይ ሲለቅ ካሣ የለውም ፣ ሰውም ከሄደ በኋላ ተመልሶ አይመጣም። መንገዱ መሄጃ እንጂ መመለሻ የለውም። እስካሁን ሄደው የተመለሱ የሉም፣ በየቀኑ የሚሄዱ ግን ብዙ ናቸው። ሞትን ብናምንም መሞታችንን ግን አናምንም። እኛም ወደዚያው ነን። የሤራው ጉባዔ፣ የአድማው ስብሰባ ሞትን አለማሰብ ነው። ሰውን ብንንከባከበውም ሟች ነው፣ ታዲያ ለመግደል ለምን ፈጠንን ? እንቅልፍ አጥተን ስናሴር እንቅልፍ አጥተን ለምን አንጸልይም ?
ሁሉም ነገር ጊዜያዊ ነው፣ እግዚአብሔር ብቻ ዘላለማዊ ነው። ቤቱም መኪናውም እሳት ይበላዋል። በምንተኛበት ክፍል በኩል መንገድ ይወጣል። ደርሰን ስንመለስ የሚገኝ ነገር የለም። ያለውና የሚኖረው፣ ሳይለወጥ ሁሉን የሚለወጠው የእኛ አምላክ እግዚአብሔር ብቻ ነው። በአሥር ሚሊየን የሚቆጠር ሰው የገደሉ እነስታሊን ዛሬ የሉም። ገዳዩም ሟች ነው። ታላላቅ የጦር ሜዳ ጀግኖች ሞትን ማሸነፍ አልቻሉም። ብዙ ርስት የነበራቸው በሦስት ክንድ ከስንዝር መሬት ተጠቃለዋል። እኮ ታዲያ ክፋት ምን ይሠራል?
አዛዥም ናዛዥም መሆን ለጊዜው ነው። ስንቱን የጣለ ያ ክንድ በቀጭን ፈትል ይታሰራል፣ መግነዙን ሊበጥስ ኃይል የለውም። ዛሬ በተወጠረ ልብስ የምናሳየው አካል ነገ ለመፍረስ ይቸኩላል። የኖርንለት ስም ተሽሮ የደበቅነው ስመ ክርስትና ሲጠራ ይውላል። ዓለም ኪራይ ነው። አንድ ቀን ጥለነው እንሄዳለን። ያ ቀን ዛሬ ሊሆን ይችላል። እኮ ያዘነብንን ያለቀሰብንን ሰው እንዴት ይቅርታ አንጠይቅም?
ልጄ ሆይ መንገድህን አሳምር።
ዛሬ ስትሾም በተሻረው ሰው ቦታ ላይ ነው። አንተም አንድ ቀን ትሻራለህ። ማማር ለሁልጊዜ አይደለም። ሁልጊዜም መመንዘር አይኖርም። ሁልጊዜ ደፋርነትም አይገኝም፣ ፍርሃት የሚያንቀጠቅጥበት ቀን ይመጣል። ዛሬ ሲጠሩህ አትሰማም፣ ነገ ብትጣራ የሚሰማህ አይኖርም። ልጄ ሆይ መንገዶች ሁሉ ወደ ሮም አያደርሱም። የሚያደርሰው መንገድ አንድ ነው። ሁሉ በሁሉ የሆነውን ክርስቶስን እመን!
ዓለም የኪራይ ቤት ናት። የፈረቃ ክርስትና ይብቃህ። ዓለም ከእንግዲህ ቤት አትሆንም። መታከትህ፣ መፍጨርጨርህ ፣ ማዘንህ፣ መተከዝህ በልክ ይሁን ። እያኖርህ ያለው የኖርክላቸው ሰዎች ሳይሆኑ የረሳኸው እግዚኣብሔር ነው። ለእርሱ እጅህን ስጥ። ምርኮኛን ልጄ ብሎ መጥራት ልማዱ ነው። ለአክባሪው ተማረክ ! እኔንም በተቀደሰች ጸሎትህ አስበኝ !
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ኅዳር 3 ቀን 2017 ዓ.ም.